Monday, 03 February 2020 11:37

ሕግና ለዘብተኞች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

   “--አንዳንድ ለዘብተኛ ሙስሊሞች፣ ይህንን ከማለት አልፈው ‹‹እስልምና›› ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት አብረው የሚሄዱ ብቻ ሳይሆኑ በእስልምና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አስተዳደርን ማስፈን በግድ ሊፈጸም የሚገባው አስፈላጊ ተግባር ነው›› የሚል ክርክር ያቀርባሉ::--”
በርካታ ለዘብተኛ ሙስሊሞች ‹‹ዴሞክራሲ›› እና ‹‹ሰብዓዊ መብት›› የሚባሉት ጽንሰ ሀሳቦች ‹‹ዓለም አቀፋዊ አይደለም›› የሚለውንም ሆነ ‹‹ምዕራባውያን በተለየ ሁኔታ ተግባራዊ የሚያደርጓቸው እንጂ ለሌሎች ሀገሮች ባህል ምቹ ወይም ተስማሚ ያልሆኑ ናቸው›› መባሉን አይቀበሉም፡፡ እንዲህ ያለው አባባል ብሔርተኝነትን ለመሸፈን የሚደረግ ነው:: ምክንያቱም አባባሉ የሚያመለክተው ከምእራባውያን ውጪ ያሉት አገራት በባሪያቸው ‹‹በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ መኖር አይችሉም፣ ለሕግ የበላይነት አይገዙም፣ ስለ ሰዎች መብት አይገባቸውም›› ማለት ነው:: ምዕራባውያን ‹‹ዴሞክራሲ›› የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ማመንጨታቸው እውነት ነው፡፡ የግለሰብ መብት የሚባለውም ነገር ከዴሞክራሲ ተነጥሎ የማይታይ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ከምዕራባውያን ውጪ ያሉ ማህበረሰቦች ሁሉ ዕድሜ ልካቸውን በአምባገነን ሥርዓት ጫማ ስር ሆነው እንዲሰቃዩ ተፈርዶባቸዋል ማለት ግን አይቻልም፡፡ ሰብዓዊ መብትን ማክበር ማለት መሰረታዊ የሞራል መርህ ነው ብለው ያምናሉ፤ ለዘብተኞች፡፡ በመሆኑም ሰብዓዊ መብትን ማክበር ሙስሊሞች ልንከተለው የሚገባው የስነ ምግባር ግብ ነው፡፡ በርግጥ በርታ ለዘብተኛ ሙስሊሞች ‹‹እስላማዊ ሕግ የታወቁ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አሉት›› የሚለው ሀሳብ የሚታመን አለመሆኑን በመቀበል፣ ሰብዓዊ መብት የሚባለው ጽንሰ ሀሳብና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ እንደ ሥርዓት ከእስልምና ሕግም ሆነ ከእስልምና ስነ መለኮታዊ ትምህርት ጋር የሚቃረኑ አይደሉም ይላሉ፡፡ አንዳንድ ለዘብተኛ ሙስሊሞች፣ ይህንን ከማለት አልፈው ‹‹እስልምና›› ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት አብረው የሚሄዱ ብቻ ሳይሆኑ በእስልምና ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት አስተዳደርን ማስፈን በግድ ሊፈጸም የሚገባው አስፈላጊ ተግባር ነው›› የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡
እስላማዊ ባህልን በመገንባት ሂደት ማንኛውም ሰው ክብርና ነፃነትን የማግኘት መብት ትንሹ ሊረጋገጥለት የሚገባ መብት ነው በማለት ይከራከራሉ፤ ለዘብተኞች፡፡ ለዘብተኞች በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን እምነት የሚያጠናክሩት፣ ጭቆና በፈጣሪና በሰዎች ላይ የሚፈጸም ወንጀል መሆኑን በአስረጅነት በማቅረብ ነው:: ቁርኣን ‹‹ጨቋኞችን›› ምድርን የሚያበላሹ መሆናቸውን፣ ‹‹ጭቆናን›› ደግሞ የፈጣሪን ሕግ መጣስ መሆኑን ይገልጻል፡፡ በለዘብተኞች አስተሳሰብ ሁሉም የሰው ልጆች የተከበሩ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ፈጣሪ ሁሉንም የሰው ልጆች የላቁ እንዲሆኑ ትሩፋቱን ሰጥቷል:: ይህንን በተመለከተ ቁርዓን እንዲህ ይላል፡፡
የአዳምንም ልጆች በእርግጥ (ከሌላው ፍጡር) አከበርናቸው፡፡ በየብስና በባህርም አሰፈርናቸው፣ ከመልካሞች (ሲሳዮች) ሰጠናቸው፣ ከፈጠርናቸውም ፍጡሮች በብዙዎቹ ላይ መብለጥን አበለጥናቸው፡፡ (ቁርዓን፤ 17፡70)
ነፃነትና ምርጫ ለሰብዓዊ ክብር እውን መሆን አስፈላጊ ቅመሞች ናቸው፡፡ ሰዎች በካቴና ሲታሰሩ፣ ወህኒ ሲወርዱ፣ ሲጨቆኑ ወይም የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው እንዳይወስኑ ሲደረጉ በራስ የመተማመን መንፈሳቸው ክፉኛ የሚጎዳ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ትልቁና ስልታዊ ነጻነት ንፍገት ደግሞ በመንግሥታት የሚደረግ አምባገናንነትና ጭቆና ነው፡፡ ጭቆና መንግሥት የሕዝብን ክብር የሚቀማበት ዘዴ ነው፡፡ ዜጎችን መቆጣጠርና በሕይወታቸው ጣልቃ መግባት የዘመናዊ መንግሥታት የእለት ከእለት ተግባር መሆኑን ለዘብተኛ ሙስሊሞች ይገነዘባሉ፡፡ መንግሥታት የሥልጣን ኃይል ያላቸው መሆኑ፤ የተለየ ሀሳብ የሚያራምዱ ሰዎችን ማሳደድ፣ ማሰርና መግረፍ አስችሏቸዋል፡፡
ምንጭ፡-“ታላቁ ዝርፊያ… እስልምናን ከጽንፈኞች የማስመለስ ትንቅንቅ” መጽሐፍ

Read 3101 times