Tuesday, 04 February 2020 00:00

የአገራችን ፖለቲካ፣ የሆንግ ኮንግ ወይም የፈረንሣይ ፖለቲካ አይደለም

Written by  ዮሃንስ. ሰ
Rate this item
(2 votes)

      - ለወራት ባልበረደ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሰልፍ፣ የሰው ህይወት ላይጠፋ ይችላል -በፈረንሳይ፡፡
              - በአገራችን ግን፣ የፖለቲካ ሰልፍ ተጀምሮ፣ በማግስቱ ከተደገመና በሳልስቱ ከቀጠለ… አገር ቀለጠ
              - ለሦስት ወራት የሚካሄድ የምርጫ ዘመቻና የፖለቲካ ንትርክ፣ ለአገራችን “ኦቨር ዶዝ” ነው፡፡
             
             በሆንግ ኮንግ፣ ከስድስት ወር በላይ የዘለቀው የፖለቲካ ውዝግብና ሰፊ የተቃውሞ ቀውስ፣ አገሪቱን (ከተማዋን) ክፉኛ ጐድቷታል:: ኑሮና ስራ፣ ንግድና እንቅስቃሴ ሁሉ፣ ከሳምንት ሳምንት እየተደነቃቀፈ፣ ኢኮኖሚዋ ተንገራግጯል፡፡ በስኬት አርያነቱ የሚታወቀው ኢኮኖሚ፣ ከማደግ ይልቅ ወደታች አሽቆልቁሏል:: ይህም ብቻ አይደለም፡፡
የሁለት ሰው ህይወት አልፏል፡፡ ድንገት ወድቆ የተጐዳ አንድ ወጣት፣ እንዲሁም በጡብ የተፈነከቱ አዛውንት፣ ሞተዋል፡፡ አይናቸው የጠፋ፣ እጃቸው የተሰበረ፣ የቆሰሉ፣ በእሳት የተለበለቡ ሰዎች በርካታ ናቸው - አሳዛኝ የቀውስ መዘዝ፡፡
በእርግጥ፣ ለተቃውሞ መነሻ የሆነው የህግ ደቂቅ፣ ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡ የቻይና መንግስት፣ “በወንጀል እጠረጥራቸዋለሁ” በማለት ጥያቄ ካቀረበ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ተጠርጣሪዎችን ለቻይና አሳልፋ እንድትሰጥ የሚያስገድድ ነበር - ረቂቁ ህግ፡፡ ሰፊ ተቃውሞ የተለኮሰው በዚህ ህግ ሳቢያ ቢሆንም፤ ውስጥ ለውስጥ ሲብላሉና ሲብሰለሰሉ የቆዩ በርካታ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስጋቶች ናቸው፣ ዋናዎቹ የቀውስ መንስኤዎች፡፡
ሆንግኮንግ፣ ለ50 ዓመታት፣ እንደ አሜሪካና እንግሊዝ የነፃነት አገር ሆና፣ በዓለም ካርታ ላይ ግን እንደ አንድ የቻይና ክፍለ ሀገር ሆና እንድትቆይ ነበር፤ በ1997 አለማቀፍ ውል የተፈረመው፡፡ አሁን ቀጠሮው ተጋምሷል:: 27 ዓመት ነው የቀረው፡፡ ያኔ ሆንግ ኮንግ፣ ሙሉ ለሙሉ በቻይና ትጠቃለላለች፡፡ በአንድ በኩል፣ ሩቅ መስሎ ይታይ የነበረው የ50 ዓመት ቀጠሮ እየተቃረበ ሲመጣ፣ በሆንግኮንግ ውስጥ የፍርሃት ስሜት እየበረታ መጥቷል፡፡ ለቻይና መንግስት ደግሞ፣ ሆንግ ኮንግን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቅለል፣ የቀጠሮው ዓመት ሩቅ ሆኖበታል:: እናም ገና ካሁኑ፣ ማሴርና መቦርቦር አብዝቷል ብለው የሚሰጉ የሆንግ ኮንግ ነዋሪዎች ብዙ ናቸው፡፡
በዚህ መሃል፣ “ተጠርጣሪዎችን ለቻይና አሳልፎ መስጠት” የሚል ህግ ሲመጣ፣ ተቃውሞው ገንፍሎ አገሪቱን ለወራት አጥለቀለቃት፡፡  
