Saturday, 25 January 2020 12:21

የሚፈራ መንግሥት በሌለበት የምን ምርጫ?!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

 ከግንቦት 20 ቀን 1983 እስከ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የቆየው የሕወኃት ኢሕአዴግ መንግሥት፤ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ የሚል ደልቃቃ ነበር፡፡ አዲስ አበባ እንደ ገባ ሕግና ደንብ የሚባል ነገር የማያውቁት ወታደሮች (ተጋዳላይ)፤ ሲሰርቅ የሚያገኙትን ሰው ፖሊስ ጣቢያ ወስደው፣ ምርመራ አድርገው፣ ለሕግ ከማቅረብ ይልቅ የሚቀጡት ግንባሩን ወይም ደረቱን በጥይት በማለት ነበር፡፡
ሥልጣን የማደላደል ተግባሩን በአስደንጋጭ እርምጃ የጀመረው ሕወኃት/ኢሕአዴግ፤ የቀጠለው በሚያነሷቸው ሀሳቦችና ባላቸው ተሰሚነት ይፈታተኑኛል ያላቸውን ሰዎች እየለቀመ በጠራራ ፀሐይ በመግደል ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ዋና ፀሐፊ የአቶ አሰፋ ማሩና የመስታዋት መጽሔት አዘጋጅና ባለቤት የነበረው የሕግ ሙያተኛው የአቶ ተስፋዬ ታደሰ አሟሟት ለዚህ ተግባር ጥሩ ማስረጃ ናቸው፡፡
በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍንና ሕዝብ የመንግሥት ሥልጣን ባለቤት እንዲሆን ለማብቃት የተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ፣ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከማድረጉ በተጨማሪ አባሎቻቸውን በልዩ ልዩ ምክንያት በማሰርና በማሳደድ፣ ፓርቲዎች በገዛ ገንዘባቸው ቤት ተከራይተው ቢሮ እንዳይከፍቱ አከራዮችን በማስፈራራት እንዳይንቀሳቀሱ አድርጎ መቆየቱን ሕወኃት ኢሕአዴግ የሚዘነጋው እንዳልሆነ አምናለሁ፡፡
በገጠር የመንግሥት ኮሚቴና በከተማ፣ የከተማ ነዋሪዎች ፎረም፣ የእድሮች ፎረም፣ የወጣቶችና የሴቶች ፎረም ወዘተ… የሚባሉ የብዙኃን አደረጃጀቶች በመዘርጋት፣ አመራሩን በድርጅት አባላትና ታማኞች በማስያዝ፣ የሌሎች ኃይሎችን የመንቀሳቀሻ ሜዳ በማጥበብ፣ ሕወኃት ኢሕአዴግ ይበልጥ የሚፈራ መንግሥት እየሆነ ሄደ፡፡ ከ1997 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ በኋላ ደግሞ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ብቻ ሳይሆን ሕጎችም የእሱን ጥቅም እንዲያስከብሩና ገደብ የለሽ ጥበቃም እንዲያደርጉ እየታሰበ ይታወጁም ይተገበሩም ጀመር፡፡  ይህ ብቻ አይደለም፤ ከዚህ በኋላ እና ከዚህም ቀደም ብሎ መንግሥት፣ የፍትሕ ተቋማትን ይሁነኝ ብሎ የማጥቂያ መሣሪያ ሲያደርጋቸው ቆይቷል፡፡ በፈጠራ ክስና በተዘጋጁ የሐሰት ምሥክሮች ለእሥራትና ለእንግልት አልፎም ለአካል መጉደል ብዙዎች ተዳርገዋል፡፡ ይኸ ደግሞ በቀላሉ በማይጠገን ደረጃ የአገሪቱን የፍትሕ ሥርዓት ታማኝነትን እንዲያጣ አድርጓል፡፡
የሕወኃት/ኢሕአዴግ መንግሥት፣ በልዩ ልዩ መንገድ ጉዳት ያደረሰበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፍና በደሉን መሸከም ከማይችልበት ደረጃ በመድረሱ፣ በ2008 ዓ.ም መገባደጃ ጀምሮ በየቦታው ተቃውሞና አመጽ ተቀሰቀሰ፡፡ ሕዝብ ተቃውሞውን ለመግለጽ በግልና በመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተና ጥቃት ፈፀሙ፡፡ ፋብሪካዎች ወደሙ፣ መኪናዎች ተቃጠሉ፡፡ መንግሥት 70 ሺህ በላይ ሰዎችን እንደ በአዋሽ አርባ፣ ጦላይ ወዘተ… ቢባሉ በፊት የወታደር ማሰልጠኛዎች በነበሩ ቦታዎች ወስዶ ቢያጉርም፣ 1500 ሰዎችን ለፍርድ ቢያቀርብም፣ ከዚህም አልፎ ተደጋጋሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያወጅም፣ ሕዝቡን ከአመፁ የሚገታ አልሆነም፡፡ ግፊቱን መቋቋም ያቃታቸው አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ሥልጣናቸውን መልቀቅ እንደሚፈልጉ ይፋ አደረጉ፡፡  እሳቸውን በመተካትም ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አሊ የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ቀጥለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ፡፡
