Monday, 03 February 2020 11:34

በእሾህ የታጠረው ፖለቲካችን!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)


                 “--ሃገሪቱ ቡዳ ናት፤ ጎበዝ ወጣ ሲባል ትበላለች፤ ማስተዋል ያለውን ታንሸራትታለች፡፡ በቅርቡ እንኳ አቶ ለማ መገርሳን ልትውጥ አስባ ተፍታለች፡፡ በታሪክ ውስጥ ብዙዎችን አሳስታለች፡፡--”
              
             ከደርጉ የአፈና ፖለቲካ በኋላ በወያኔ ዘመን፤ ከአንድ ብቸኛ ፓርቲ ወደ ብዙ ፓርቲ፣ ከአንድ ልሳን መጽሔት ወደ ብዙ መጽሔት ተሸጋግረን ነበር፡፡ የወያኔ መራሹ መንግስት አመጣጥና አጀማመር ተስፋ ሰጪና በጎ መልክ ያለው ይመስል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ መጽሄትና ጋዜጦቹ፣ አዘጋጆቻቸውን ወደ ወህኒ ወርዉረው፣ ከህዝብ አይን ተሰወሩ፡፡ ፓርቲዎቹም ከጎሳ ያለፈ የሚያቀነቅኑት ሃሳብ፣ የሚያቀርቡት አማራጭ ስላልነበራቸው የትም መድረስ አልቻሉም፡፡ የአህያ ልጅ በቅሎ አይነት ሆኑ፡፡ የሃገሪቱ መሪዎች አበላሽተው ሰሯቸውና ጠብበው ቀሩ፡፡ ባለ ወንበሮቹ ለህልማቸው መሰላል አድርገው ቀረጹዋቸው፡፡ ወደ ኋላ የመጡት ፓርቲዎች የሰለጠኑና  የሃገሪቱን አንድነት የሚያስከብሩ ዐይነት ቢሆኑም፣ ወያኔ ዕድሜ አልሰጣቸውም፤ እየቀጠፈ በላቸው:: በተለይ የህዝቡን አንድነት ለመጠበቅ የሚተጉትን ሁሉ በእስርና እንግልት፣ ሌሎቹንም በገንዘብ ሀይል እየከፋፈለ ባዶ አደረጋቸው፡፡ ወህኒ የሚጣሉት ተጣሉ፣ የሚሰደዱት ተሰደዱ፤ ገንዘብ አፋቸው ላይ ጣል የተደረገላቸው፣ በተቃዋሚ ወንበር፣ የመንግስትን ዙፋን የሚከልሉ አጋፋሪዎች ሆኑ፡፡
ከወያኔ ጓዳ የመጣው ለውጥ ያግበሰበሳቸውን ሆድ አደሮች ሙሉ ለሙሉ መቀየር ስለማይችል የባሰባቸውን ዘወር እያደረገ፣ ሌሎቹን ይዞ መጣ:: ይህ አዲስ ቀለም የተቀባውና በዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጠ/ሚኒስትርነት ሀገሪቱን በመምራት ላይ ያለው ፓርቲ፣ ቁመናውና ፍልስፍናው፤ ዛሬ በሃገሪቱ ላይ ከሚንቀሳቀሱት ፓርቲዎች አንጻር፣ የተሻለ ነው ሊባል ይችላል፤ ከእነ ኮተቱም ከጥፋት ሊያድን የማይችል፣ ዕብደት ውስጥ ያልገባ፣ ነገ ምን ሊያመጣብን ይችላል? የሚል ጥንቃቄ የሚሰማው ዐይነት በመሆኑ ሃገሪቱን ከጥፋት ሊያድን ይችላል ብለን ትንሽ ተስፋ ልንጥልበት መችል ነው፤ ቢያንስ ሃገሪቱ እንዳትፈርስ ፍላጎት ያለው ነው፡፡
በሌላ በኩል ስናየው፤ የየትኛውም ብሄር ተኮር ፓርቲዎች መነሻ፣ ባብዛኛው ጥላቻ በመሆኑና የህዝብ ድጋፍ የሚያገኙትም በሃሳባቸውና በዕውቀታቸው ልክ ሳይሆን ጥላቻን ባራገቡበት ልክ በመሆኑ፣ ሁሉም በሚባል ደረጃ ከፍ ከማለት ይልቅ ቁልቁል ወደ ጎጥ እየወረዱ እንደሆነ እያየን ነው፡፡
