Monday, 03 February 2020 11:31

መንግሥት በየትኛውም ወገን የሚፈፀም ሥርዓት አልበኝነትን እንዲያስቆም ኢዜማ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)


              መንግሥት በየትኛውም ወገን የሚፈፀምን ሥርዓት አልበኝነትና የሕግ ጥሰት በእኩል ዓይን ተመልክቶ  በአገሪቱ ሕግና ሥርዓት የማስከበር ሃላፊነቱን እንዲወጣ ኢዜማ ጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ትናንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫው፤ ‹‹በየትኛውም ወገን የሚፈፀም ሥርዓት አልበኝነትን በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው›› ብሏል፡፡
‹‹የዴሞክራሲ ሥርዓትን ማዋለድ ከባድ ምጥ እንዳለውና የጭንቅ ጊዜ ማሳለፍ የግድ መሆኑን እገነዘባለሁ›› ያለው ኢዜማ፤ ሆኖም ይሄን ወቅት ተጠቅመው ግርግር በመፍጠር፣ የራሳቸውን ፍላጎት በሃይል ለመጫን የሚፍጨረጨሩ ቡድኖችና ግለሰቦች በየቦታው ብቅ እያሉ ነው ብሏል፡፡
ከዚህ አንፃርም፤ በየትኛውም የአገሪቱ ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችም ሆኑ ግለሰቦች የአገሪቱን ሕጎችና የተቀበለቻቸውን አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አክብረው እንዲንቀሳቀሱና ከሕግ በታች መሆናቸውን እንዲረዱ የማድረግ ሕጋዊ ኃላፊነቱንና ግዴታውን መንግሥት እንዲወጣ ኢዜማ ጠይቋል፡፡
መንግሥት ሕግ የማስከበር ግዴታውን የማይወጣ ከሆነ፣ ማንም እየተነሳ የፈለገውን አድርጎ ‹‹አልጠየቅም›› የሚል ማናለብኝነት ከሰፈነ መቼውንም ማቆሚያ ወደሌለው ሁከትም ልንገባ እንችላለን ሲል አስጠንቅቋል - ፓርቲው፡፡
በአሁኑ ወቅት የሃይማኖትና የአገርን ሰንደቅ ዓላማ ክብር በማዋረድ ከፍተኛ የአገር ክህደት እየተፈፀመ ነው ያለው ኢዜማ፤ ለዚህም መንግሥት ተገቢውን የሕግ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል፡፡ የታገቱ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም እንዲለቀቁ መንግሥት ሃላፊነት ወስዶ ጥረት እንዲያደርግና አጥፊዎችን ለሕግ እንዲያቀርብ፣ ስለ እገታውና ታጋቾቹ ስላሉበት ሁኔታም የጠራና ተገቢ መረጃ እንዲሰጥም አሳስቧል፡፡
ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ችግሮችና ጥምቀት ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዳይከበር ያደረጉ እንዲሁም በሞጣ መስጊድ ያቃጠሉ አካላት በሚገባ ተጣርተው ለሕግ እንዲቀርቡም ኢዜማ በመግለጫው ጠይቋል፡፡     

Read 9893 times