Monday, 03 February 2020 11:53

‹‹ጠበኛ እውነቶች›› ወይስ ‹‹ጠቢበኛ እውነቶች››?

Written by  ጥላሁን አበበ (ወለላው) tilahun.ab23@gmail.com
Rate this item
(1 Vote)

  “በኔ ስሜት ይህ ነው የሜሪ ፈለቀ መፅሐፍ፡፡ ‹‹ጠበኛ እውነቶች›› ለኔ የተሰማኝ እንዲህ ነው፡፡ አንባቢያን ደግሞ ብዙ ሌሎች ስሜቶች እንደሚፈጥርባችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሌላ እርግጠኛ የሆንኩት ግን ማንም ሰው ማንበብ ያለበት መፅሐፍ መሆኑን ነው፡፡” ‹ብሩህ ነገ› የሚባል ቀን የለም፡፡ ማንም ቢሆን ነገን ኖሮ የሚያውቅ የለም፣ ምክንያቱም፣ ‹ነገን› መኖር ስንጀምር ‹ዛሬ› ተብሏል፡፡ …[ይልቅ] ‹ብሩህ ቀን›
በእጃችን ያለው ‹ዛሬ› ነው፡፡››
              ጥላሁን አበበ (ወለላው) This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.


                 ለወትሮ ሰው በጻፈው መፅሐፍ ላይ እንዲህ ሰፋ ያለ ሃሳብ ሰጥቼ አላውቅም፣ ምናልባትም እንደ ማንም አንባቢ ጠቅለል ያለ አመለካከቴን ማካፈል ካልሆነ በስተቀር፡፡ በመፅሐፍ ላይ ዝርዝር ሃሳብ ወይም ዳሰሳ ማቅረብ፣ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ተግባር ነው ብዬም አምን ነበር፡፡ ነገር ግን ሙያዊ አስተያየት መስጠትና፣ የግል አረዳድንና ስሜትን በራስ ቋንቋ እንደ ወረደ መግለፅ፣ የተለያዩ አቀራረቦች እንደሆኑ የተከሰተልኝ ይህንን ‹‹ጠበኛ እውነቶች›› የተሰኘውን የደራሲ ሜሪ ፈለቀ፣ መፅሐፍ አንብቤ ስጨርስና፣ የተሰማኝን ስሜት ለማጋራት ብዕሬን ሳነሳ ነው፡፡
ስለዚህ ይህ ዳሰሳ፣ ልክ መፅሐፉን አንብቤ ከጨረስኩ በኋላ የተሰማኝን አሁናዊ (Immediate) ስሜትና የግል አረዳዴን የሚገልፅ ነው ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሌላ አንባቢ ደሞ፣ የራሱ ወይም የኔን የሚጋራ ግንዛቤ ይኖረው ይሆናል፡፡ ገና ከጅምሩ በመፅሐፉ ሽፋን ላይ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፣ በትልልቁ የተፃፉ ፊደላት እይታህን ከወሰዱት፣ በሙሉ አካል፣ ነገር ግን ባነሰ ቁመት የተፃፈን ድብቅ ፊደል ቀርቶ፣ በአንድ ፊደል ስር የተሰነቀረች ኢምንት የፊደል ተቀጥላን ምልክት ላታስተውል ትችላለህ፡፡ እንዲህ ያልኩህ እኔ ያየሁትን አንተም አላየኸውም ለማለት ሳይሆን፣ የአንዲት ቅጥያ ስንጥር፣ ወይም በትንሹ የተፃፈች አንዲት ፊደል፣ ስለ መፅሐፉ ያለህን ሙሉ ግምትንም ሆነ ትርጉምን እንደሚያፋልስ የገባኝና የመፅሐፉን የመጀመሪያ ክፍል ታሪክ ከጨረስኩ በኋላ፣ ሃሳቡን ከመፅሐፉ ርዕስ ጋር ለማዛመድ፣ በድጋሚ ሽፋኑን ባስተዋልኩ ወቅት ስለሆነ ነው::