የተሻለ አመለካከትና የሰለጠነ አተያይ አላቸው የምንላቸው ሁሉ ወደ ተራና የሞቅ ሞቅ ፖለቲካ እየገቡ፣ ወዳጆቻቸውን ሳይቀር ማሳፈር ይዘዋል:: ለጊዜው ውዥንብር ያስጮኸላቸውን የሰፈር አድመኞች እንደ ትልቅ ሰው የሚያስቆጥረው ግርግር፣ ትልልቅ የመሰሉንን  ሁሉ ወደ ጡጦ ሃሳብ እያሽቆለቆለ ጉድ አፍልቷል፡፡
ከታችኞቹ ፖለቲከኞቹ  ተርታ ላያቸው የማልፈልገው ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንኳ ምን እንደነካቸው ሳይታወቅ፣ የዜግነት መታወቂያውን በእጁ ያልጨበጠ ፖለቲከኛ መዝግበው ተገኙና ወዳጆቻቸውን አስደነገጡን:: በግሌ እንኳን በቀደሙት ጊዜያት አሻራ ያለውን ሰው ቀርቶ፣ የቱንም ጉዳዩ የሚመለከተውን ሰው ወደ ፓርቲያቸው ለምን አስጠጉ?  የሚል ጭፍን ጥላቻ የለኝም፤ ግን ለምን ነገሮችን ሰከን ብለው አላዩም! ቢያንስ የዜግነት ጥያቄ መኖሩን ለምን አላጠሩም?!...ፖለቲካ ውስጥ ችኮላና ስሜታዊነት የሚያመጣውን ጣጣ ለርሳቸው መንገር ለቀባሪ ማርዳት በመሆኑ ዝም ከማለት ውጪ ምንም ማለት አይቻልም፡፡
እኒህ ሰው በእኔ እምነት፣ ለኢትየጵያ ፖለቲካ ተስማሚና በሰላማዊ ትግሉ ልምድ ያላቸው፤ምናልባትም ግጭትን የሚጸየፉ ስለነበሩ፣ ለተዘበራረቀው ፖለቲካችን በጣም ተስፋ ሳደርጋቸው ቆይቻለሁ፡፡ በተለይ መጻሕፍታቸውን ሳነብ የታየኝ ተስፋ ብዙና መልካም ነበር፡፡ ቀደም ካሉት ዐመታት ጀምሮ  በጦቢያ መጽሄት ላይ ሳያቸው፣ ሰውየው እጅግ ሚዛናዊና ማንንም እማይፈሩ፣ ቀጥተኛና ሃቀኛ ፖለቲከኛ  ናቸው፡፡ አሁን አሁን ግን ፓርቲያቸው ውስጥ ያሉ ሰዎችን የብሄር ጠርዝ ይዘው ሃገር የሚከፍል፣ ሕዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ የጥላቻ ፖለቲካዊ አቋም ይዘው ሳይ፣ አካሄዳቸው ግራ የሚያጋባ ሆኖብኛል:: የአቋም ለውጥ ይሁን የስሜት ነውጥ ግራ ገብቶኛል፤ ከዚህ ዐይነቱ ጽንፈኛ አቋም ጋር ያዛመዳቸውም ነገር ግር አሰኝቶኛል፡፡ በተረፈ ከዘመነ ደርግ ጀምሮ የጠመንጃን ውጤትና የግጭትን ዋጋ የሚያውቁት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና አንጋፋው ፖለቲከኛ፣ የያዙትን አካሄድ መመዘን ያቅታቸዋል ብዬ ማሰብ ያዳግተኛል:: ምናልባትም ስጋቴ፣ የሃገሪቱን ፖለቲከኞች የሚበላ ሾተላይ እንዳያገኛቸው ነው፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት፤ “ሃገሪቱ ቡዳ ናት፤ ጎበዝ ወጣ ሲባል ትበላለች፤ ማስተዋል ያለውን ታንሸራትታለች፡፡ በቅርቡ እንኳ አቶ ለማ መገርሳን ልትውጥ አስባ ተፍታለች፡፡ በታሪክ ውስጥ ብዙዎችን አሳስታለች፡፡”
