Print this page
Sunday, 26 January 2020 00:00

ለ32ኛው ኦሎምፒያድ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • ከስፖርት ሚዲያው ጋር በስፋት ሊሰራ ነው፡፡
         • የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለዝግጅት 200 ሚሊዮን ብር ይዟል፡፡
         • ከብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ ጋር የገቢ ማሰባሰቢያ፤ የስፖርት ውድድሮች እና የሙዚቃ ኮንሰርት ታስቧል

          በጃፓኗ ከተማ ቶኪዮ የሚካሄደው 32ኛው ኦሎምፒያድ የቀረው ከ6 ወራት ያነሰ ጊዜ ሲሆን የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ‹‹ከቶኪዮ እስከ ቶኪዮ›› በሚል ርእስ ከትናንት በስቲያ ከስፖርት ጋዜጠኞች  ጋር  ልዩ ምክክር አድርጓል፡፡ በዚሁ መድረክ  ላይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ የሚኖራትን ተሳትፎ ስኬታማ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሙሉ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፍቅር ይልቃል ባቀረበው የመነሻ ሃሳብ ከቶኪዮ ኦሎምፒክ ጋር በተያያዘ በህትመት፤ በብሮድካስት፤ በኦንላይንና በሌሎች የመረጃ መረቦች የሚሰሩ የስፖርት ጋዜጠኞች በተለያዩ አቅጣጫዎች ሰፊ ሽፋኖችን መስጠት  እንደሚኖርባቸው አስገንዝቧል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ልዩ የምክክር መድረክ በማዘጋጀት ከስፖርት ሚዲያውን አብረን እንስራ ማለቱን ያደነቁት የስፖርት ሚዲያዎች በ32ኛው ኦሎምፒያድ ኢትዮጵያ የሚኖራትን ተሳትፎ ከኦሎምፒኩ በፊት በኦሎምፒኩ ወቅት እና ከኦሎምፒኩ በኋላ ሰፊ ሽፋን በመስጠት ለመደገፍ ቃል ከመግባታቸው በላይ በየሚዲያ አውታሮቻቸው የሚሰሯቸውን ተግባራት እና እቅዶች ለኦሎምፒክ ኮሚቴው እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ  ከ2  ሳምንት በፊት በአቶ አባዱላ ገመዳ ሰብሳቢነት የሚመራ ብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴ በማቋቋም በስፋት መንቀሳቀሱን የጀመረ ሲሆን፤ በስሩ ያሉት ሶስት ኮሚቴዎች የገቢ ማሰባሰብ፤ የገፅታ ግንባታ እና የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን የሚያከናውኑ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለፁት ለአጠቃላይ ዝግጅት የሚሆን 200 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዟል፡፡ ከብሄራዊ የዝግጅት ኮሚቴው ጋር በሚቀጥሉት ወራት በገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ፤ በስፖርት ውድድሮች እና በሙዚቃ ኮንሰርት በመስራት ከባለድርሻ አካላት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚሰበሰብም ገልፀዋል:: የኦሎምፒክ ኮሚቴው በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ታዋቂ ባለሃብቶች ድጋፍ እየሰጡን ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ከዚያ ባሻገር የመንግስት ልማት ድርጅቶች፤ የክልል መንግስታትና የከተማ መስተዳድሮችን የላቀ አስተዋፅኦ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል:: የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በምክትል ከንቲባው ታከለ ኩማ በኩል የገባውን ቃል ኪዳን የጠቀሱት ዶክተር አሸብር፤ የከተማው መስተዳድር በቶኪዮ ኦሎምፒክ የላቀ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ኦሎምፒያኖች የመሬት ስጦታ እና ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ለመስጠት የሰጠውን ተስፋ ምሳሌ ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