ሜሪ ከጅምር እስከ ጭርስ ድረስ በተቀኘችባቸው፣ በአንድ ዘውግ ውስጥ ባሉት አራት የተለያዩ ትርክቶች፣ የደቦና የፊት ለፊት አመለካከት ብቻ፣ ብዙ ጊዜ ትክክል እንዳልሆነ የምትነግርህ በርዕሱ ስዕላዊ ቅኔ ይመስለኛል:: ‹ምናልባት እኔ እዚህ ስዕላዊ ቅኔ ላይ የታየኝ ነገር፣ ደራሲዋ አውቃ ያደረገችው ምስጢር ይሁን ወይም አይሁን አላውቅም፡፡› ነገር ግን የመፅሐፉ ጥልቀትና ረቂቅ ፍልስፍና እንዲህ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡
ነገሩ ወዲህ ነው…
የፊት ሽፋኑ ላይ ያለውን የመፅሐፉን ርዕስ አይኖችህን አጮልቀህና ግንባርህን ጨምድደህ በአትኩሮት ካላየኸው የሚነበበልህ ፊደል በትልቁ የተጻፈው ‹‹ጠበኛ እውነቶች›› የሚለው ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በርዕሱ ላይ ‹‹ጠበኛ..›› ከምትለዋ ቃል ውስጥ በተለየ ሁኔታ ‹‹በ›› የምትለው ፊደል የግራ እግር ውስጥ፣ ‹‹እ›› ከምትለዋ የታችኛው ፊደል አናት ጋር የተሰፋች ‹‹ቢ›› የምትል በነጭ የተፃፈች ፊደል ታገኛለህ:: ያኔ… ‹‹ጠበኛ›› ለምትለው ቃል፣ ሁለተኛ አናባቢ እንዳላት ትረዳና፣ ‹‹ጠቢበኛ›› የሚል አማራጭ ቃል ይነበብሃል፡፡ እኔም ገና ጀምሬ፣ በጠበኛ እውነቶች ውስጥ ጠቢበኛ እውነቶች አሉ ለማለት የፈለገች ወይም ጠበኛ እውነቶችን በጠቢበኛ እውነቶች የምታስታርቅበት አውድ አለ ማለት ነው ብዬ አሰብኩ፡፡
ሜሪ ፈለቀ፤ በጠበኛ እውነቶች መፅሐፏ፣ አራት ደሴቶች ወስዳ ትሰቅዝሃለች፡፡ ከዚህ ቀደም በሁለት ፅንፍ ተወጥረህ የተጠራጠርከውን ነገር፣ አንዱን ከአንዱ ጎራ አስገብታህ ታረጋግጥልሃለች፣ አሊያም የራስህን ጎራ ፈጥረህ ከራስህ ጋር እንድትታረቅ ታደርግሃለች፡፡ ከጠበኛውም ሆነ ከጠቢበኛው እውነት ጋር ሳትወድ በግድህ ትጠርቅሃለች፡፡
ለኔ ጀግና ከምላቸው ፀሃፍት ውስጥ ፓውሎ ኴልሆን (Paulo Coelho) ታውቀው ይሆናል፣ ቢያንስ በሰፊው በሚታወቀው ዘ-አልኬሚስት የተሰኘ ድርሰቱ፡፡ ፓውሎ ካሳተማቸው ወደ ሃያ የሚጠጉ መፅሐፍቶቹ ውስጥ Eleven Minutes, Alef, እና Adultery የተሰኙትን ለዋቢነት ልጥቀስልህ፡፡  ከኛው ጀግና ደራሲ ደግሞ የስብሃትለአብ ገ/እግዚአብሔርን ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ››ን ለናሙና እንውሰድ፡፡
