Monday, 03 February 2020 11:28

‹‹እናት ፓርቲ›› ምርጫው እንዲራዘም ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


               እናት በልጆቿ መካከል ልዩነት እንደማታደርግ ሁሉ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንደ እናት የማገልገል አላማ አለኝ የሚለው አዲሱ ‹‹እናት ፓርቲ›› ከሰሞኑ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና አግኝቷል፡፡
ፓርቲው በዋናነት የኢትዮጵያን ባህል ወግና ልማድ መነሻ በማድረግ፣ አላማና ግቡን ቀርፆ መመስረቱን የገለፀ ሲሆን ዋነኛ አላማዬ በኢትዮጵያውያን መካከል አንድነትና መግባባትን ማምጣት ይሆናል ብሏል፡፡
የሕዝቡ የአብሮነት እሴት የሚጠብቀውና የሚጠነክረው ማህበራዊ እሴቶቻችን ሲጠበቁ ነው የሚለው ፓርቲው፤ ‹‹እኛና እነርሱ›› የሚል አስተሳሰብን ያስወገደና ‹‹ሁላችንም የአንዲት ኢትዮጵያ የአንዲት እናት ልጆች ነን›› ብሎ እንደሚያምን ጠቁሞ፣ አሁን ያለው የፌደራሊዝም አወቃቀር እንደገና እንዲከለስ የማድረግ አላማ እንዳለው ጠቁሟል፡፡
‹‹በፌደራላዊ ሥርዓት አምናለሁ፤ ይሁን እንጂ ሥርዓቱ መመስረት ያለበት በፖለቲከኞች ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ከምሁራን፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከመላው ሕዝቡ ጋር በሚደረግ ምክክር ነው›› ብሏል - እናት ፓርቲ፡፡
በአጠቃላይ ፓርቲው የቆየውን የኢትዮጵያውያንን የመከባበር፣ የመተሳሰብና ነውር ተግባራትን የመፀየፍ ባህልና እሴት ለመመለስ የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍ እንደሚታገል አስታውቋል ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ጊዜ የተቃወመው ፓርቲው፤ ምርጫው መራዘም አለበት ብሏል፡፡
በደንቢ ዶሎ በተማሪዎች ላይ የተፈፀመውን እገታ በማውገዝ፤ መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርጊቱን በጋራ እንዲያወግዝ ጠይቋል፡፡

Read 9974 times