Print this page
Monday, 03 February 2020 11:49

“የሙዚቃ ትርኢት ዝግጅቶች ፈራቸውን እየለቀቁ ነው”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    • በዓመት አንድ ጊዜ ታላቅ የባንዶች የሙዚቃ ውድድር ማዘጋጀት ይቻላል
               • ለቤተ መንግስት የሙዚቃ ዝግጅት የፕሮቶኮል ባንድ ማቋቋም ያስፈልጋል

       በባህልና ቱሪዝም በኩል ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ለሚመለከታቸው ክፍሎች ኃላፊነት ተሰጥቶ፣ ተቋሟት አካሄዳቸውንና አደረጃጀታቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያደርግ ሪፎርም ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሪፎርሙ ካልተካሄደ፣ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡


            አቶ አበበ ካሣ ይባላሉ፡፡ አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያ ናቸው፡፡ በቀድሞ የፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ክፍል ውስጥ ሲሰሩ፣ በውጭ አገር ለ8 ዓመታት፣ ከፍተኛ የሙዚቃ ሥልጠና መውሰዳቸውን ይናገራሉ፡፡ ወደ ሃገር በቤት ተመልሰውም በወታደራዊ የሙዚቃ ክፍሎችና በታላላቅ ሆቴሎች ውስጥ በሙዚቃ ባለሙያነት (ኤክስፐርት) ለረጅም አመታት አገልግለዋል:: በሆቴሎች ውስጥ በምን ሰአት፣ ምን ሙዚቃ መቅረብ አለበት? በታላላቅ መንግስታዊ ሥነስርአቶች ላይ የሚቀርቡ የሙዚቃ ትርኢቶች  እንዴት መዘጋጀት አለባቸው? የፕሮቶኮል ባንድ የሚባለው ምንድን ነው? በሚሉ ጉዳዮ ላይ ሠፊ ልምድና የአካዳሚ እውቀቱ እንዳላቸው የሚገልጹት አቶ አበበ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ በመንግስታዊ ታላላቅ ግብዣዎች ላይ የሚካሄዱ የሙዚቃ ትርኢቶች ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ በሙዚቃ ትርኢቶች ዝግጅት ዙሪያ አቶ አበበ ካሳን አነጋግሯቸዋል፡፡