ሁለቱም የግሌ ጀግና ያልኳቸው ደራሲያን፣ ሥነ-ፆታና ወሲብ ነክ ተረኮችን ከማህበረሰባዊ ውግዘት ወይም (taboo) በላቀ ከፍታ ‹‹ከማንነት እና ከስነልቦናዊ ስብዕና›› ጋር አጣምረው ባንተነትህ ላይ ያለውን ተፈጥሮአዊ ተፅዕኖ በማትክደው መንገድ ያስረዱሃል፡፡
እዚህ ጋ ‹‹ጠበኛ እውነቶች››ን ከሌሎች ስራ ጋር በደረጃ መድቤ እያነፃፀርኩ አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ዘውግ ደረጃ በሃገራችን ስነፅሁፍ (ከስብሃት በኋላ ሌሎች የደፈሩት ዘውግ መሆን አለመሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ባልችልም) ደራሲ ሜሪ ፈለቀ ግን ከላይ እንደጠቀስኳቸው ሁለት ደራሲያን፣ በግሩም አገላለፅና ፍልስፍና፣ ሽፍንፍንህን ትገልፅልሃለች፡፡ አንተው ከኖርከው ወይም ከመሰከርከው ታሪክ ሃዲድ አንዲትም ሳትወጣ አይንህን በልጥጠህ፣ ሳታምንበት የተጣላኸውን፣ ከራስህ በግድ የተካካድክበትን የገዛ እውነትህን ጠቅልላ ታጎርስሃለች፡፡
ጠበኛ እውነቶች፣ በአንድ ተመሳሳይ ዘውግ (ውቅያኖስ) የተቃኘ ሲሆን በውስጡ አራት አጫጭር ታሪኮች (ደሴቶች) አሉት፡፡ እናም እነዚህ አራት ደሴቶች ላይ ነው የግሌን ምልከታ ወይም ዳሰሳ የምገልፅልህ፡፡ ደግሜ እንደምለው፣ አንብበህ ስትጨርስ ደግሞ አንተም ያንተ ይኖርሃል፣ ወይም በከፊል ከኔ ምልከታ ጋር ትስማማለህ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
 የመጀመሪያው ደሴት፡ ‹‹ቅዳሴና ቀረርቶ››
በዚህኛው የመጀመሪያ ደሴት፣ ደራሲ ሜሪ ባንቺን ትሰጥሃለች፡፡ በሷ ታሪክ ውስጥ በማህበረሰብ ሚዛን የተቀመጠ ግዙፍ እውነት፣ ብዙ ጊዜ ከጥጥ ክምር የተሰራ ራስን የማታለል ትልቅ ተራራ እንጂ፣ በእጅህ የምትጨብጠውና ከባድ የሆነ ሃቅ እንዳልሆነ ትነግርሃለች፡፡ ቅዱስ መፅሐፍ እንደሚያስተምረው፤ ‹በሰው ላይ ያለ ጉድፍ የምታክል ስህተት ከማንሳትህና ከመፍረድህ በፊት፣ በገዛ አይንህ ላይ እንደ ምሰሶ የተገተረውንና የካድከውን ትልቅ ግድፈት› ማየት እንዳለብህ ብዙም ሳትቸገር ትተርክልሃለች፡፡
በተጨማሪም፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለታይታም ይሁን አምነህበት፣ መቼም ቢሆን የማይናወጥ መርህ እንዳለህ ምንም ያክል ብንዘበዝብም፣ ምንም ያክል ብትታገለውም፣ በሁለት የተጣረሱ ገፀ ባህርያትና የተገፋፉ እውነቶች ትርክት ውስጥ ሃቁን ትነግርሃለች:: ሃቁ ደግሞ፣ ሁላችንም በሆነች ቀን፣ በሆነች ቅፅበት፣ ወይም በሆነች ክስተት፣ ለዘመናት የነበረንን የይስሙላ ወኔ ክደን፣ ለትክክለኛው ሃቅ የምንሰበርበት ኩርባ ወይም ነጥብ (Breaking Point) እንዳለ ትነግርሃለች:: ያኔም ወደ ራስህ ትመለከትና ራስህን በርግጥም በብዙ እጥፋቶች፣ ኩርባዎችና ስብራቶች መካከል ታገኘዋለህ:: ሰዎች ተሳስተሃል ቢሉህም፣ ላንተ ግን በጣም ትክክልና በጎ የነበሩ ስብራቶችህ ትቆጥራቸዋለህ፡፡
