Monday, 03 February 2020 11:54

“ከሙዚቃ ውጪ ራሴን ማሰብ አልችልም”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

   ከሰሜን ሸዋ ገጠራማዋ አካባቢ መዘዞ፣ ነው የተመዘዘው፡፡ በልጅነቱ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ከሙዚቃ ጋር የተዋወቀው ት/ቤት ውስጥ ነው፡፡ በተለያዩ ክለቦችና የሙዚቃ ባንዶች ሲሰራ ቢቆይም ይበልጥ ዕውቅናና ተቀባይነት ያገኘው በ“ባላገሩ አይዶል” ተወዳድሮ በማሸነፉ ነው፡፡
ከአራት አመት ሥራ በኋላ በቅርቡ ለአድማጭ ያደረሰው “የኔ ዜማ” አዲስ አልበሙ ተወዳጅና አነጋጋሪ ሆኖለታል፤ የዛሬው እንግዳችን ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከሙዚቃ ጅማሮው አንስቶ አሁን እስካለበት ደረጃ ደረጃ ያሳለፈውን ጉዞ አስመልክቶ አነጋግራዋለች፡፡ እነሆ፡-
                            

            አድማጭ ስለ አልበምህ ምን እያለ ነው?
አስተያየቱ በጣም ደስ የሚል ነው፡፡ እኛ ለረዥም ጊዜ ሥራው ላይ ስለከረምን፣ ከሰው ተራርቀን ነበር፡፡ አልበሙ በተለቀቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ እየደረሰኝ ያለው አስተያየትና አቀባበል ግን ከጠበቅነው በላይ ሆኗል፡፡
‹‹ባላገሩ አይዶል››ን ከመቀላቀልህ በፊት የነበረህ የሙዚቃ ሕይወት ምን ይመስላል?
ድምፄ ለሙዚቃ እንደሚሆን ያወቅሁት… በት/ቤት ቆይታዬ በወላጆች ቀንና በመሳሰሉት ስሳተፍ ነበር፡፡ አስተማሪዎቹም ተማሪዎቹም ለኔ የተለየ አስተያየት ነበራቸው፡፡ ድምፄ በጣም ቆንጆ እንደነበር ይነግሩኝ ነበር፡፡ ሙዚቃን ሥራዬ ብዬ በደንብ የጀመርኩት፣ በ2001 ዓ.ም ደብረ ዘይት አየር ሀይል ውስጥ ሥራ ከተቀጠርኩ በኋላ ነው፡፡
አየር ሀይል ከመቀጠርህ በፊትስ?
ተወልጄ ያደግሁት ሰሜን ሸዋ አካባቢ በሚገኝ መዘዞ የተባለ ገጠር ውስጥ ነው፡፡ በ3 ዓመቴ ነው አጎቴ ጋር መጥቼ ያደግሁት፡፡ እስከ 15 ወይም 16 ዓመቴ ድረስ ከአጎቴ ጋር ከቆየሁ በኋላ፣ ራሴን ችዬ መኖርና መንቀሳቀስ ጀመርኩ::
ዳዊት ጽጌ በሚለው ስምህ ነው የምትታወቀው፡፡ ጽጌ ግን የ“አጎት”ህ ስም መሆኑን ሰምቻለሁ። በእኛ አገር ባህል የአባት ስም በቀላሉ አይለወጥም፡፡ እስኪ ስለዚህ ጉዳይ አጫውተኝ?
እውነት ነው፤ ‹‹ጽጌ›› የአጎቴ ስም ነው፡፡ ከልጅነት ዕድሜዬ ጀምሮ አጎቴ ጋ ስላደግሁ፣ በአጎቴ ስም ነው የምጠራው፡፡
እንዳልኩህ በአገራችን የአባትን ስም በቀላሉ መለወጥ ወይም መተካት አይቻልም፡፡ በተለይ በገጠሩ አካባቢ ወግ አጥባቂነቱም አለ፡፡ ወላጅ አባትህ በወንድማቸው ስትጠራ ቅር አልተሰኙም?