ይሁንና በግሌ የብሄር ፓርቲዎች ለብሄራቸው ለምን ይታገላሉ አልልም፡፡ ይሁን እንጂ ለራሳቸው ብሄር ሲታገሉ የሌላውን ቤት እያፈረሱ፣ የጎረቤታቸውን እንባ እየጠቡ መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም ቤቱ የሚፈርስበት ወገን ለጊዜው ዝም ቢልም፣ እርሱም ተራውን ጠብቆና ቀን አይቶ በሃይል ብቅ ማለቱ አይቀርም፤ ያኔ  መተላለቅ ይሆናል፡፡ የዚህ ዐይነቱ አካሄድ በእልህ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ መጨረሻው ተያይዞ ገደል መግባት ነው፡፡ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ይህ አደጋ የሚያሳስባቸው አይመስሉም:: ሁሉም ራሱን ለመከላከል ሰይፉን ከመዘዘ የሚያስከትለውን ጣጣ መገመት አቅቷቸዋል:: ነገሮች ከመንግስት እጅ ከወጡ ሊፈጠር የሚችለው ጉዳይ፣ በእንባና በጸጸት የማይመለስ መሆኑን ማሰብ የተሳናቸው ይመስላል፡፡
አሁን በሃገሪቱ ላይ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች አካሄድ ስናይ፣ በአብዛኛው ጉዳዩ የስልጣን እንጂ ለህዝብ ነጻነት የመቆርቆር አይመስልም፡፡ የአማራው የቅርብ ጊዜ ፓርቲም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ ተሟጋች ነን የሚሉትን በርካታ ፓርቲዎች ስናይ፣ ወደ ህዝቡ ሊደርስ የሚችል የበረከት ሃሳብ ብዙም አይታይም፡፡
እንደ ትንሽ ማሳያ ብንወስድ፣ በዘመነ ወያኔ፣ ያለ ጥፋቱ ቶርች ገብቶ የተደበደበውና ሁለት እግሮቹ ለተቆረጡት ወጣት አንድም ሰው ለህይወቱ ስለሚጠቅመው ወይም አንዳች ተሸከርካሪ ሊያቀርብለት የሞከረ ፖለቲከኛ አልታየም፤ ይልቁኑ ለፖለቲካና ለራስ ምስል ማግዘፊያ ሲጠቀሙበት ቆይተው ረስተዉታል:: ሚሊየኖቻቸው ባንክ የሚጨፍሩ  የህዝብ ታጋዮች ግን የቅንጦት ኑሮ እንጂ ህዝብ ምናቸውም ስላልሆነ አንድም ነገር ሲያደርጉለት አላየንም፡፡ ይልቅስ ህዝብን ገበያቸው አድርገዋል፡፡ አንዳንዶቹም ግፍ የተሰራባቸውን ወገኖቻቸውን በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ስቃያቸውንና እንባቸውን በሚያረክስ መንገድ ገዳዮቻቸው ጋ እየሄዱ በስቃያቸው ተሳልቀዋል፡፡ በይቅርታ እንኳ ያልታጠበ በደላቸውን በመድገም ቁስላቸው ላይ ሚጥሚጣ ጨምረዋል፡፡ ለተራበው ህዝብ ዳቦ፣ ህክምና ብርቅ ለሆነበት ደሃ ሃኪም ቤት አይመኙም፤ ይልቅስ እንጀራቸው እንዳይቋረጥ፣ ጭብጨባው እንዳይጎድልባቸው እሳቱ ላይ ቤንዚን ያርከፈክፋሉ፡፡
እውነት ለመናገር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጣሪያውን እየያዙ ያሉት እሾሆቹ ናቸው፡፡ በሃገራችን እንደተለመደው በየትኛውም ፓርቲ ውስጥ ፖለቲካውን የሚደፍሩት ሆዳሞችና አስመሳዮች ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ የተሻሉ ሰዎች ገብተዋል ካልንም፣ በ1997 ዓ.ም በወያኔ ሽንገላ፣ እውነተኛ ምርጫ ይካሄዳል ብለው የተታለሉ ብቻ ነበሩ፡፡