ወደህም ሆነ ተገደህ… ወደ ኋላህ ወይም ወደ- አሁንህ እውነታ ትመለሳለህ፡፡ እናትህን ታያለህ… እህትህን ታያለህ፡፡ በመንጋ እምነት የወነጀልከውን ነፃ ታወጣለህ፣ በመንጋ እምነት ያቀፍከውን ትጠየፋለህ፡፡ ባጭሩ፣ ገና በመጀመሪያው ደሴት ከራስህ ትታረቅና፣ ቀጣዮቹን ሶስት ደሴቶች ለመጎብኘት ቀጠሮ ሳትሰጥ፣ ወዲያውኑ ጉዞህን ትቀጥላለህ… የመጨረሻውን ገፅ ገልጠህ የምታነብበው ስታጣ ነው፤ ይህን ያልኩህን ምትሃት የምታምነው፡፡
ሁለተኛው ደሴት፡ ‹‹ቀላውጦ ማስመለስ››
በዚህኛው ደሴት ላይ ደራሲዋ፣ ‹‹ወለላ›› ብላ በሰየመቻትና በአካል የምታውቃት የምትመስልህ ገፀ-ባህሪ፣ በአጫጭር የሶስትዮሽ ወግ አንዳች ምስቅልቅል ያለ ምስጠት ውስጥ ትከታለች፡፡ በፊልም ዘውግ ልብ አንጠልጣይ (Thriller)፣ ወንጀል (Crime)፣ ፍቅር (Romance) ድራማ እንደሚባለው፣ ሁሉንም በታሪኮቿ ውስጥ አስተሳስራ፣ አንባቢዋንም ከመፅሐፉ ጋር ቋጥራ ትይዛለች፡፡
የሲግመንድ ፍሩድን ፍልስፍና በቁንፅልም ቢሆን የምታውቅ ከሆነ፣ እሱ በአምስት የዕድሜ (የዕድገት) ደረጃ ከፋፍሎ ካስቀመጣቸው የፆታ-ስነልቦና (Psychosexual) መደቦች መካከል፣ በተለይ 4ኛው ደረጃ ላይ ማለትም ከ6 ዓመት እስከ ጉርምስና (Latent Period) የሚለው ላይ በሚፈጠር ማንኛውም ስነ-ፆታዊም ሆነ ወሲባዊ ጥቃት የሚከሰተው የህሊና ደዌ (Fixation)፣ ምን ያክል የሰውን ልጅ ህይወት ምስቅልቅል ውስጥ እንደሚከት በህያው አስረጅ ታሳይሃለች:: ይህ ጉዳት ፍሩድ በ5ኛ ደረጃ ካስቀመጠው ማለትም ከጉርምስና እስከ ሞት ድረስ (Genital Stage) ያለውን የህይወት ዘመንህን ዜማ እንዳሻው እየቃኘ እንደሚወስድህ ታሳይሃለች፣ እስከ መጨረሻዋ የእስትንፋስህ ፀጥታ ድረስ፡፡
በዚህ ደሴት በሰደረችው ሶስት ጉልቻ ወይም የሦስትዮሽ ወግ፣ ለየትኛው እንደምትወግን ግራ እስኪገባህ ሃይለኛ ጡዘት ውስጥ ትከትሃለች:: አሁን የተናደድክበትን ቀጥሎ ታዝንለታለህ፣ አሁን ያዘንክለትን ቀጥሎ ትናደድበታለህ፣ የገፀ ባህርይዎቿን ታሪክ፣ ደስታና ሃዘን… ክፋትና ደግነት… ሞኝነትና ብልጠት… እርካታና ፀፀት… ወዘተ፣ ወዲህ እያፋቀረች… ስትፈልግ እያዋሰበች… ሲሻት እያናቆረች፣ ከልጅነት እስከ እውቀት ድረስ ያለውን የሰው ልጅ ህይወት በሶስት ጉልቻ ጥዳ ታንተከትከዋለች፡፡
