Saturday, 25 January 2020 12:08

“በኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ ላይ ከማንም ጋር አንደራደርም” - ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(22 votes)

    ከደቡብ ክልል ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በክልሉና በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን ውይይት ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ መንግስታቸው በኢትዮጵያ ህልውና ከማንም ጋር እንደማይደራደር አሳሰቡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የኢትዮጵያን የብልጽግና ጊዜ ማቆም የሚችል ሃይል የለም” ብለዋል፡፡
ከሀገሪቱ ሠላም ማጣትና የህልውና ስጋት ጋር በተያያዘ ከተሰብሳቢዎቹ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለሠላም መስፈን ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መንግስታቸውም በሀገሪቱ አንድነትና ህልውና ጉዳይ ላይ ከየትኛውም ሃይል ጋር እንደማይደራደርም አረጋግጠዋል፡፡
“የኢትዮጵያን የብልጽግና ጊዜ ማቆም የሚችል ሃይል ከእንግዲህ የለም” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያን በብልጽግና እንቀይራለን፣ አንዴ ስራ ጀምረናል፣ አንዴ ለውጥ ጀምረናል፣ ወደ ኋላ አንመለስም” ብለዋል፡፡
“የኢትዮጵያን ህልውና በሚመለከት ስጋት አይግባችሁ” በማለት ማንም እንዳይጠራጠር በአጽንኦት የተናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያ ለድርድር የምትቀርብ ሃገር አይደለችም” ብለዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ጥላ ውስጥ መነጋገር መጨዋወት ተፈቅዷል፣ የኢትዮጵያን ህልውና የሚነካ ነገር ሲፈጠር ግን ዛሬም እንደ ትናንቱ ህልውናችንን እናስከብራለን” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡
አክለውም፤ በኢትዮጵያ ህልውና ጉዳይ ላይ ፈጽሞ ድርድር እንደሌለ በማስረገጥ ተናግረዋል::
በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ ያሳሰቡት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ተያይዘን እንዳንጠፋ አንዱ ለአንዱ ምክር እየሰጠ አብረን ለሠላም መቆም አለብን” ብለዋል፡፡
“ሠላም በምኞት ብቻ አይመጣም” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “መስጊድ ሲቃጠል ክርስቲያኑ ለምን ብሎ መጠየቅ አለበት፤ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠል ሙስሊሙ ለምን ብሎ መጠየቅ አለበት፤ ይህ ሲሆን ነው ሠላም የሚመጣው” ብለዋል፡፡  

Read 17367 times