ምናልባት በልጅነቴ ስለመጣሁና አጎቴም ሁለት ሴት ልጆች ስለነበሩት፣ የእነሱ ወንድም ሆኜ በስሙ እየተጠራሁ እንዳድግ በመፈለጉ ሊሆን ይችላል፡፡ የመዝገብ ስሜም ዳዊት ጽጌ ነው፡፡ አጎቴ ጋ ለ15 ወይም 16 ዓመታት ስኖር፣ አባቴን የማየት አጋጣሚ አልነበረኝም:: ይሄ ለምን ሆነ? የሚለውን ነገር የማውቅበት አጋጣሚ አልነበረኝም፡፡ ይሄ ሁሉ ካለፈ በኋላ ግን ከቤተሰቤ ጋር ተገናኝቻለሁ፡፡ እዚህም ይመጣሉ፡፡ ነገር ግን በጽጌ በመጠራቴ፣ በቤተሰቤ መካከል የተፈጠረ መጥፎ ነገር የለም::
ቀደም ባለው ትውልድ ሙዚቀኛ መሆን የሚያስመሰግን ሳይሆን የሚያስገፋ ሙያ ነበር፡፡ ‹‹አዝማሪ›› የሚለው መጠሪያ እንዳሁኑ መከበሪያ ሳይሆን ማፈሪያ ተደርጎ ይወሰድ ነበር:: ብዙ ቤተሰብም ልጁ ሙዚቀኛ ወይም አዝማሪ እንዲሆን አይፈልግም ነበር፡፡ አንተ ወደ ሙዚቃ ስትገባ ይህ አይነት ፈተና አልገጠመህም?
ኦ! በጣም ከባድ ነበር፡፡ የኔን ቤተሰብ ደግሞ ከባድ የሚያደርገው፣ ጭራሽ ዘፋኝነትን አይደግፉም ነበር፡፡ ዘፋኝ እንድሆንም አይፈልጉም፡፡ ልክ እንደ ማንኛውም ወላጅ ዶክተር… ፓይለት እንድሆንላቸው ነበር የሚፈልጉት፡፡ ነገር ግን እኔን የጠቀመኝ፣ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ በልጅነቴ ነው ብቻዬን መኖር የጀመርኩት፡፡ እናም የፈለግሁትን እያደረግሁ፣ የተሰማኝን እየሰራሁ ነው እዚህ የደረስኩት:: ቤተሰቤ ግን ይህን በፍፁም የሚቀበል አይደለም፤ ብቻዬን መኖር ባልጀምር፣ እዚህ እደርሳለሁ ብዬም አላስብም፡፡ በጣም ይከብደኝ ነበር፡፡
እንዴት ወደ አየር ሀይል እንደገባህ እስቲ አጫውተኝ?
ከ10ኛ ክፍል ጨርሼ ምሥራቅ ኮሌጅ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ጀመርኩኝ፤ ነገር ግን ወዲያው የአየር ሀይሉ የስራ ዕድል መጣልኝና አቆምኩት፡፡ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ እህት ወንድሞቼ ነበሩ፤ ግን እነሱም የተሻለ ሁኔታ ላይ ስላልነበሩና ከአጎቴም ቤት ቀደም ብዬ ስለወጣሁ፣ ተረጋግቶ የመማሩ ሁኔታ አልተፈጠረልኝም፡፡ ስለዚህ ያለኝ አማራጭ ወደ ሥራ መግባት ነበር፤ ዕድሉም ገጠመኝና አየር ሀይል ገባሁ፡፡ ትልቅ ኦርኬስትራ ውስጥ እየሰራሽ፣ ደሞዝም እየተከፈለሽ… መኖር እስቲ አስቢው… ለእኔ ትልቅ ዕድል ነበር፡፡ ይሄ እንግዲህ ፈጣሪ ወደዚህ ሙያ ጠልቄ እንድገባ ያመቻቸልኝ መንገድ ይመስለኛል፡፡ ዕድሉን ያገኘሁት እንዴት መሰለሽ? አየር ሀይል ሁለት ድምፃዊ እንደሚፈልግ ማስታወቂያ ማውጣቱን ሰው ነገረኝ፡፡ በጣም እየተጠራጠርኩ ነው… ልሞክረው ብዬ የሄድኩት፡፡
ለምን ተጠራጠርክ?