ያንተ ድርሻ የተጣደው የበሰለ የመሰለህ ሰዓት ላይ እንዳሻህ መቅመስ፣ መጭለፍ፣ ወይም ዝም ብለህ ማብሰል ነው፡፡ በዚህ ደሴት ከህይወትና ሞት ፅንፍ ይልቅ፣ በህይወት ጅማሬና በህይወት ማማ ላይ ያለውን ሰማይ ጠቀስ ርቀት ታሳይሃለች፣ ከዚያም ትቀጥልና ደግሞ በህይወት የመጨረሻ አፋፍ ላይ እና በሞት ጅማሬ መካከል ያለችው ኢምንት ድልድይ ላይ ታፈናጥጥህና፣ በዚያች ቅፅበት ውስጥ ያለውን እውነታ ልብህን ሰቅዛ፣ ከራስህ የህይወት ተሞክሮ ሳትርቅ፣ ከገዛ ኑሮህ ጓዳ ቀድታ ታጠጣሃለች፡፡
ማንም ሰው ያለ አንዳች ምክንያት ደግም… ክፉም፣ ደደብም… አዋቂም፣ ሴሰኛም… ሱሰኛም፣ ነፍስ ታዳጊም… ነፍሰ-ገዳይም፣ ቅዱስም… ኃጥዕም ወዘተ… እንደማይሆን፣ በ3 ጉልቻ የጣደችልህን የትርክት ወጭት በመጨረሻ አውርደህ ስትከፍተው ታሳይሃለች:: ከዚያም እስከ ዛሬ በማንም ላይ በግልህ የወሰድከውን ችኩል ሚዛንና ፍርድ፣ ወይም በማህበረሰባዊ አመለካከት ግፊት የተቀበልከውን መንገኛ አመለካከት፣ ሁሉንም በድጋሚ እንድትከልሰውና እንድታስተካክለው ትሞግትሃለች፡፡ ያኔ በእርግጠኝነት ብዙ ህያው የራስህ ትዝታዎች፣ ሰዎች፣ አመለካከቶች፣ እውነቶች ወዘተ እየተግተለተሉ ለተወሰነ ጊዜ ከራስህ ጋር እንድትነጋገር ያደርጉሃል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ለኔ የተሰማኝ በእርግጠኝነት ይህ ነበርና፡፡
ሶስተኛው ደሴት፡ ‹‹እናቴን ተመኘኋት››
በዚህችኛዋ አነስተኛ ደሴት ላይ ስታደርስህ ደግሞ፣ አንተ በተፈጥሮህና በራስህ አዕምሮ ያመንክበት ፍቅር የሚሉት ነገር፣ ወይም አንተ ያመንክባትና በነፍስህ ያነገስካት እውነተኛ ፍቅረኛህ፣ የትኛዋ እንደሆነች በአንደኛው የእውነት ፅንፍ ላይ ታስቀምጥልሃለች፡፡ በመቀጠል ደግሞ ማህበረሰብ፣ ባህል፣ ሃይማኖት ወዘተ የመረጠልህንና ያፀደቀለህን ፍቅርና ፍቅረኛ፤ በሌላኛው ማህበረሰባዊ የእውነት ፅንፍ ላይ ታስቀምጥልሃለች፡፡ ከዚያም እነዚህን ሁለት እውነቶች ጠበኛ፣ ህሊናህን ደግሞ የፍልሚያው አውድማ አድርጋ ታሰጥሃለች፡፡ ዳኝነቱንና አሸናፊውን መለየቱ ያንተ ስራ ነው፡፡ ይህን ደግሞ ብዙም ሳትርቅ በኮማሪቷ ታሪክ፣ የወይን-እሸት የሆነ ታሪክ ታስሸመጥጥሃለች፡፡ ያኔ ወደድክም ጠላህም ነፍስ ካወቅክበት፤ ቅፅበት ጀምሮ በነፍስያህ የታተመችውን ፍቅርህን ታውቃታለህ፡፡
ከዚህ በተለየ ደግሞ ይቺ ደሴት፣ ከላይ ካልኩት ታሪክ ባሻገር ለኔ ዘለግ ያለ ግሩም ‹‹ግጥም›› እንደሆነች አድርጌ ነው የተረዳኋት:: ይቺ አጭር ደሴት በሌላ ምስል የገዛ ሃገሬን፣ በውስጤ የሳልኳትን፣ የማምንባትን ኢትዮጵያዬን በግሩም ቅኔ የገለፀችውም መስሎኛል፡፡ እናንተም ወይ ተመሳሳይ ወይ ደግሞ ሌላ ቅኝት ታገኙበትም  ይሆናል… ማን ያውቃል!?
