Saturday, 25 January 2020 11:32

ጠ/ሚኒስትሩ ከደቡብ ክልል ተወካዮች ጋር ተወያዩ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ከደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ከተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የህዝብ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት የክልልነት፣ ዞንነትና ልዩ ወረዳነት ጥያቄዎች በስፋት ቀርቦላቸዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደውና ከ3ሺህ በላይ የሚሆኑ ከሁሉም የደቡብ አካባቢዎች ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር በተደረገው ውይይት፤ የክልልነት ዞንነትና ወረዳነት ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡
56 ብሔር ብሔረሰቦችን ያሰባሰበውና መቀመጫውን ሃዋሳ አድርጐ ክልሉን ሲያስተዳድር የቆየው የደቡብ ክልላዊ መንግስት፤ በአካባቢዎቹ ፍትሃዊ የሃብትና መሠረተ ልማት ክፍፍል እንዲሠፍን አለመስራቱ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮች መባባሳቸው የክልልነትና ዞንነት እንዲሁም ልዩ ወረዳነት ጥያቄዎች ተጠናክረው ለመቀጠላቸው ምክንያት መሆኑን የመድረኩ ተሣታፊዎች አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር፣ የመንገዶች አለመመቻቸት እንዲሁም በቋንቋ ለመዳኘት የመቸገር ሁኔታዎች፣ ለእነዚህ ጥያቄዎች መበራከት ገፊ ምክንያት መሆናቸውም ከተሰብሳቢዎች ተነስቷል፡፡
አሁን ባለው የደቡብ ክልል አስተዳደር ሁኔታም፣ ክልሉ አንድ ላይ የመቀጠሉ እድል ዝቅተኛ መሆኑንም ከተሰብሳቢዎቹ በስፋት ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት የከፋ፣ ጌድኦ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ወላይታ የክልልነት ጥያቄዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንና በመድረኩም ከእነዚህ አካባቢዎች ተወክለው የተሳተፉ ተሰብሳቢዎች ተመሳሳይ የክልልነት ጥያቄ ማንሳታቸውን የስብሰባው ተሳታፊዎች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ስብስባ በዋናነት የደቡብ ክልል እጣ ፈንታ ምን ይሁን? የሚለው አጀንዳ ሆኖ የዋለ ሲሆን፤ ጠ/ሚኒስትሩ የክልልነት፣ ዞንነትና ልዩ ወረዳነት ጥያቄ የህዝብን ፍላጐት መሠረት ተደርጐ የሚፈታ ህገ መንግስታዊ መብት መሆኑንም አስገንዝበው፣ መንግስት በቀጣይ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ ከመላው የደቡብ ክልል የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች መሳተፋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡


Read 961 times