ያው ከዕድሜዬም ሆነ ከነበረኝ ልምድ አንፃር፣ እዛ ቦታ ተቀባይነት አገኛለሁ ብዬ አላሰብኩም ነገር፤ ግን ሄጄ ስወዳደር ሁለተኛ ወጥቼ አለፍኩኝ፡፡
አየር ሀይል ለምን ያህል ጊዜ ሰራህ? እዚያ በነበረህ ቆይታ ምን ተማርክ? ምን ዕድል ፈጠረልህ?
እዚያ ቦታ ላይ ከሙዚቃው በላይ በጣም የተማርኩት ዲሲፕሊን ነው፡፡ ያው የወታደር ቤት እንደመሆኑ፣ ከምንም በላይ ሥነ ሥርዓት የምትማሪበት ቤት ነው፡፡ በዚያ ላይ ኦርኬስትራው ውስጥ ያሉት ሰዎች በሰብዕናም በዕድሜም… በጣም ትልልቅና የበሰሉ ናቸው። ከእነ ጥላሁን ገሰሰ ጀምሮ ትልልቅ ድምፃዊያንን ያጀቡ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ ከእነርሱ ጋር መስራት ለእኔ በጣም ትልቅ ዕድል ነበር፡፡ ከሥራ ሰዓታችን ውጭ የሚነግሩኝና የሚያጫውቱኝ ነገር ሁሉ ለእኔ ትምህርት ነበር፡፡ ትንሽ ልጅም ስለነበርኩ፣ ሁሉም በተለየ አይን እያዩኝ ልምዳቸውን ያካፍሉኝ ነበር፡፡
ብዙ ጊዜ ‹‹የገበሬ ልጅ ነው፤ እዚያ ተቆንጥጦ በማደጉ ጨዋና ጥሩ ሰብዕና ያለው ሆኗል›› ሲባል እሰማለሁ፡፡ አንተ ደግሞ ከወላጆችህ ገና በሕፃንነትህ ነው የተለየኸው፡፡ ሰብዕናህ የተቀረፀው አየር ሀይል ውስጥ በነበረህ የስራ ቆይታ - ነው ማለት ይቻላል?
እርግጥ አጎቴም ቤት በጥሩ ሁኔታ ነው ያደግሁት… ነገር ግን ሙያን በማክበርና በማፍቀር፤ እንዲሁም በሕይወት ክህሎት ረገድ አየር ሀይል በደንብ አንፆኛል፡፡ ምንም እንኳን በአየር ሀይል የቆየሁት ለአንድ ዓመት ቢሆንም፣ ብዙ የተማርኩበት ት/ቤቴ ነው ማለት እችላለሁ::
በ‹‹ባላገሩ አይዶል›› ባታሸንፍ፣ ኖሮ… በዚህ ፍጥነት ለዝናና እውቅና ትደርስ ነበር?
በውስጤ ያለውን ልንገርሽ፤ ሙዚቃ በጣም እወዳለሁ፡፡ ለዚያ ተፈጥሬያለሁ ብዬ አስባለሁ፤ እናም ለሁሉም ነገር ሂደቶች አሉ፡፡ ወደ ሰው የምትደርሺበት… እግዚአብሄር የሰጠሽ ፀጋ አለ፡፡  የምታስታውሺ ከሆነ ከ”ባላገሩ” በፊትም ‹‹ገላዋ›› የሚል ነጠላ ዜማ ሰርቼ ነበር፡፡ የነበረኝ አማራጭ ወደ ሚዲያ የምወጣበትን ሥራ መሥራት ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ክለብ ውስጥ መጫወት እዛው መቅረት መሆኑን ተረድቼአለሁ፡፡ ስለዚህ የራሴን ስራዎች እየሰራሁ ወደ ሕዝብ የሚደርስበትን መንገድ አመቻቻለሁ የሚል ዓላማ ነው የነበረኝ:: ያው ‹‹ባላገሩ›› በመሀል እንደ እድል መጣ፡፡ አስታውሳለሁ… ቤት ቁጭ ብዬ በሬዲዬ ነው የሰማሁት፡፡ ‹‹አብርሃም ወልዴ ጨረታውን አሸነፈ›› እያሉ እነ ሰይፉ ፋንታሁን ሲናገሩ ሰማሁ፡፡ በጣም ከፍተኛ ደስታ ነበር የተሰማኝ:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ራሴን ያዘጋጀሁት፡፡
የተደሰትከው እንደምታሸንፍ ውስጥህ ነግሮህ ይሆን?