አራተኛው ደሴት፡ ‹‹ምርጫ አልባ ምርጫ - ከረቂቅ እስከ በረከት››
ይህ ደሴት ማሳረጊያህ ነው፡፡ በሶስቱ ደሴቶች ስትዋልል የቆየችው ጀልባህ ማረፊያ፣ ወደ የብስ መገናኛህ፣ ወደ ህያው ኑሮህ መሸጋገሪያህና መልህቅህን ጥለህ፣ ከራስህ የምትታረቅበት ወደብ ነው፡፡ እዚህ ወደብ ላይ ነው ደራሲዋ በብዙ ‹‹ረቂቅ በረከቶች›› የምትዘንብብህ፡፡ የዚህን ወደብ ጉብኝት ስትጨርስ በሃገርኛው ልሳን እጅህን በአፍህ ጭነህ ‹‹ወቼ ጉድ›› ትላለህ፣ ወይም በእንግሊዝ አፍ ‹‹ዋው…!›› ማለትህ አይቀርም፡፡  በዚህኛው ፅንፍ ምርጫ ሰጥታ ምርጫ ትነሳሃለች፡፡ በዚያኛው ፅንፍ ደግሞ ምርጫ ነስታህ ምርጫ ትሰጥሃለች፡፡ ሁለቱንም ፅንፎች በህያው እውነቶች ትጀቡንብህና ጠበኛ እውነቶች ታደርግብሃለች፡፡
‹‹በረቂቅ›› ተረኳ ውስጥ፣ ‹‹ስለ…›› ብለህ ስትኖር… ‹‹እኔ…›› የሚለው ይጎትትሃል… ‹‹እኔ…›› ብለህ የምታደርገውን ‹‹ስለ…›› የሚለው ሌላኛው አንተነትህ ይከነችርሃል፡፡ በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ፣ ብዙ ምርጫ ባለበት ሽሬታ አንዱንም ሳትሸምት ልትመለስ ትችላለህ፣ ወይም ምንም ምርጫ በሌለበት አውላላ ብዙ ምርጫ ሽረህ ልትመጣ ትችላለህ፡፡ ወደድክም ጠላህም፣ አንተ ያላስተዋልከው የምርጫ ሚዛንህ ያጎነበሰው ‹‹ትናንት/ ትዝታ›› ወይም ‹‹ዛሬ/ አሁን›› ወይም ‹‹ነገ/ ተስፋ››… ከሚሉት ሶስት ሁነቶች የሚወጣ ሊሆን አይችልም ትልሃለች፡፡ ምርጫው ግን ያንተ ነው…!
