Monday, 03 February 2020 11:29

መንግስት የታገቱ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ በጥንቃቄ እየሠራሁ ነው ብሏል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)


                     በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ ስለታገቱ ተማሪዎች መንግስት በሰጠው መግለጫ ‹‹ተማሪዎችን ለማስለቀቅ በጥንቃቄ እየሠራሁ ነው›› ያለ ሲሆን የእገታ ድርጊቱን የሚያወግዝ ሠላማዊ ሠልፎች ከማክሰኞ ጥር 19 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክለል የተለያዩ ከተሞች እየካሄዱ የሰነበቱ ሲሆን በዛሬው እለትም በአዲስ አበባ እና በደሴ ከተሞች ሠልፎች ይካሄዳሉ ተብሏል፡፡
በተማሪዎቹ ላይ እገታ የተፈፀመው ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርስቲ በጋምቤላ አድርገው አዲስ አበባ ለመግባት በማይጠበቅ አቅጣጫ ሲጓዙ ነው ያለው መንግስት አንፋሎ ወረዳ ሱዲ በሚባል ቀበሌ ሲደርሱ ህዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም በሽፍቶች እንደታገቱ የፌደራል ፖሊስ፣ ጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት የተሰጠው መግለጫ ያመለክታል፡፡
12 የደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ 19 ሰዎች በአሁኑ ወቅት በአጋቾቹ እጅ እንደሚገኙ ያረጋገጠው መንግስት ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ሶስት የምርመራ ኮሚቴዎችን አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የታገቱ ተማሪዎች ያሉበትን ቦታ በተመለከተም ፖሊስ መረጃ እንዳለውና ቦታው ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑንም መንግስት አስታውቋል፡፡
የታገቱ ተማሪዎች ወላጆችም ከጠ/ሚሩ እና ከምክትላቸው ጋር መንግስት ልጆቻቸውን ለማስለቀቅ እያደረገ ባለው ጥረት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 8 መቶ ያህል የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው እንደሚገኙም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
ከተማሪዎቹ መታገት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አካላት ድምፃቸውን እያሰሙ ሲሆን “አብሮነት” የተሰኘውና በኢዴፓን ኢሃን እና ህብር ኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች የተመሰረተው ትብብር፣ እናት ፓርቲ፣ መኢአድ በበኩላቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን በእኩል እንዲያወግዙና በጉዳዩ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዲይዙ ጠይቀዋል፡፡
ድርጊቱን በመቃወም ከማክሰኞ ጥር 19 ቀን ጀምሮ በባህርዳር፣ ደብረ ማርቆስ ጨምሮ በበርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ሠላማዊ ሠልፎች የተካሄዱ ሲሆን በሠላማዊ ሰልፎቹ መንግስት ተማሪዎቹን እንዲያስመልስና ለድርጊቱ ኃላፊነት እንዲወስድ ተጠይቋል፡፡


Read 8987 times