ከዚያ ውጭ ቀደም ሲል ወደ ፖለቲካ የተጠጉትን ሁሉ የበላው የደርግ እሳት ሰውን ፈሪ አድርጎታል፡፡ ኦሮሞ ሆኖ ለአለም አቀፋዊነት ይዘምር የነበረው ሓይሌ ፊዳን ጨምሮ(ሓይሌ መዝሙሩ ሁሉ ዐለምዐቀፋዊነት እንደነበር ድርሳናት ይናገራሉ) ተስፋዬ ደበሳይን፣ ጌታቸው ማሩን፣ ብርሃነመስቀል ረዳን፣ ትውልዱን ሁሉ የበላው እሳት ፍርሃት ለቆ ሄዷል፡፡ አንዳንዶችም በዐይነአፋርነት ጥግ ስለያዙ ደፋሮችና ጭራ ቆልተው ሳኒቲም የሚለቅሙ ሆዳሞች ተሰግስገውበታል፡፡ ቀደም ሲል በንጉሱ ዘመንና በደርጉ ጊዜ ለሰዎች መሞት ክብር ሲሆን፤ አሁን ለራስ ክብር ሌሎችን ማስገደል ተለምዷል፡፡ ሰው ብር መሰብሰቢያ ጭዳ እንጂ የማንም ርዕሰ ጉዳይ አልመስል ብሏል፡፡
ዕድሉ እስኪመስል ድረስ ስሙ ጥላሸት የተቀባው የአማራ ህዝብም እስካሁን መከራውን የሚቀንስለት አላገኘም፡፡ ባለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት ብሄር ብሄሩን ያስተዳድር በተባለ ጊዜ እንኳ እሱን የሚያስተዳድሩት የራሱ ተወላጆች አልነበሩም፤ ስለዚህም እንደ እንጀራ ልጅ ሲደቆስና ሲከሰስ ኖሯል፡፡ የክልሉ ቢሮ ሃላፊ ሳይቀር ከሌላ ክልል እንዲሾምለት ተደርጎ ነበር፡፡ ለምን እንደሆነ ባይገባኝም ሁልጊዜ በጥቂት የገዢው መደብ ግፍና ጭቆና የተነሳ ሁሉንም አማራ፣ እዚያ ውስጥ የሚነክሩ ጅሎች ቁጥር አሁንም አልቀነሰም፡፡ የአማራ ገበሬ የቱም ኢትዮጵያዊ ወገኑ የተቀበለውን መከራ መቀበሉን ማስታወስ የሚፈልግ የለም፡፡ እኩል ድህነት እንደፈጨው፣ ግፈኞች እንደረገጡት የሚያስታውስ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ለማየት በወሎ ድርቅ ጊዜ ስፍራው ድረስ ተጉዞና ዐጥንቶ የጻፈውን  የደራሲ ብርሃኑ ዘርይሁንን  ‹‹ማዕበል›› የተሰኘ ታሪክ ቀመስ መጽሃፍ ብቻ ማንበብ በቂ ይመስለኛል፡፡ ከረሃቡ ጎን ለጎን የባለርስቶች ዛቻና ዱላ ምን ያህል እንዳደቀቀው መጽሀፉ ያሳያልና!! የአማራ ገበሬ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ደም አልቅሶ፣ መሬቱን ተነጥቆ የኖረ ነው፡፡ በሌላ ክልል ነበረ ለሚባለው ባለርስትነቱም ከሆነ አማራውም ኦሮሞውም አብሮ ባለርስት እንደነበረ ብዙ ምስክሮች መጻሕፍት የጻፉለት ሀቅ ነው፡፡ ይህንን  ከማንም የበለጠ ደቡብ ክልል የኖርን ኢትዮጵያውያን እናውቀዋለን፡፡