‹‹በበረከት›› ስትቋጭህ ደግሞ በብዙ መንገድ ማጣፊያ ያጣህለትን የገዛ ህሊናህን ዳግም ታጥበዋለህ ወይም ታጨቀየዋለህ፡፡ አማኝ ከሆንክና በፈጣሪህ ጥበብ የተደነቅከውን ያክል፣ ያመሰገንከውን ያክል፣ ለአፍታም ቢሆን ከፈጣሪህ ጋር ሙግት ትገባለህ፡፡ ኦሪት ላይ ያነበብከው የኢዮብና የሚስቱ ታሪክ ውልብ ይልብሃል፡፡ በስጋ አመለካከትህ፣ ኢዮብ ነኝ ያልከው ሰውዬ፣ በሆኑ ቅፅበቶች ራስህን የኢዮብን ሚስት ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ፣ ሰው መሆንህ ይፈትንሃል፡፡ በመንፈስ አይንህ ደግሞ፣ ብዙ በረከቶችን ታያለህ፣ በረከትነታቸውም ከስም ባሻገር በብዙ መለኮታዊ ምስጢራት ይገለፁልሃል፡፡
ይህቺኛዋን ደሴት ስትጨርስ በአንድ በኩል የትኛውን ጠበኛ እውነት እንደመረጥክ ሳታውቀው ግን ከሰጠችህ እውነቶች አንዱን ‹‹ጠቢበኛ እውነት›› ይዘህ፣ ወይም ደግሞ የራስህ የሆነ አንዳች ‹‹ጠቢበኛ እውነት›› ሰንቀህ መፅሐፍህን ትዘጋዋለህ፡፡  
መፅሐፏንም ስትቋጨው የመጨረሻው ገፅ ላይ እንዲህ ትልሃለች…
‹‹ብሩህ ‹ነገ› የሚባል ቀን የለም፡፡ ማንም ቢሆን ነገን ኖሮ የሚያውቅ የለም፣ ምክንያቱም፣ ‹ነገን› ለመኖር ስንጀምር ‹ዛሬ› ተብሏል፡፡ …(ይልቅ) ብሩህ ቀን በእጃችን ያለው ‹ዛሬ› ነው፡፡››
በኔ ስሜት ይህ ነው የሜሪ ፈለቀ መፅሐፍ:: ‹‹ጠበኛ እውነቶች›› ለኔ የተሰማኝ እንዲህ ነው:: አንባቢያን ደግሞ ብዙ ሌሎች ስሜቶች እንደሚፈጥርባችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሌላ እርግጠኛ የሆንኩት ግን ማንም ማንበብ ያለበት መፅሃፍ መሆኑን ነው፡፡  
ከመጨረሴ በፊት ግን ‹‹ምናልባት ለወደፊቱ የተሻለ ስራ ግብዓት ይሆናታል›› ያልኩትን ምክረ-ሃሳብ ሳልናገር አልወጣም፡፡
ደራሲዋ የመጀመሪያ በሆነው የህትመት ስራዋ፣ አራት አጫጭር (ከፊል መካከለኛ) ታሪኮችን በመምረጥ መጥታለች፡፡ አጫጭር ታሪኮችን መፃፍ ራሱን የቻለ ዓለም-አቀፍ የስነ-ፅሁፍ ዘውግ እንደሆነም አውቃለሁ፡፡ የደራሲዋም የግል መብትና ውሳኔም እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን ይህ ምርጫዋ፣ ማለትም በአራት አጫጭር ታሪኮች መከሰቷ፣ በእርግጥ ‹‹ደራሲዋ ወደ ህትመት ውሳኔ ከመምጣቷ በፊት ጀምሮ የነበረ ነው ወይስ ወደ ህትመት ውሳኔ ስትደርስ በአስገዳጅ ሁኔታዎች የቀየረችው ነው?›› የሚለው ነገር ትንሽ ጥርጣሬን ፈጥሮብኛል:: ጥርጣሬዬን የፈጠረው ደግሞ በተለይ ሶስቱ ታሪኮች (ክፍሎች) አጠቃላይ ስሜታቸውን ስረዳ፣ ‹እያንዳንዳቸው ራሳቸውን የሚችሉ አንድ ረጅም ልብወለድ ድርሰቶች መሆን የሚችሉ› ሆነው ተሰምተውኛል፡፡ በተለይ አንዳንድ ሰፊ ትርክት ይኖራቸዋል ብዬ የጠበቅኳቸውን ታሪኮች በጣም ባጠረና፣ በተጠቀለለ መንገድ ያለፈችባቸው ሁነት፣ ታሪኩን በግድ ለማሳጠር የተገደደች እንዲመስለኝ አድርጎብኛል፡፡