ይህንን ከአገራችን ጋር አነፃጽሩት፡፡ የፖለቲካ ፉክክርንና ክርክርን የሚያግድ፣ የድጋፍና የተቃውሞ ሰልፍን የሚከለክል አፈና፣ ለየትኛውም አገር፣ ክፉ በሽታ ነው፡፡ ነገር ግን፣ የድጋፍና የተቃውሞ ሰልፍ አለቅጥ ከበዛ፣ የፖለቲካ ክርክርና ውዝግብ እንደ እለት ምግብ እየተዘወተረ አለልክ ከበረከተ፣ ለማንኛውም አገር አደገኛ በሽታ ይሆናል፡፡ አደጋው ግን ይለያያል፡፡  እንደየአገሩ የስልጣኔ ደረጃ፣ የዚያኑ ያህል የአደጋው መጠን ይለያያል፡፡
በስልጣኔ ጐዳና ደህና የተራመዱ አገራት፣ የፖለቲካ ክርክር ከጨዋነት እንዳያፈነግጥ፣ የአደባባይ ሰልፍ ከህግና ስርዓት እንዳይርቅ የመግራት አቅም አላቸው፡፡ እንዴት? አብዛኛው ሰው ጨዋነትን የሚመኝ ህግ አክባሪ ቢሆን፣ በቂ አይደለም፡፡ ትክክለኛ መርሆች ያስፈልጋሉ:: የሀሰት ውንጀላንና ስድብን፣ አመጽንና ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችሉ ጠንካራ የስነምግባር፣ የነፃነትና የህግ የበላይነት መርሆች እስካልተዳከሙ ድረስ፣ ብዙ አደጋ አይፈጠርም:: የስልጣኔ ልክም ይሄ ነው፡፡ በኋላቀር አገራትስ? ለአንዳንዱ፣ የፖለቲካ ክርክርና ሰልፍ ሲበዛ፣ አጣዳፊ አለርጂ ይሆንበታል፡፡ ለአንዳንዱ ደግሞ፣ ገዳይ “ኦቨር ዶዝ” ይሆንበታል፡፡
ለሆንግ ኮንግስ? በየጊዜው ከ100ሺ በላይ ነዋሪዎች፣ ለተቃውሞ ሰልፍ በተደጋጋሚ ወደ አደባባይ እየወጡ፣ ከሚሊዮን በላይ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፍ
የሚካሄዱበት አጋጣሚ እየተፈጠረም፣ ሆንግ ኮንግ አልተተራመሰችም፡፡ ከነዋሪዎች መካከል ሲሶ ያህሉ፣ ለተቃውሞ ቢወጡም፣ አልተናወጠችም፡፡ አነሰ ቢባል፣ አንድ ሺ እዚያ፣ 10ሺ ወጣቶች እዚያ ከሳምንት ሳምንት ያለማቋረጥ  ተቃውሞ እያሰሙ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፎቹ እጅግ ሰላማዊ ስለነበሩ፣ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰ የከፋ ጉዳት አልነበረም፡፡ በእርግጥ፣ ቀስ በቀስ ነገሩ እየደፈረሰ፣ ሰላማዊ ሰዎች አደባባይ ከመውጣት እየተቆጠቡ፣ ከተቃውሞ ይልቅ ወደ አመጽ የሚያዘነብሉ ጥቂት ነውጠኛ ወጣቶች፣ ሜዳውን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ አይተናል:: ድንጋይ ውርወራ፣ ዱላ ስንዘራ፣ የህንፃ በርና መስኮት መስበር፣ መንገድ መዝጋትና ስራን መረበሽ ነው ፍላጐታቸው፡፡
ከዚህ መዘዝ ማምለጥ ያስቸግራል፡፡ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፍ፣ ያለ እልባት ለወራት ከቀጠለ፣ ‹‹ሰልጠን›› ላሉ አገራትም አደገኛ ነው - ለነውጠኛ ዓመፀኞች በር ይከፍታል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐን የሚመጣ መንትያ መዘዝም አለ፡፡
በኤስያ ውስጥ፤ በሙያ ብቃቱና በስነምግባር ጥራቱ ቀዳሚ እንደሆነ የሚነገርለት የሆንግ ኮንግ ፖሊስ፣ ፈተና ላይ ከመውደቅ አላመለጠም፡፡ አንዳንዶቹ ፖሊሶች ስርዓት ከማስከበር ይልቅ፣ ወደ  እልህና ቁጣ ገብተዋል፡፡ ከዚያም አልፈው የዘቀጡ ጥቂት ነውጠኛ ፖሊሶችም አሉ፡፡ እናም በጭካኔ ሰላማዊ ሰዎችን የማጥቃትና፣ የወደቀን ሰው የመደብደብ ክፋት፣ መከሰቱ አልቀረም፡፡
ታዲያ፣ ከወራት የፖለቲካ ውዝግብና የተቃውሞ ሰልፍ በኋላ፣ የጥቂት ነውጠኛ ወጣቶች አመጽና፣ የጥቂት ነውጠኛ ፖሊሶች የጭካኔ ጥቃት ቢከሰትም፣ ከቁጥጥር ውጭ አልወጣም፡፡
በአገራችንስ?
የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሰልፍ፣ ከአንድ ቀን ካለፈ፣ በማግስቱ ከተደረገመ፣ በሳልስቱም ከቀጠለ፣ አገር ቀለጠ ማለት ነው፡፡ ስንቱ እንደሚሞት፣ ስንቱ እንደሚቆስልና ስንቱ ከኑሮ ተነቅሎ እንደሚሰደድ፣ በተደጋጋሚ አይተናል:: የሚዘረፈውና በቃጠሎ የሚጋየውን ቤትና ንብረት፣ እርሻና ፋብሪካ  አስቡት፡፡
በፈረንሳይስ? ቅዳሜ ቅዳሜ ብቅ እያሉ በየከተማውና በየጐዳናው ቅሬታቸውን በሚገልፁ “ብጫ ለባሽ” ነዋሪዎች አማካኝነት የተቀሰቀሰው ሰፊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ፣ አመት ሞልቶታል፡፡ አዎ፣ ፈረንሳይ ከሃብታም አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ የኢኮኖሚ መሰረቷ፣ እንደ ብዙዎቹ የአውሮፓ አገራት፣ ተሸርሽሯል፡፡ የዜጐች ኑሮም ብርድ ብርድ ብሎታል፡፡
በእርግጥ ለዓመታት እየተጠራቀመና እየተደራረበ በመጣ የኑሮ ቅሬታ የተማረሩ ዜጐች፣ በየሳምንቱ አደባባይ መዋል የጀመሩት፣ ገና አምና ህዳር ወር ላይ ነው፡፡ ለምን?
በጣሊያንና በእንግሊዝ እንደታየው፣ በፈረንሳይም ባለፉት 20 ዓመታት፣ የፋብሪካ ስራ ተቀዛቅዟል፡፡ ከመስፋፋት ይልቅ እየተሸረሸረ፣ ሩብ ያህል ነባር የፋብሪካ ስራ ቀንሷል፡፡ ሚሊዮን ያህል የፋብሪካ የስራ እድሎች ተዘግተዋል፡፡
የሚሊዮኖች ኑሮ፣ ከመሻሻል ይልቅ መቅኖ እየሸሸው፣ ደንዘዛ አልያም ተስፋ የለሽ ቀበዝባዛ ህይወት ሆኖባቸዋል… ለብዙ ፈረንሳዊያን፡፡
መንግስት ደግሞ በየጊዜው ታክስ ይጨምራል፡፡
ከአገሪቱ የአመት ምርት ውስጥ፣ መንግስት ግማሽ ያህሉን ይወስዳል፡፡ በዚህ ሁሉ ላይ፣ “የካርቦን ልቀትን ወደ ዜሮ ለማውረድ” በሚል ምክንያት፣ በነዳጅ ላይ አዲስ ተጨማሪ ታክስ ታወጀ፡፡
እየተቆለለና እየከበደ በመጣው የኑሮ ቅሬታ ላይ፣ አዲስ የታክስ ጫና ሲደረብበት፣ የ “ብጫ ለባሾች” ተቃውሞ ተለኮሰ፡፡ ለሳምንታት፣ ከዚያም ለወራት ሰላማዊው ተቃውሞ ቀጥሏል::
በእርግጥ ሳምንት አልፎ ሳምንት በመጣ ቁጥር፣ ከሰላማዊ ሰልፈኞች መሃል፣ እዚህም እዚያም፣ ግርግርና ረብሻ የሚያምራቸው፣ በጊዜያዊ የቁጣ ስሜት አልያም በክፉ የአምባጓሮ አመል፣ አመጽ የሚፈጥሩ ነውጠኞች አልጠፉም፡፡ የፓሪስ አደባባይና ጐዳናዎች፣ የሙዚየምና የንግድ ህንፃዎች፣ ከአንዴም ሁለቴ የቃጠሎ መናኸሪያ ሆነዋል፡፡