             በታላላቅ ሆቴሎች የሚቀርብ ሙዚቃ የራሱ ስርአትና የአቀራረብ ቅደም ተከተል እንዳለው ነግረውኝ ነበር፡፡ እስቲ ያብራሩልን?
አንድ ሆቴል ደረጃውን የጠበቀ ነው የሚያስብለው የሙዚቃ ፕሮግራሞች አዘገጃጀቱ ነው፡፡ ሆቴሉ ናይት ክለብ ይኖረዋል፡፡ ፍሎርቪው የሚባል የ40 ደቂቃ የእራት ሙዚቃ ትርኢት፣ የባር ሙዚቃ … ይኖሩታል፡፡ እነዚህ የየራሳቸው የአሠራር ስርአት አላቸው፡፡ የአቀራረብ ቴክኒካቸውም ይለያያል፡፡ ለምሣሌ የእራት ሙዚቃን ስንመለከት፤ በጣም የማይረብሽ፣ ከሩቅ የሚሰማ እንዲመስል ተደርጐ ነው የሚከፈተው፡፡ ፒያኖ ባር የሚባለው የሙዚቃ አቀራረብ ደግሞ ሰዎች እየተወያዩ፣ እየተነጋገሩ፤ በጣም በወረደ ድምጽ የሚከፈት ነው፡፡ በፒያኖ ባር የሙዚቃ ቴክኒክ ላይ የመድረክ ዘፋኝም ሊካተትበት ይችላል፡፡ ናይት ክለብ ደግሞ ተዝናኞችን ሊያስደንሱ የሚችሉ ሙዚቃዎች ይከፈታሉ፡፡  ፍሎር ሾው የሚባለው፣ ሰው ራት ከበላ በኋላ በመጠጦች እየተዝናና የሚቀርብ ዝግጅት ነው፡፡ ዳንስ ማለትም እንደ ባሌት ባሉ ዳንሶች የታጀበ ወይም በኛ ሁኔታ የባህላዊ ሙዚቃዎች ውዝዋዜ ያላቸው አይነት… በድምፃውያን ታጅቦ የሚቀርብ ነው፡፡ ይሄ ለ40 ደቂቃ ብቻ የሚቀርብ ትርኢት ነው፡፡ ይሄን በእኛ ሀገር በተሳሳተ መንገድ፣ በታላላቅ ዝግጅቶች  ሳይቀር ራት እየተበላ ያቀርቡታል:: እንዲህ አይነት ዝግጅት የሚቀርበው ከእራት በኋላ ነው፡፡
ሆቴሎቻችን እርስዎ የሚሉትን የሙዚቃ አቀራረብ ሥርዓትና ቴክኒክ ይተገብራሉ ወይስ...?
ቴክኒኩ የለም፡፡ እኔም ይሄን እንድናገር ያስገደደኝ ይኸው ነገር ነው፡፡ ብዙ ታዝቤያለሁ፤ ቴክኒኩን በሚገባ የሚተግብር የለም፡፡ ይህ የሆነው ጠያቂ ባለሙያ በመጥፋቱ ነው፡፡ ሙያው ባለቤት አጥቷል፡፡ ቀደም ብሎ የነበሩ መሰል ዝግጅቶችን የሚያቀርቡ ቡድኖች ፈርሰው፣ ሁሉ ነገር ተበላሽቷል፡፡ በቲያትር ቤቶች ሳይቀር የሙዚቃ ዝግጅት የሚያቀርቡ ባለሙያዎች የሉም፤ ሙያዬ ብለው እየሠሩበት አለመሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ቲያትር ቤቶች ያን ያህል የተደራጀ የሙዚቃ ቡድን የላቸውም፡፡
በተቋማቱ ላይ የሚስተዋሉ ጉልህ ችግሮች ምንድን ናቸው?
ተቋማቱ፤ የሰው ሃይል አደራጅተው፣ የራሳቸውን ወጥ ሥራ በሚገባ ተለማምደው፣ ስርአቱንና ቅድመ ተከተሉን በጠበቀ መልኩ እየሰሩ አይደለም፡፡ ይሄ ደግሞ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሙያተኞችን በሚገባ ፈትኖ፣ መርጦ የመቅጠር፣ ከዚያም ሲያልፍ ጠንካራ ልምምድ የማድረግ ዝንባሌ እየቀረ መምጣቱን ያመላክታል፡፡ በአዲስ አበባ ባህልና ቢሮ በኤክስፐርትነት ስሰራ ያስተዋልኩት ይሄንን ነው፡፡ አሁን በቲያትር ቤቶች የሙዚቃ ትርኢቶች የሚቀርቡት፣ በጥቂት ቀናት የለብለብ ዝግጅት ነው፤ ስለዚህ ያን ያህል ማራኪ አይደሉም፡፡ ቀደም ሲል እኮ የምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ክቡር ዘበኛ፣ ብሔራዊ ቲያትር የመሳሰሉት የየራሳቸው ጠንካራ ተቋማት ነበራቸው፡፡ በመካከላቸውም ጠንካራ ውድድር ነበር፡፡ ይሄም በወቅቱ የሙዚቃ ዘርፉን አሳድጓል፡፡ አሁን ግን እንዲህ አይነት አሰራር የለም፤ ሙያው በባለሙያዎች እየተመራ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ነገሩ የተበላሸው፡፡ ለዚህ ነው በዘርፉ እድገት የሌለው፡፡
መፍትሔው ምንድን ነው ይላሉ?