እንደዛ ሳይሆን እኔ ወደ ውድድር ከመምጣቴም በፊት የማዳምጠው የድሮ ዘፈኖችን ነበር፡፡ እንዴት እነዚህን ዘፈኖች ዘፍኜ ወደ ሰው ጆሮ ላድርሳቸው እያልኩ አስብ ነበር፡፡ ‹‹ባላገሩ አይዶል›› ሊጀመር ነው ሲባል በጣም የተደሰትኩትም፣ በውድድሩ እነዚህን ዘፈኖች ለሰው ጆሮ የማድረስ እድል አገኛለሁ ብዬ ነው፡፡ ለእኔ ዋናው ነገር ‹አሸንፋለሁ› ወይም ‹አላሸንፍም› የሚለው አልነበረም፡፡ ዓላማዬ መድረክ ላይ ወጥቼ እነዚያን ዘፈኖች መጫወትና ለሰው ማሰማት ነበር፡፡ ምክንያቱም ውድድሩ ረጅም ጊዜ ይወስዳል፤ እኔም በየዙሩ እነዚያን የምወዳቸውን  የድሮ ዘፈኖች በመዝፈን መቀጠል ነበር አላማዬ፡፡
አልበምህ ከወጣ በኋላ ‹‹አብርሃም ወልዴ፤ ዳዊት ጽጌን ዳግም ወለደው›› የሚል አስተያየት እየተደመጠ ነው፡፡ አንተ በዚህ ትስማማለህ?
አዎ! አብርሽ የተለየ ተሰጥኦና ለአርት ጥልቅ ስሜት ያለው በመሆኑ እኛንም በሰው ውስጥ ይህንን ያህል ጊዜ እንድንቆይ አድርጎናል:: ባላገሩ ከሌሎቹ አይዶሎች በተለየ መልኩ በመቅረቡ ነው፤ እኛንም ሰው ውስጥ እንድንቆይ ያደረገን፡፡ እኔ አሁን ለአራት ዓመት ያለ አልበም ሳላቋርጥ ሰርቻለሁ፤ እንደውም ብዙ ሥራዎችን እየመለስኩ ማለት ነው፡፡ ያ የሆነው በውድድሩ ግዝፈት ነው፡፡ ይሄ ውድድሩ ለሙያው የሰጠውን ክብር ያሳያል፡፡  የአብርሃምን የሐሳብ ትልቅነት ይመሰክራል፡፡  አብርሃምን በጣም ነው የምወደውና የማክበረው፡፡ ከእርሱ ጋር ሰርቼ እዚህ በመድረሴ እድለኛም ነኝ፡፡ ወደ አልበሙም ስንመጣ፣ አብርሃምን ጨምሮ ብዙ ትልልቅ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ እንደምታይው በአልበሙ ተቀባይነትና ተወዳጅነት አትርፈናል፤ ስለዚህ አባባሉን በደንብ እቀበላለሁ፡፡
‹‹ውሃ አይጣላ ከውሃ›› የሚለው ዘፈን፤ የወለደውንም ያልወለደውንም በሀዘን ልብን የሚነካ ነው፡፡ የአንዲትን ደሃ እናት ሕይወት የሚተርክ ዘፈን ነው፡፡ አንተ ደግሞ ከውድድሩ ጀምሮ እስካሁን በስሜት ነው የምትዘፍነው:: አብርሃም ወልዴ የታሪኩን ሙሉ የፊልም ስክሪፕት ጽፎ ነው የሰጠው ይባላል፡፡ እውነት ነው?
