Saturday, 25 January 2020 13:10

ጥላሁን ገሠሠና አትሌቲክስ፤

Written by  ጌጡ ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

       በ2000ዓ.ም. (በእሥራ ምዕቱ) በክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ መኖሪያ ቤት ‹‹67ኛ›› በዓለ ልደቱ ተከበረ፡፡ የሙዚቃው ንጉሥ ልደት በቤቱ የተከበረበት ምክንያት ቁጭት የወለደው ነበር:: የኢትዮጵያ ሜሌኒየም ምክንያት በማድረግ በሚሌኒየም አዳራሽ ከሱዳን የመጡ ታዋቂ ሙዚቀኞች‹‹ጥላሁን ገሠሠ የታለ!?›› ሲሉ አዘጋጆቹን ጠየቀ፡፡ አስደንጋጭ ጥያቄ ነበር፡፡ በሚያሳዝንና በሚያፍር መልኩ ጥላሁን በክብረ በዓሉ ላይ አልተጋበዘም፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ለአገርና ለህዝብ የሠሩ ጀግኖች በህይወት እያሉ የክብርና የምስጋና ዝግጅት ተደርጎላቸው አላየሁም፤ በሙያዬም እንዲህ አይነቱን ኹነት ዘግቤ አላውቅም፡፡ ጋሽ ጥላሁን ልደቱን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ፕሮግራም አልጠበቀም፡፡ እንባ አውጥቶ አለቀሰ:: ስሜተ-ስሱው ከያኒ እምባ አውጥቶ አለቀሰ፡፡ እገኛም በደስታ አነባን፡፡
በዓለ ልደቱ በቤቱ ያዘጋጁት፤ ታምራት ሀይሉ (የቁምነገር መጽሔት ባለቤትና ማኔጂንግ ኤዲተር) እና ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ (ጋዜጠኛና ደራሲ) ናቸው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ የሙዚቃ ንጉሥ›› በሚል ርዕስ ግለ ታሪኩን በመጽሐፍ ለመሥራት የጠነሰሱት እነርሱ ነበር፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር በግል ህይወቱ ላይ ያተኮረው መጻሕፉን አሳትሞታል፡፡
የዝግጅቱ የመድረክ አጋፋሪ (Master of ceremony) እንዲሉ እኔ ነበርኩ፡፡ የዕለቱ ታዳሚ ስለ ጋሽ ጥላሁን የሚያውቀውንና የሚሰማውን ይናገር ዘንድ ዕድል መስጠት ጀመርኩ፡፡
ከአንጋፋዎቹ እስከ ወጣቱ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ድረስ አድናቆታቸውን አዘነቡ፡፡ ድምፃዊውን አወደሱት፤ አሞገሱት፡፡
ጋሽ፣ ጥላሁን በደስታ ረሰረሰ፡፡
እኔም ተራዬ ደረሰ፡፡ ጋሽ ጥላሁን ፊት ቆሜ ዓይን ዓይኑን እያየሁ፣ የማውቀውን ማውጋት ጀመርኩ፡፡ የወጌ ርዕስ ‹‹ጥላሁን ገሠሠና ስፖርት›› የሚል ነበር፡፡
ጳጉሜ 5 ቀን 1952 ዓ.ም. የሮም ኦሎምፒክ በጣሊያን ሀገር ተካሄደ፡፡ አትሌት አበበ ቢቂላ ሮጦ ያሸነፈበት ቬና አደባባይ፣ ሞሶሎኒ ሁለት እጆቹን እያወናጨፈ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት መዳፍ ውስጥ ለማስገባት ወታደራዊ ትዕዛዙን ያሰማበት ሥፍራ ነበር፡፡ የክቡር ዘበኛው አሥር አለቃ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ አሸነፈ፡፡
ከድሉ በኋላ የኢጣሊያ ጋዜጦች ‹‹ሮም በአንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር ተወረረች›› የሚል ርዕስ ዜና ይዘው ወጡ፡፡
አበበ ቢቂላ ከሮም ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ::
‹‹እቱ ይሻልሻል፤ ይሻልሻል፣
እቱ ይሻልሻል፤ ይሻልሻል፣
አበበ ቢቂላ ያገባሻል፣
     ጥላሁን ገሠሠ ይድርሻል … ››
የሚል የሕዝብ ዜማና ግጥም በአዲስ አበባ ከተማ ተደመጠ፡፡ ምናልባትም ቀስ እያለ በመላ ኢትዮጵያ ሳይዳረስ አልቀረም፡፡
***
መስከረም 15 ቀን 1993 ዓ.ም. በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ትንሿ አዳራሽ የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች ተሰብስበዋል፡፡ በድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ የሙዚቃ ህይወት ላይ ሲምፖዚየም፣ በአውስትራሊያ ደግሞ የሲድኒ ኦሎምፒክ እየተካሄደ ነበር፡፡