የኦሎምፒክ ኮሚቴው በተለያዩ ስፖርቶች የሚያደርገውን ዝግጅት አስመልክቶ ዶክተር አሸብር ለስፖርት ጋዜጠኞች ሲያብራሩ፤ በቦክስ ስፖርት እና በዎርልድ ቴኳንዶ ለተሳትፎ የሚያስፈልገውን ውጤት ለማስመዝገብ ለስፖርተኞቹ በቂ ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም በሟሟላት በሆቴል ተቀምጠው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በአትሌቲክስ ውድድሮች አትሌቶች በቀረው ሚኒማ የሟሟያ ጊዜ በተለያዩ ውድድሮች እንደሚሳተፉ እናውቃለን ብለው፤ ከኦሎምፒኩ በፊት የተሟላ ዝግጅት እንዲደረግ ሲታሰብ ባንዲራ አንግበው ለሚሰለፉበት መድረክ በጥንቃቄ እና በትኩረት እንዲሰሩ በሚኖራቸው ውጤት ከፍተኛ ሽልማት ምናልባትም ለሜዳልያ ውጤት እስከ 4 ሚሊዮን ብር ሽልማት ለእያንዳንዱ ኦሎምፒያን በነፍስ ወከፍ ለመሸለም ስራዎች እያከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ከቶኪዮ ከባድ ሙቀት ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የማራቶንና የርምጃ ውድድሮችን  ከዋና ከተማዋ በስተሰሜን 800 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ተዛውሮ እንዲሄድ መወሰኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ልዩ ዝግጅት ማድረጉንም ፕሬዝዳንቱ ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ ተናግረዋል፡፡ በማራቶን የሚወዳደሩ አትሌቶችን ከመረጥን በኋላ አስፈላጊውን የመጨረሻ ዝግጅት የምናካሂደው ወደ ቶኪዮ አትሌቶችና አሰልጣኞችን በመላክ የውድድር ስፍራውን በመገምገም ከሚሰሩ ጥናቶች በመነሳት ይሆናል ብለዋል፡፡
በ33 ስፖርቶች በ50 የተለያዩ መርሃ ግብሮች 339 ውድድሮች የሚካሄዱበት ሲሆን፤ 206 አገራትን የወከሉ 11091 ኦሎምፒያኖችን ለሚሳተፉበት ታላቁ የስፖርት መድረክ በኦሎምፒክ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ የሚጠቀሰው 12.6 ቢሊዮን ዶላር ለዝግጅት ወጭ ሆኖበታል::
ከ4 ዓመታት በፊት በብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ ላይ በተከናወነው 31ኛው ኦሎምፒያድ በ3 የስፖርት አይነቶች 35 ኦሎምፒያኖችን ያሳተፈችው ኢትዮጵያ በ1 የወርቅ፤ 2 የብር እና 5 የነሐስ ሜዳልያዎች ማግኘቷ የሚታወስ ሲሆን በዚሁ የሜዳልያ ስብስብ ከ207 አገራት 44ኛ ደረጃ እንዲሁም በአፍሪካ በ3ኛ ደረጃ የተመዘገበ ከፍተኛ ውጤት ማግኘቷ ይታወቃል:: ቶኪዮ ክምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ በፊት በ13 ኦሎምፒያዶች ተሳትፎ ለማድረግ የበቃችው ኢትዮጵያ በኦሎምፒክ መድረክ በአጠቃላይ የሰበሰበቻቸው  ሜዳልያዎች ብዛት 53 የደረሰ ሲሆን 22 የወርቅ፤ 9 የብርና 22 የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡
32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ኢትዮጵያ በሚኖራት ተሳትፎ የምታስመዘግበውን ውጤት አስመልክቶ የተለያዩ ትንበያዎች ኦሎምፒኩ ከመጀሩ አንድ አመት በፊት ጀምሮ በይፋ እየተሰራጩ ቆይተዋል፡፡በግሬስ ኖት ለኢትዮጵያ በተሰራው የሜዳልያ ትንበያ 9 ሜዳልያዎችን 2 የወርቅ፤ 4 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ 31ኛ ደረጃ እንደምታገኝ የተጠቆመ ሲሆን  የቅርብ ተቀናቃኟ ኬንያ 12ኛ ደረጃን በ17 ሜዳልያዎች 8 የወርቅ፤ 3 የብርና 6 የነሐስ ሜዳልያዎች ታገኛለች ተብሏል፡፡ ቤስትስፖርትሰ የተባለ ድረገፅ ከ3 ሳምንት በፊት ባወጣው ትንበያ ደግሞ ኢትዮጵያ 8 ሜዳልያዎችን 3 የወርቅ፤ 1 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን እንደምትሰበስብ የገመተ ሲሆ ኦሎምፒክ ፕሪዲክሽን ድረገፅ ደግሞ ለኢትዮጵያ የተነበየው 10 ሜዳልያዎችን 3 የወርቅ፤ 3 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎችን ነው፡፡

Read 1247 times