እውነት ለመናገር ዘፈኑን ሲሰማ በጣም ስሜታዊ የሚሆን ሰው አለ፡፡ እንደውም ባይዘፈን ይሻላል የሚሉም አጋጥመውኛል:: ባይዘፈን የሚሉት… የዘፈኑ ጥልቀት ውስጥን ስለሚነካ ነው፡፡ እኔ ደግሞ አንዳንዴ በጥበብ ውስጥ እንዲህ አይነት መረር ያሉ ሀሳቦች ያስፈልጋሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ያንን ነገር ማየት… ስሜቱን ማዳመጥ… ያስፈልጋል እላለሁ፡፡ ታሪኩን ስታይው የዚህች ሴት ፈተና ፈርጀ ብዙ ነው፡፡ በእውነተኛ ታሪክ ላይም ተመስርቶ ነው የተሰራው፡፡ ለዚያም ነው መቀየር ያልፈለግነው እንጂ ትንሽ ቀየር አድርጎ በጣም የሚያሳዝነውን ክፍል ቀነስ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን እውነተኛ ታሪክ ስለሆነ መቀየር አልተፈለገም፡፡
የድሬዳዋ የጎርፍ አደጋ ጊዜ የተሰራ ነው ይባላል?
አዎ፤ ያኔ በአደጋው ጊዜ ታስቦ የተሰራ ነው:: አሁን ደግሞ ከአስራ ምናምን አመት በኋላ መጥቶ እንዲህ የሰውን ስሜት መንካት ችሏል:: ይሄ የዘፈኑን የሀሳብ አቅም ያሳያል፡፡
እስካሁን ከአልበምህ ሥራዎች ውስጥ የትኞቹ ዘፈኖች ይበልጥ ተወደዋል?
እኔ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለማየት እየሞከርኩ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር አንዱን ከአንዱ የማበላለጥ ነገር ብዙ አላስተዋልኩም:: ነገር ግን ይደውሉና “ሁለት ቁጥሩ ወይም አራት ቁጥሩ አሪፍ ነው” ይሉና ደጋግመው ያንን ሰምተው ሲያበቁ፣ እንደገና ሌላውንም ይወዱትና ይደውሉልኛል፡፡ የመቆየትና ሁሉንም የመስማት ጉዳይ እንደሆነ እንጂ ሁሉንም ዘፈን ሰው ወዶታል፡፡ እኛ እንደውም አስተያየቶችን ለማሰባሰብ ሞክረን ነበር፡፡ የትኛው የበለጠ ተወዷል ብለን ቪዲዮ ለመስራትም እያጠናን ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ዘፈን ተወደዋል ማለት ይቻላል፡፡
ባንተ አልበም ውስጥ የ“ባላገሩ አይዶል”ን አስተዋጽኦ እንዴት ትገልፀዋለህ?
በጣም ትልቅ አበርክቶ ነው ያለው፡፡ እዚህ አገር ላይ እንኳንስ አልበም ነጠላ ዜማም   ለማውጣት ብዙ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ምንም የተመቻቸ ነገር የለም፡፡ ፕሮዲዩሰሮችም የሉም:: አርቲስቱ ራሱ ታግሎ ነው የሚሰራው:: ሌላው እኔ የውስጤን ለመተንፈስ መድረክ እፈልግ እንደነበረው ሁሉ ሌሎችም መድረክ የሚፈልጉ አቅም ያላቸው እንቁዎች ይኖራሉ:: ልክ እንደ ባላገሩ ደረጃውን የጠበቀ መድረክ ሲፈጠር ሕብረተሰቡም የዚያን ሰው ተሰጥኦ በአግባቡ ለመከታተል ይችላል፡፡ ምክንያቱም መድረኩ ኪነ ጥበብ ላይ ትኩረቱን ያደረገና ለኪነ ጥበብም ዋጋ የሚሰጥ ስለሆነ ማለቴ ነው:: ስለዚህ ጥበበኛውም በአግባቡ ራሱን ያሳያል፤ ሕብረተሰቡም የተሻለ ባለሙያ ያገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር የ“ባላገሩ አይዶል” አበርክቶ በቃላት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ በጣም ትልቅና ደረጃውን የጠበቀ፤ ለሕዝቡም ለባለተሰጥኦም ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡
ሙዚቃ ላንተ ምንድን ነው? “ሕይወት ነው” ብለህ እንዳታሳጥረው…
ሙዚቃ ሕይወቴን የማባብልበት፤ ሲከፋኝም ሲደላኝም ስደሰትም የምደገፍበት… ብቻ  ምን ብዬ እንደምገልጽልሽ አላውቅም፡፡ የፈራሽው አልቀረም፡፡ በቃ ሙዚቃ ለእኔ ሕይወቴ ነው፤ ከሙዚቃ ውጭ ራሴን ማሰብ አልችልም፡፡
አልበምህ ውስጥ ባይቀር ኖሮ ብለህ የተቆጨህበት ዘፈን ይኖራል?