ከውድድሩ በፊት አትሌት ኃይሌ በተረከዝ ህመም ምክንያት ልምምዱን አቋርጦ ነበር:: ይሁን እንጂ ሻለቃ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ኬንያዊ ተፎካካሪውን ፖል ቴርጋትን በአስደማሚ የአጨራረስ ብቃት አሸነፈው፡፡ ጀግናው አትሌት እንዳለመደው የድል ታሪኩን በወርቃማ ብዕሩ ከተበ፡፡
የኃይሌ ድል ከትንሿ አዳራሽ ጀርባ በጩኸት ተስተጋባ፡፡ ጭብጨባና እልልታው ቀለጠ፡፡ የሲምፖዚየሙ ታዳሚዎች የድሉና የደስታው ተካፋይ ለመሆን ቅንጣት አልፈጀብንም፡፡
ጋሼ ጥላሁን ‹‹ምንድነው?›› ሲል ጠየቀ፡፡ በአዳራሹ የሲዲኒው ድል ተበሰረ፡፡
‹‹ኃይሌ ገ/ሥላሴ የአትላንታውን ድል በሲድኒ ደገመው›› ተባለ፡፡ ተጨበጨበ፡፡ (ለኃይሌ ክብር በአዳራሹ ቆመን ለጀግንነቱ አጨበጨብን)
የሲድኒው ኦሎምፒክ የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ ፉክክር የተደረገው በቴርጋትና በኃይሌ መካከል ብቻ አልነበረም:: በኬንያና በኢትዮጵያ ተመልካቾች መካከልም ነበር::  ... የመጨረሻዎቹ 200 ሜትሮች ላይ ቴርጋት ተስፈንጥሮ ወጣ፡፡ ኃይሌ እየተምዘገዘገ ተከተለው፡፡ ፖል ቴርጋት የድል ጠርዝ ላይ ደረሰ፡፡ ይሁንና ኃይሌ ጥርሱን ነክሶ 27፡18፡21 በሆነ ሰዓት ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቀቀ፡፡ በ0.09 ማይክሮ ሰከንድ ብልጫ ፖል ቴርጋትን ዳግም በኦሎምፒክ አደባባይ አሸነፈው፡፡ ይህ የድል ዜና ዛሬም ለኔ አዲስ ነው፡፡ ትውስታው አይደበዝዝም፡፡
ጋሼ - ጥላሁን በአዳራሹ ለተሰበሰበው ታዳሚ ‹‹ለኃይሌ ገ/ሥላሴ ቆዳዬ ተገፎ ይሠራለት ጫማ›› ሲል አድናቆቱን ገለፀ፡፡ በአዳራሹ የነበረው ሰው ለንግግሩ፤ ለኃይሌም ክብር ከመቀመጫው ተነስቶ አጨበጨበ፡፡
የጦቢያ ሙያተኞች እንኳንስ እርስ በእርስ ለመደናነቅና ለመከባበር ለእግዜር ሰላምታም እምብዛም አልታደሉም፡፡ በትንሿ የሀገር ፍቅር አዳራሽ ባስተዋልኩት የአድናቆት ትዕይንት በእጅጉ ተገረምኩ፡፡
መስከረም 26 ቀን የሲድኒ ኦሎምፒክ ጀግኖች የክብር አቀባበል በመስቀል አደባባይ ተደረገላቸው፡፡
ለዓለማችን ብርቅዬ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ጥያቄ ቀረበለት፡፡
‹‹ጥላሁን ገሠሠ ‹ቆዳዬ ተገፎ ይሠራለት ጫማ› ሲል አድንቆሃል፡፡ ምን አስተያየት ይኖርሃል?›› …
ጀግናው አትሌትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ‹‹ለጥላሁን ገሠሠ ዘፈን ሰው ይሞታል ቢባል የመጀመሪያው ሟች እኔ ነኝ››፡፡
‹በኢትዮጵያ ምድር ጀግንነትና ክብር ለዘላለም ይኑር!› አልኩና ወጌን ቋጨሁ፡፡
ነፍሱን ይማረውና! ጋሼ፤ ጥላ-ሁን ገሠሠ ጠርቶ ግንባሬን ሳመኝ፡፡ በደስታ ተፍነከነኩ፡፡ ይህንን ታሪክ ሚዲያ እየተቀባበለ አስተጋባው፡፡
… ጥላ ከለላዬ፤ ኢትዮጵያ አገሬ …
***
አበሻ ምን ነካው ዛሬ?!
ነቢይ መኮንን
ዛሬን ብቻ አበሻ በሆንኩ
የአበሻ ልጅ ነቅሎ ወጥቶ፣
ባንድ አዳራሽ ተሰብስቦ
የአንድ ድምጽ ልደት ያክብር፣ የረሳውን
ኮከብ ከቦ?!
ያለ ባህሉ? ያለ አመሉ?
አበሻ ምን ነካው በሉ?
ምን ምልኪ ነው በበለስ፣ ከቶ አለ ውሉ መዋሉ፡፡
ኧረ አበሻ እንዲህ አያውቅም፣ ዛሬ ነው የተወለደ
ያገር ኮከብ ያከበረ
ከ60 ዓመት ዋርካ ጥላ፣
ከአድባር ዛፍ ሥር የዘመረ
ክታብ መቁጠር የጀመረ፡፡
በበለስ ዛሬ ነው ኧረ!
ዛሬን ብቻ አበሻ በሆንኩ፡፡
ወዲያ ከወደ ወሊሶ
አንድ አራስ ድምፅ ተፀንሶ
እናት ልጅ ወለድኩ ብላ
አንቀልባ ሙሉ ድምፅ አዝላ
ልቅሶ መስሏት ስታባብል
በዝማሬው ስትማልል
ጥላሁን ብላ ብታዝለው፣ እሱ ፀሐይ ሆኗል
ነግሦ
ከአድማሳት በላይ ነፍሶ
የሳቁን የዕንባውን አምባ፣ የዘመናት ግድብ
ጥሶ
አንድ አገር ሙሉ ልደት፣
በአንድ ቀን አብራክ ደግሶ
የህዝቦች ኮንሰርት አወጀ፣ ስልሳ ጧፍ ባፉ
ለኩሶ!!
(በቅርቡ ለንባብ ከሚበቃው የጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን “የጉዞ ማስታወሻ” መጽሐፍ ላይ የተወሰደ)


Read 1818 times