ይህን ያልኩበት ምክንንያት በቀጣዮቹ ግላዊ ስሜቶች ወይም ግምቶች በመነሳት ነው፡-
ደራሲ ሜሪ ፈለቀ ለብዙ ዓመታት ብዙዎቻችን የምናውቃት በተለይ ፌስቡክ ላይ በምትፅፋቸው አጫጭር ልብወለዶችና ተረኮች ነው፡፡ የፌስቡክ አውድ ደግሞ፣ በጣም በዛ ከተባለ ለተከታታይና አጫጭር ለሆኑ ፅሁፎች እንጂ፣ ለረጅም ልብወለድ የሚሆን አይደለም፡፡ ከዚህም በመነሳት፣ ለዘመናት በፌስቡክ አምድ ላይ ካሳለፈችው ተመክሮ አንፃር፣ በዚህ መፅሐፍ ላይ የፃፈቻቸው ታሪኮች መርዘም እየቻሉ፣ ነገር ግን በልምድ ተፅዕኖ የተነሳ በግድ ያሳጠረችው እንዳይሆን የሚል ግላዊ ስጋት…
በተወሰነ መልኩ፣ ከላይ እንዳልኩት፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ታሪኩ በፍጥነት የታጠፈበት ሁነት፣ ፅሁፉ ጅምር ስራው ከፊልም ስክሪፕትነት ወደ ህትመት የተለወጠ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ ልክ ፊልም ላይ አንዳች የኋላ ታሪክን (Flashback) አጠር አድርገው በትርክት መሃል እንደሚመስሉት አይነት…
እንደ ማንኛውም የመጀመሪያ ስራውን ለህትመት ያበቃ ጸኃፊ፤ ‹ሰዋዊ ፍርሃት ወይም ስጋት ውስጥ ገብታ ይሆን እንዴ በራሳቸው ወጥና ረጅም ልብወለድ ሊሆኑ የሚችሉ ታሪኮችን አሳጥራ ያቀረበችው…?› የሚለውም ሌላኛው ግላዊ ስሜቴ ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ፣ እኔ ከላይ ካልኳቸው ሶስት ግላዊ ስሜቶቼም ሆነ ‹‹ከሌላ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ ነበርኩ… ፅሁፎቹም ከፅንሰታቸው ጀምሮ እስከ ህትመታቸው ድረስ እንዲህ እንዲሆኑ የታቀዱ ወይም በሂደት ሆነው የተፈጠሩ ነበሩ›› ብላ ደራሲዋ ካመነች ደስ ይለኛል፡፡ ከሷ በላይ ማንም በእርግጠኝነት ሊያውቅ አይችልምና፡፡ በመጨረሻም፣ ‹‹ጠበኛ እውነቶች›› ከገጣሚ ያሬድ ጌታቸው ‹‹መባቻ›› የተሰኘ የግጥም መድበል ጋር በመጪው ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም በራስ ሆቴል ከምሽቱ 12፡00 ላይ ይመረቃል፡፡ አዳራሹ ለማንም ሰው ክፍት መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡
እንዲህ ያሉ ትንታግ ደራሲያንን ያብዛልን…!
እንደ ሜሪ ፈለቀ ያሉ ሴት ደራሲያንን ያብዛልን…!
ሃገራችንን ኢትዮጵያን ሰላም ያድርግልን…!


Read 2177 times