Saturday, 25 January 2020 12:39

የቻይናው የ“ኮሮናቫይረስ” ወረርሽኝ ዓለማቀፍ ስጋት ፈጥሯል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በቅርቡ በቻይናዋ ዉሃን ግዛት የተቀሰቀሰውና ከ17 በላይ ቻይናውያንን ለህልፈተ ህይወት በመዳረግ ወደ ሌሎች ግዛቶችና አገራት በፍጥነት በመዛመት ላይ የሚገኘው “ኮሮናቫይረስ” የተሰኘው አዲስ የቫይረስ ወረርሽኝ  ዓለማቀፍ ስጋት መፍጠሩ እየተነገረ ነው፡፡
በቻይና የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከ633 በላይ ሰዎችን እንዳጠቃ የተነገረለት “ኮሮናቫይረስ”፤ ድንበር አልፎ ወደ አሜሪካ፣ ታይላንድ፣ ታይዋን፣ ጃፓንና ደቡብ ኮርያ መዛመቱን የዘገበው ቢቢሲ፣ የቻይና መንግስት የመተንፈሻ አካላትን በማጥቃት ለሞት የሚዳርገውን ይህን ተላላፊ ቫይረስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡ እስካለፈው ሃሙስ ድረስ 95 ያህል በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች በጽኑ መታመማቸው በተነገረባት ቻይና፤ ውሃንን ጨምሮ ቫይረሱ ከተስፋፋባቸውና 20 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ከሚኖርባቸው ሶስት ግዛቶች መንገደኞች እንዳይወጡና ቫይረሱን እንዳያሰራጩ ለማድረግ ሲባል ሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎቶች ባለፈው ሃሙስ ዝግ የተደረጉ ሲሆን በሌሎች ግዛቶች የሚንቀሳቀሱ ዜጎችም ጥብቅ የጤና ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝና የአዲስ አመት በዓልን ጨምሮ ሌሎች ዝግጅቶች እንዲሰረዙ መወሰኑም ተነግሯል፡፡
እስካለፈው ሃሙስ ድረስ በታይላንድ አራት፣ በደቡብ ኮርያ አንድ፣ በጃፓን አንድ፣ በታይዋን አንድ እንዲሁም በአሜሪካ አንድ ሰው ማጥቃቱን የዘገበው ቢቢሲ፤ አውስትራሊያ፣ ሲንጋፖር፣ ሆንግኮንግ፣ ሩስያንና ጃፓንን ጨምሮ ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ የተረጋገጠው ይህ አደገኛ ቫይረስ ያሰጋቸው በርካታ አገራትም ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየመረመሩ ወደ ግዛቶቻቸው በማስገባት ላይ እንደሚገኙም ገልጧል፡፡
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጋና፣ ዚምባቡዌና ግብጽን ጨምሮ ቻይናውያን ለንግድና ለቱሪዝም በብዛት የሚመጡባቸው የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከቻይና የሚመጡ መንገደኞችን በአውሮፕላን ጣቢያዎች ባቋቋሟቸው የምርመራ ማዕከላት እየመረመሩ ማስገባት መጀመራቸውንም ዴይሊሜይል ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡  
የቻይና መንግስት ባለፈው የፈረንጆች አመት የመጨረሻ ዕለት፣ ከአለም የጤና ድርጅት ጋር በጋራ በሰጠው የማስጠንቀቂያ መግለጫ፣ ቫይረሱ መቀስቀሱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከአስር ቀናት በኋላ በቫይረሱ የተያዘው የመጀመሪያው ሰው መሞቱንና በቀጣይ ሳምንታትም በስፋት በመሰራጨት በርካቶችን ማጥቃቱንም አክሎ ገልጧል፡፡

Read 5374 times