Print this page
Monday, 03 February 2020 11:36

የፖለቲካ ጨዋታው ተቀይሯል! (100%)

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(8 votes)

  ትላንት ምርጫ ሲቃረብ የሚያስፈራን የመንግሥት ድንፋታና እርምጃ ነበር፤ ዛሬ የሚያስፈራን የፅንፈኛ ተቃዋሚው ጠብ ቀስቃሽ የጥላቻ መልዕክት ሆኗል፡፡
ትላንት የሚያስፈራን የመንግሥት በጠመንጃ የታገዘ ሃይልና ጉልበተኝነት ነበር፤ ዛሬ የሚያስፈራን የፅንፈኛ ተቃዋሚ የቡድንተኝነት አካሄድና ወደ ቀውስ የሚያስገባ አጀንዳ ነው፡፡
ትላንት የሚያስጋን የመንግሥት ፍረጃና ከፋፋይነት ነበር፤ ዛሬ የሚያስፈራን የተቃዋሚው ሰፈር ጐራ በዘርና ጎሳ የተከፋፈለ አደገኛ እንቅስቃሴ ነው፡፡  
ትላንት የሚያስፈራን መንግሥት ምርጫውን እንዳያጭበረብር የሚለው ጉዳይ ነበር፤ ዛሬ የተደቀነብን ስጋት “ፅንፈኛው የተቃዋሚ ቡድን ምርጫውን ቢያጭበረብርስ?” የሚለው ጥርጣሬ ነው::
ትላንት የሚያስፈራን መንግሥት ምርጫውን ቢሸነፍ የሚወስደው ሥልጣኑን ማስጠበቂያ “ቁርጠኛ” እርምጃ ነበር፤ ዛሬ የሚያስፈራን ተቃዋሚው ቢሸነፍ አመጽና ረብሻ ለመቀስቀስ የሚደረድረው ሰበብና የሚወስደው እርምጃ ነው፡፡
ትላንት የሚያስፈራን የምናውቀው ‹ሰይጣን› (ኢሕአዴግ)፤ “ደልሎም ይሁን አስገድዶ ሥልጣን የሙጥኝ ማለቱ አይቀርም” የሚለው ጉዳይ ነበር፡፡ ዛሬ የሚያሰጋን… የተቃዋሚው ቡድን “በባሌም ይሁን በቦሌም” ቤተ - መንግሥት የመግባት ጥልቅ መሻት ነው፡፡
ትላንት የሚያስፈራን በምርጫ ሰሞን መንግሥት በተቆጣጠራቸው ‹‹የሕዝብ ሚዲያዎች›› የሚነዛው አደገኛ ፕሮፓጋንዳ ነበር፤ ዛሬ የሚያስፈራን የተቃዋሚው ጎራ በጽንፈኛ ሚዲያዎችና በፌስ ቡክ የሚያሰራጨው ግጭት ቀስቃሽ ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡
ትላንት ምርጫውን በግድም በውድም ገዢው ፓርቲ እንደሚያሸንፍ ስለምናውቅ ውጤቱ አያስፈራንም ነበር፤ ዛሬ አሸናፊውንም ተሸናፊውንም ስለማናውቅ በስጋት መራዳችን ቀጥሏል፡፡
ትላንት የሚያስፈራን መንግስት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ምሎ መገዘቱ ነበር፤ ዛሬ ስጋት ውስጥ የከተተን የሚበዛው ተቃዋሚ አደገኛ በሆነው የዘረኝነት ፖለቲካ ውስጥ መዘፈቁ ነው፡፡
ትላንት የሚያስፈራን የመንግስት ዲሞክራሲን ይበልጥ ማፈንና የፖለቲካ ምህዳሩን ማጥበብ ነበር፤ ዛሬ የሚያሰጋን የፅንፈኛ ተቃዋሚ ጐራው የሥልጣን ጥመኝነት፣ አገራችንን እንዳያፈርሳትና መድረሻ እንዳናጣ ነው፡፡
ለሁሉም ግን ፈጣሪ አይርሳን!! (ደግነቱ ረስቶን አያውቅም፤ እኛ እንዳንረሳው እንጂ!)

Read 4940 times