በፖሊስ በኩልስ? ህግና ስርዓትን የማስከበር፣ በየቦታው ጥበቃ የማጠናከር፣ ሁከተኛና ነውጠኛ ሰዎችን የመግታት፣ ለጊዜው በቁጥጥር ስር የማዋል፣ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎችንም እንደየጥፋታቸው ልክ ለፍርድ የማቅረብ ትክክለኛ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመፈፀም የሚጥሩ ናቸው - አብዛኞቹ ፖሊሶች:: ነገር ግን፣ ህግን ከማስከበር ይልቅ፣ በዘፈቀደና በእንዝህላልነት፣ በእልህና በቁጣ፣ ከዚያም አልፎ በክፋትና በጭካኔ፣ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ጥቂት ፖሊሶች በገሃድ ታይተዋል፡፡
እናም ዘኢኮኖሚስት፣ በሳምንታዊ መጽሔቱ እንደዘገበው፣ “ብጫ ለባሽ” ተቃውሞ ከተጀመረ ወዲህ፣ በዓመት ውስጥ፣ አስራ አምስት ሰዎች፣ አንድ አይናቸው ጠፍቷል፡፡
ሌሎች 5 ሰዎች እጃቸውን አጥተዋል:: ከ300 በላይ ሌሎች ሰዎችም ተፈንክተው ተጐድተዋል - አካላቸው ባይጐድልም፡
ይህንን ከአገራችን ጋር አነፃጽሩት፡፡ ሰላማዊ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሰልፍ፣ ለአንድ ቀን፣ በአንድ ቦታ በሰላም ሊጠናቀቅ ይችላል:: ከተደጋገመ ግን ግርግር፣ ረብሻ፣ ሁከት፣ አመጽ ይተካዋል፡፡ መንገድ ከመዝጋት ጀምሮ ሰዎችን ከኑሮ እስከመንቀል፣ ሱቅ ከመዝጋት ጀምሮ እስከማቃጠል፣ ከዝርፊያ እስከ ግድያ፣ አካባቢው ሁሉ ሲዖል ይሆናል፡፡ ፖሊስስ? አንድ ሁለት ቀን፣ በጥንቃቄና በብቃት፣ ህግና ስርዓትን ማስከበር ይችል ይሆናል፡፡ ከዚያስ? አንዳንዴ፣ ፖሊስ ከዳር ሆኖ ይመለከታል፤ ሰዎች በአመጽ ይገደላሉ፡፡ ብዙ ህይወት ይጠፋል፡፡  
ወይም አመፁ፣ ከፖሊስ አቅም በላይ ይሆንና፣ የሞት ሽረት ወከባ ውስጥ እየገባ፣ የስሜትና የዘፈቀደ እርምጃ እየበረከተ፣ ለጥቂት መጥፎ ፖሊሶች፣ የክፋት እድል ይከፈትላቸዋል:: ሰላማዊ ሰዎች ይሞታሉ፡፡
የአገራችን “ሰላማዊ ፖለቲካ” ሁሌም፣ እንዲህ በጥፋት አፋፍ ላይ የሚውተረተር፣ ከሁለት ከሦስት ቀን በላይ በፈተና ውስጥ ሰላማዊ ሆኖ ለመዝለቅ የሚቸገር እንደሆነ፤ እልፍና እልፍ ጊዜ በገሃድ አይተነዋል፡፡
ለዚህም ነው፣ የምርጫ ዘመቻውም ሆነ የፓርቲዎች ፉክክርና የፖለቲከኞች ክርክር፣ የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፎች፣ “ኦቨር ዶዝ” እንዳይሆኑ መጠንቀቅ፣ ብልህነት የሚሆነው:: ክርክርና ፉክክር፣ የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፍ ካልተንዛዛ፣ ስልጣኔን ባያስገኝልንም ወደ ስልጡን ፖለቲካ ለመራመድ ያግዘናል፡፡ ከተንበዛበዘ ግን፣ ወደ ስልጡ ፖለቲካ የመራመድ እድልን በእንጩ የሚቀጭ በሽታ ይሆንብናል፡፡


Read 9058 times