“ኢሕአዴግ በፈፀመው ስህተት በተፈጠሩ አዳዲስ ለውጦችና ፍላጐቶች ምክንያት አሳሳቢና ወቅታዊ ችግሮች ተፈጥረዋል” ያሉት የኢሕአዴግ ሊቀ መንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ በሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ አደረጉ፡ ተለይተው “እነሱማ አይፈቱም” ተብለው የተደመደመባቸውንና ጥርስ የተነከሰባቸውን ሰዎች ጭምር ሥልጣናቸውን መደራደሪያ አድርገው እስከ ማስለቀቅ ሄዱ፡፡ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት የጀመረው ዘር - ተኮር ማፈናቀል የቀጠለ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ሁኔታው እየቀነሰ የተፈናቀሉትም ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ ነው፡፡ ይህ መልካም እርምጃ ነው፡፡  ይሁን እንጂ እንዲህ ባለው ሁኔታ ውስጥ ደግሞ የሰሚን ልብ የሚያደሙ፣ በቅርብ ሆኖ ላያቸው የሚዘገንኑ ወንጀሎች በአገሪቱ እየተፈፀሙ መጡ፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግድያና እንዲሁም በየ አካባቢው የሚፈጠሩ ግጭቶችና እያስከተሉት ያለው አለመረጋጋት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ተዘግቶ የቆየ ቤት ሲከፈት የሚፈጥረው ጥሩ ያልሆነ ሽታ ነው” በማለት ጊዜያዊ ችግር አድርገው ቢያዩትም፣ አንዳንዱ ወንጀል እራሱን ወደ ልማድ እየለወጠ መጥቷል፡፡
አንድ ወይም ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች፤ አንድ ወይም ሁለት መስጊዶች ሲቃጠሉ ዝም ተብለው የታለፉ ወንጀለኞች፤ በደርዘን የሚቆጠሩ ቤተክርስቲያኖችን ከሃያ ሰባት ያላነሱ  መስጊዶችን እስከ ማቃጠል ደፈሩ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ወንጀል የየአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዳሉበት ተደጋግሞ ቢገለጽም፣ ፍርድ ቤት የቀረበ የተቀጣ ሰው ስለመኖሩ የተሰማ ነገር ግን የለም፡፡ የሞጣ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያንን ለማቃጠል የተደረገው መከራና የተከተለው የሶስት መስጊዶች መቃጠል፣ ይህ ቸልታ ያመጣው ውጤት መሆኑን በግልጽ መናገር ይገባል፡፡ እየተመረጡ የተቃጠሉና የተዘረፉ የንግድ ተቋማትም ጉዳይ ተቃሎ መታየት የለበትም፡፡
ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም የሲዳማ ክልልነት መታወጅ አለበት ብለው የተነሱ ቡድኖች በሐዋሳና ከሐዋሳ ውጪም በአለታ ወንዶ፣ በአገረ ሰላም፣ በይርጋለምና በአፓስቶ ከ100 በላይ የንግድ ሱቆችና መኖሪያ ቤቶችን እንደሚወድሙ አድርገዋል፡፡ ሲዳማ ባልሆኑት ላይ ያነጣጠረው በዚህ ጥቃት የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ቢገለጥም፣ የተጠየቀ መኖሩን ግን አላውቅም፡፡ ቡራዩ ላይ ጥቃት የተፈፀመባቸው ሰዎች ጉዳይም ቢሆን በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ያለ ጉዳይ ነው፡፡       
በቅርቡ የተፈፀሙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እገታና በአማራ ክልል ወላጆቻቸው ገንዘብ ካልሰጡ ተብለው የተገደሉ ሕፃናት ጉዳይ ስናይ መንግሥት ሕግ ያስከብራል፣ ወንጀለኛን ተከታትሎ ይዞ ለፍርድ ያቀርባል የሚል እምነትን እየሸረሸረ መምጣቱ ሳያንስ፣ ጥፋት ፈፃሚዎቹም የወንጀል ድርጊታቸውን ወደ ከፋ ሁኔታ እያሸጋገሩት መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
ጨከን ብሎ ሕግ ማስከበር ባለመቻሉ የተደፈረውና እየተደፈረ ያለው መንግሥት፤ መጪውን አገር አቀፍ ምርጫ እንዴት አድርጐ ማካሄድ ይችላል? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡
አንድ ጊዜ ባሕርዳር ላይ ኢዜማ ስብሰባ ይጠራል፡፡ ፊታቸውን የሸፈኑና መሣሪያ የያዙ ሰዎች ‹‹በዚህ የሚያልፍ ስንት ሱሪ የታጠቀ ነው›› ብለው መንገዱን ይዘጉታል፡፡ አቤት ቢባልም… የሚደርስ አልነበረም፡፡ እንዲህ አይነቱ የጉልበተኞች እርምጃ ላለመደገሙ ማን እርግጠኛ ይሆናል?
ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ፣ ለማሸነፍ ደግሞ በራሪ ወረቀቶች ማሰራጨት ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ በነፃነት አላማን ማስተዋወቅና ማስረዳት፣ መቀስቀስ ይጠይቃል፡፡ ከእያንዳንዱ እጩ አልፎም እያንዳንዱ ፓርቲ ይህን ያደርግ ዘንድ ምን ያህል ከሥጋት ነፃ ነው? ምን ያህልስ የመንግሥት ጥበቃ ይደረግለታል? ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡
ከሁሉም ከሁሉም በፊት ከራሱ መንግሥት የሚፈራና የሚከበር መሆን አለበት፡፡ ከዚያ አገር ወደ ምርጫ መግባት ትችላለች፡፡
አበው “የዳኛ ልል በጥፊ ያወላወል” እንዳሉት እንዳይሆን!!   

Read 1707 times