Saturday, 25 January 2020 11:59

ኦፌኮ የምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ አልገባሁም ብሏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 - “የአቶ ጀዋርን ዜግነት ለማረጋገጥ እያጣራሁ ነው”
            - ዜግነታቸውን ማረጋገጥ ካልቻሉ ፓርቲው ህልውናውን ለማስጠበቅ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ይኖራሉ”

            የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከምርጫ ቦርድ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ በቅርቡ አባል በአባልነት የተቀበላቸውን የአቶ ጀዋር መሀመድን የዜግነት ጉዳይ እያጣራሁ ነው ብሏል፡፡ ግለሰቡ ማስረጃቸውን ለማቅረብ በሂደት ላይ መሆናቸውንም ፓርቲው ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
‹‹በአቶ ጃዋር በኩል ዜግነታቸውን ለማረጋገጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ተገንዝበናል›› ያሉት የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ አቶ ጀዋር ዜግነታቸውን ለማረጋገጥ  የማይሳካላቸው ከሆነ፣ ፓርቲው ሕልውናውን ለማስጠበቅ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ይኖራሉ ብለዋል፡፡ እንዴት ኢትዮጵያዊነታቸውን ሳታረጋግጡ ከጽ/ቤታችሁ መታወቂያ ተሰጣቸው በሚል ከአዲስ አድማስ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ መስጠት አልፈልግም” ብለዋል - ዋና ፀሐፊው፡፡
አቶ ጀዋር የዜግነት ጉዳያቸውን አሟልተው ለፓርቲው የሚያቀርቡበት የጊዜ ገደብም አለመቀመጡን ዋና ፀሐፊው ጠቁመው በዚህ ሂደት ውስጥ ፓርቲው ለምርጫ የሚያደርገውን ዝግጅት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ከሕዝብ ጋር የመተዋወቅ እንጂ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ አለመሆኑንም አቶ ጥሩነህ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የፓርቲውን ፖሊሲ፣ አላማና ደንብ ከማስተዋወቅ በዘለለ የምርጫ ቅስቀሳ ውስጥ አልተገባም ያሉት አቶ ጥሩነህ፤ አንዳንድ የምርጫ ቅስቀሳ የሚመስሉ ጉዳዮችም ሆን ተብለው የተደረጉ አይደሉም ብለዋል፡፡  

Read 17948 times