ይሁን እንጂ ፖለቲከኞቻችን ይህንን የተገነዘቡት፣ ወይም ለፖለቲካቸው ቁማር ስለማይጠቅማቸው የፈለጉት አይመስልም:: ሌላው ቀርቶ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሲነሳ ከስክነቱ ይልቅ ደም ፍላቱ አይሎ ስለነበር ፖለቲካውን ወደ ሌላ ጠርዝ እንዳይገፋ ተፈርቶ  ነበረ፡፡ በርግጥ በዚህ ዘመን ለተገፋውና ተወካይ ላጣው ህዝብ አለሁልህ ማለት ደግ ነው፡፡ ግን ደግሞ ሌሎች ላይ ጥላቻን ማሳደር የተለመደውን ስህተት መድገም እንዳይሆን ረጋ ብሎ ማሰብ ይጠየቃል፡፡ አጠገባችን ካለው ባሻገር በተለያዩ ክልሎች የሚኖረውን ህዝብ ከአደጋ ማዳን የሚገባ ይመስለኛል፡፡ የብሄር ፖለቲካ በነገሰባት ሃገር አማራ ብቻ ጭዳ ይሁን፣ተከራካሪ አይኑረው  የሚለውን ግብረገብነት  በግሌ አልቀበለውም፡፡ የራሴ የሚለው፣ ለመብቱ የሚታገልለትና የሚጠይቅለት፣ እንደ ሌሎቹ ሁሉ አሁን ባለው ስርዐት ተጎጂ እንዳይሆንና በግፍ እንዳይገደል ሊከራከርለት ይገባል፡፡
ይሁን እንጂ ጽንፍ ሄዶ የዘመናት ከሌሎች ጋር በፍቅር አብሮ የመኖር ታሪኩን ጥላሸት ሊቀባበትና የገነባውን ኢትዮጵያዊ መልክ ሊንድበት አይገባም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚለውን የስልጣኔና የክብር ስም ሌሎች ሰነፎች ለማዋረድ እንደሚሞክሩት ጫፍ ለመያዝ መጋለብ አይጠበቅበትም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚኮራበት፣ ከሃገር አልፎ የጥቁር ህዝቦችን ስነልቦናዊ እስራት የፈታ ታላቅ ስምና ታሪክ እንጂ  የሚታፈርበት ስንፍናና ውድቀት አይደለም፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት የቀደመው የደርግ አገዛዝ ጠባሳ ሰውን ፈሪ ስላደረገው፣ እሾሆች አደባባዩን እየያዙት ስለሆነ ጥንቃቄ የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ ያለን ይመስላል፤ ሃገሪቱ እሾሆች አናቷ ላይ እንዳይወጡ መጠንቀቅ አለባት፡፡ ይህን ለማሳየት መጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ በመሳፍንት የተጻፈውን ምሳሌ ማየት ይበቃል:: ወይራው፣ በለሱ፣ ወይኑ፣ የየራሳቸውን ነገር እየቆጠሩ እምቢ አሉ፡፡ ምናገባኝም ሊሆን ይችላል፡፡ በመጨረሻ እሾህ ንጉስ ሆኖ ቁጭ አለ:: እሾህ ስልጣን ሲይዝ መቧጠጥ፣ መቁሰል ነው ትርፉ፡፡ ስለዚህ በጊዜ ሁሉም ሰው የሃገሬ ነገር ያገባኛል ብሎ፣ በተለይ የሃገር አንድነት ጉዳይን ትኩረት ሰጥቶ ማሰብና መወሰን ይኖርበታል:: በየመንደሩ ሃገሪቱ ያለችበትን ክፉ ቀን እንኳ ከግምት ሳያስገቡ ቅርጫው ላይ ያቀረቀሩ ሁሉ አሳፋሪ ታሪክ ውስጥ እንዳሉ ቢገነዘቡ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ቆመን ማሰብ ካልቻልን ሁላችንም እንጎዳለን፡፡ ከዚህ ጥፋት አምላካችን ሊያድነን እንደሚችል ባለሙሉ ተስፋ ነኝ፡፡ እኛ ግን አርቀን ብናስብ መከራችንን እንቀንሳለን፡፡


Read 1252 times