መፍትሔው በአንድ ወይም በሁለት ሰው የሚመጣ አይደለም፡፡ በባህልና ቱሪዝም በኩል ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ለሚመለከታቸው ክፍሎች ኃላፊነት ተሰጥቶ፣ ተቋሟት አካሄዳቸውንና አደረጃጀታቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያደርግ ሪፎርም ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሪፎርሙ ካልተካሄደ፣ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡  
እርስዎ ይሄን ሃሳብ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት አቅርበው ነበር?
ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይሄን ጉዳይ ብዙ ጊዜ አሳስቤያለሁ፡፡ ነገር ግን ሚኒስትሮች ቶሎ ቶሎ የሚቀያየሩ በመሆኑ፣ አንዱ ሲሄድ ሃሳቡን ይዞት ይሄዳል፤ የመጣውም እንደ አዲስ ይሠማል፤ እሱም ሲሻር ይዞት ይሄዳል፤ እንደዚያ እየሆነ ነው እንጂ ደጋግሜ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቄአለሁ፡፡ አሁን ችግሩ፣ ሙያው ከባለሙያዎች ጋር  አለመገናኘቱ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን አንድ የሪፎርም ኮሚቴ ተቋቁሞ በፍጥነት መሠራት አለበት ባይ ነኝ፡፡  
የባንድ ሙዚቃን የምናጐለብትበት ትልቅ አቅም አለን፡፡ ግን አሁን እየተዳከመ ነው:: ለምን ከተባለ፣ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው፡፡ እንደ እኔ በዓመት አንድ ጊዜ ታላቅ የባንዶች የሙዚቃ ውድድር  ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ የሙዚቃ ማርሽ ባንዶች በስፋት ሊፈጠሩ የሚችልበት እድል ሁሉ አለ፡፡ ሁሉም የተዳከመው  በተዝረከረከና ትኩረት ባጣ የቸልተኝነት አሠራር ነው፡፡ ተቋማት በሰው ሃይል የተሟሉ አይደሉም፡፡ ይሄ ነው እኔን ያሳሰበኝና ሃሳብ እንዳቀርብ ያስገደደኝ፡፡
በቤተ መንግስት የሚቀርቡ የሙዚቃ ትርኢቶች ደረጃቸውን የጠበቁ አይደሉም ብለዋል፡፡ ከምን አንጻር ነው ይሄን የገመገሙት?
አዎ፤ አንዱ አስገራሚው ነገር እሱ ነው:: የሙዚቃ ትርኢቶች የሚቀርቡት እንደነገሩ ነው፡፡ በቤተ መንግስት በሚኖር ታላላቅ ግብዣ ላይ የሚቀርቡ ሙዚቃዎችና ሙዚቀኞች፣ በስታንዳርዱ መሠረት እጅግ የተከበሩ ፕሮፌሽናሎች መሆን አለባቸው:: የአፍሪካ መሪዎች ሲመጡ አብረዋቸው የየሀገራቱ ኮከብ ዘፋኞች መምጣትና ዝግጅት ማቅረብ አለባቸው፡፡ ትርኢቶች እስከዚህ ደረጃ ነው መዘጋጀት ያለባቸው፡፡  በቤተ መንግሥት የሚቀርቡት ላይም በአለባበስ፣ በፕሮፌሽናሊዝም በልምድ፣ በትርኢት አቀራረብ ቅደም ተከተል የማስተውለው ነገር ሁሉ የሚያሳፍርና ደረጃውን ያልጠበቀ ነው፡፡ ቀደም ሲል ክቡር ዘበኛ የተቋቋመው እንዲህ ያለውን ስራ ለመስራት ነበር፤ በእርግጥም የተሳካና ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ነበር የሚያቀርበው፡፡ ጥንቁቅና ስርአቱን የጠበቀ ሥራ ሲቀርብ፣ የሀገር ክብርና ገጽታ ክፍ ይላል፡፡  
ይሄ እንዴት ሊመጣ ይችላል?
ከተቻለ የፕሮቶኮል ባንድ ለቤተ መንግስት ዝግጅት ብቻ ተቋቁሞ መስራት አለበት:: ካልተቻለ ደግሞ የአመቱ ምርጥ የሚባሉ ባንዶች አመቱን ሙሉ ይሄን የፕሮቶኮል ስራ እንዲሠሩ ሙሉ ኃላፊነት መስጠት ይቻላል፡፡ በእነዚህ ሁለት መልኩ ሊሠራ ይችላል፡፡ አሁን  በቤተ መንግስት የሚቀርቡ የሙዚቃ ትርኢቶች  ፈጽሞ ደረጃቸው የጠበቁና የቅደም ተከትል ፕሮቶኮልን ያሟሉ አይደሉም፡፡

Read 1640 times