Monday, 03 February 2020 11:26

በጫጫታና በሁካታ የፈረሰች አገር ብትኖር፣ የመጽሐፍ ቅዱሷ እያሪኮ ብቻ ናት!

Written by 
Rate this item
(9 votes)


              ከዕለታት አንድ ቀን እጅግ ባለፀጋ የሆኑ ባልና ሚስት ነበሩ፡፡ ከጊዜ በኋላ የወለዷት አንዲት ቆንጆ ልጅ ነበረቻቸው፡፡ ይህችን ቆንጆ ልጃቸውን ላግባ ብሎ የማይጠይቅ፣ በውበቷ የማይማረክ ጎበዝ የለም፡፡ ቤተሰቧ ግን አንድም ዕድሜዋን፣ አንድም ብስለቷን በማመዛዘን፣ ገና ለጋ መሆኗን በማሰብ፣ ላግባ ብሎ የጠየቀውን ወንድ ሁሉ ይመልሱ ነበር፡፡
ልጅቱ ቀስ በቀስ አካሏም ዕድሜዋም በስሎ ለትዳር በደረሰች ጊዜ፣ ከአንድ ወጣት ጋር በፍቅር ወደቀች፡፡ ቤተሰቧም ለአካለ ሄዋን የደረሰች ልጅ ቤት ውስጥ ዘግቶ ማስቀመጥ ዋጋ እንደሌለው በማገናዘብ፣ ለሰርጓ መዘጋጀት እንደሚሻል አስተውለው፣ ልጃቸውን ያፈቀረውን ወጣት ተቀብለው፣ የሰርግ ድግሱን ማጧጧፉን ተያያዙ፡፡
ሰርጉ ድል ያለ ሆነ፡፡ በርካታ ሰው ተጠርቶ፣ እጅግ የሞቀና የደመቀ ሰርግ ሆነ፡፡ ሙሽሪት ወደ ባሏ ቤት አመራች፡፡ ውሎ አድሮም ወደ እናት አባቷ ዘንድ ልትጠይቃቸው መጣች፡፡ እናቷ በእናት ወግ አንዳንድ ጥያቄ ይጠይቋት ጀመር፡-
‹‹እኔ እምልሽ የእኔ ልጅ…››
‹‹እመት እማማ››
‹‹ሠርግሽ ከተደገሰ ዓመት ሊያልፈው ነው፡፡ የዛሬ ልጅኮ አሳብ የለሽ ነው፡፡ ለመሆኑ ቀንሽን ታውቂዋለሽ ወይ? መቼም ድሮ ነብሰ ጡር ለመሆንሽ ጥርጥር የለውም፡፡ ዋናው ነገር ግን ቀንሽን ማወቅሽ ላይ ነው። ለመሆኑ በትክክል ቀንሽን አውቀሽዋል? የገንፎ እህልም ምንም አሟልተን ጎረቤት ማብላት አለብን፡፡ እግር የጣለው እንግዳም ቢመጣ ዝም አይባልም፡፡ ይሄን ነገር አስበሽበታል?››
ልጅቱም እንደ መሽኮርመም ብላ ዝም አለች፡፡
እናት፤
‹‹ንገሪኝ እንጂ፡፡ ኋላ ውርደት ላይ እንዳትጥይን፡፡ በትክክል የፀነስሽበትን ጊዜ ታስታውሻለሽ?››
ልጅቱም፤
‹‹እማዬ፤ እኔ ምኑን አውቀዋለሁ፡፡ እሱ እንደሆነ በየቀኑ ይጨምርበታል!››
* * *
በላይ በላዩ የሚጨመር ‹‹ጥፋት›› ለማረም ያስቸግራል፡፡ አጥፊውንና ጥፋቱን እያየ እጁን አጣጥፎ የተመለከተ፣ ሁለቱም ጥፋተኞች ናቸው፡፡ ጥፋት  ነው ብሎ ማናቸውንም ድርጊት በጊዜ ያልተገነዘበና ድርጊቱንም ያልገታ፣ ከአጥፊው እኩል ጥፋተኛ ነው፡፡ እንድም የጥፋቱን ልኬት በአግባቡ ያላጤነ፣ ያላውጠነጠነና ልብ ማለት ያልቻለ፣ እኩይ ጥፋት እንደፈፀመ ይቆጠራል፡፡ ምክንያቱም ሂደቱ ለበለጠ ጉድለት ይዳርገዋልና ነው፡፡  
እውነትን ፍለጋ በቆፈርነው ምድር
እህል ዘራንበት በልተን እንድናድር
ከሁሉም ችግራችን የኢኮኖሚ ችግራችን ቀዳሚውና ዋናው ነው፡፡ የኢኮኖሚ ችግራችን አጠቃላይ ገጽታ ፖለቲካ የምንለው ነው ‹‹The Concentrated form of Economics is Politics›› እንዲሉ፡፡ በየትኛውም ሥርዓት ውስጥ የምናገኘው እውነታ ይሄው ነው። ኢኮኖሚክሱን የጎላ አድርገን እንድናይ የሚያደርገን መሰረታዊ ምክንያት፣ ጥንቱን ጠዋቱኑ እነ አዳም ስሚዝና ሪካርዶ የተባሉ የኢኮኖሚክስ ተመራማሪዎች፤
Human wants are unlimited ብለው የቀመሩት ፍኖተ - ኢኮኖሚክስ ነው፡፡
በዚህ ቀመር መሠረት፤ የሰው ልጆች መሰረታዊ ፍላጎት የሚሽከረከርበትን ሳይንሳዊ ቀመር እናገኛለን፡፡ ከጥንት ከጠዋት ጀምረን፣ የነገረ ሥራችንን ንጥረ - ነገር የምናውጠነጥነው፣ ከዚህ መሠረታዊ ሥርወ - ነገር በመነሳት ነው፡፡ በዚህ ንፍቀ  ክበብ ውስጥ አሮጌው የመውደቁን፣ አዲሱ የማሸነፉን መሠረታዊ ዲያሌክቲካዊ ድንጋጌ እናሰላው ዘንድ መላውን እንጎናፀፋለን፡፡ ማህበራዊው ሳይንሳም የሚገዛውና የሚተዳደረው በዚህ የማይሻር የዕድገት ሕግ ነው። ይሄን ሕግ ወሳኝ ነው ብለን ከተቀበልን፣ ብዙ ነገሮች ፍንትው ብለው ይታዩናል፡፡
ስለ አገራችን የሌብነት ሥርዓት የምንለው አለን፡፡ አንድ ታዋቂ የአገራችን ገጣሚ፣ በአንድ ዕውቅ የቴያትር ሥራቸው ውስጥ፤
ቀማኛን መቀማት ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ የድሆችን ጭንቅ
በእኔ ቤት ጭንቅ ነው አንድ ሰው ይሙት
አንድ መቶ ሺህ ሰው ኪኖር በምፅዋት
…ብለው ነበር፡፡ እጅግ ግልጽና አገር አከል ስንኝ ነው የቋጠሩት፡፡ እንመርምራቸው! እንመርምራቸው! እንመርምራቸው!
ነገሮችን በቅጡ ለማወቅ ሁኔታዎችን በጥንቃቄ ማጥናት ተገቢ ነው፡፡ በዋዛ የምትፈርስ አገር የለንም፡፡ በጫጫታና በሁካታ የፈረሰች አገር ብትኖር፣ የመጽሐፍ ቅዱሷ እያሪኮ ብቻ ናት!!   


Read 11994 times