ቢካተቱ ብዬ የምመኛቸው ስራዎች ነበሩ:: ነገር ግን 14ኛው ዘፈን፣ ከሲዲ ውጭ በሸክላ መተግበሪያ የተለቀቀው እንኳን… በፍፁም መቅረት የለበትም ብለን ነው፡፡ ነገር ግን የቀሩ ዘፈኖችም አሉ፡፡ በቀጣይ አልበምም ቢሰሩ ጊዜ አያልፍባቸውም። ለምሳሌ ‹‹አስችሎሽ›› የሚለውና ‹‹ልቤ ይላመዳል›› የሚለው፣ የዛሬ አራት ዓመት ነው የተሰሩት፡፡ እንደውም እንደ መለኪያ ነው የወሰድናቸው፡፡
ሁለት ኮንሰርቶች እንደምትሰራ ገልጸሀል፡፡ በጉጉት እየተጠበቅክ ይመስለኛል፡፡ መቼ ነው የኮንሰርቱ ጊዜ?
እውነት ነው፡፡ ከአብርሽ ጋር ሁለት ትልልቅ ኮንሰርቶችን እዚህና በአሜሪካ ለመስራት  ተስማምተናል፡፡ እሱን እናዘጋጃለን፡፡ ከዚያም በኋላ አብረን እንሰራለን ብዬ አስባለሁ:: በውላችን ላይ ግን ሁለቱ ኮንሰርቶች ተቀምጠዋል፡፡ በዚህ ቀን ለማለት ገና ቀኑን ባንቆርጥም፣ በቅርቡ እንደሚሆን ግን ጥርጥር የለውምና እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ከአድናቂዎቼ ጋር በደንብ እንገናኛለን::
አራት ዓመት ሙሉ ከአብርሃም ወልዴ ጋር ከተለያዩ አንጋፋና ወጣት የዜማና የግጥም ደራሲያን ጋር እንዲሁም ከተለያዩ አቀናባሪዎች ጋር ስትሰራ ያጋጠሙህ የማትረሳቸው ነገሮች ይኖራሉ?
ምን መሰለሽ… አንድን ነገር ወደሽው ስትሰሪው፣ የሚመጣብሽን ሁሉ ትቀበይዋለሽ እንጂ… በጣም ከባድ ነው፡፡ እኔን ሲያድለኝ መጀመሪያ የተገናኘሁት እንደነ አበበ ብርሃኔ ካሉ አንጋፋ ባለሙያዎች ጋር ነው፡፡ እነሱ ደግሞ ከዚህ ከአልበሙ ሥራ ውጭ የሚነግሩሽ ነገር፣ የሕይወት ምርኩዝ በመሆን ሌላ መልካም ማንነት ይሰጥሻል፡፡ እኔ መጀመሪያ ከእነ አቤ ጋር ባልገናኝ… እነፀጋዬ ደቦጭ ጋር አብሬ ባላሳልፍ… ይከብደኝ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡  ባለፈው አራት ዓመት ከዚህ አልበም ውጭ ላስብ አልችልም ነበር፡፡ ስራ ልሰራ እችላለሁ፤ የራሴ ሕይወት ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን  አልበሙን ቀን በቀን ነበር የማስበው፡፡ የበለጠ ጠንክሬ አልበሙን እንድጨርስና ለዚህ እንድበቃ፤ ከነዚህ አንጋፋ ሰዎች ጋር መገናኘቴ ጠቅሞኛል፡፡ በተረፈ ብዙ አዝናኝም የሚገርሙም ገጠመኞች አልፈዋል፡፡
አልበምህ ዘመኑን የሚዋጅ ነው ብለህ ታስባለህ?
አዎ! በደንብ ይዋጃል፡፡ እኛ አልበሙን እየሰራን እያለ፣ እንዲህ አይነት አገራዊ ሀሳቦች ያስፈልጋሉ ተባባልን፡፡ በተለይ በዚህ ጊዜ ዝም ማለት… አለመናገር አትችይም፡፡ እናም ይህን አስበን ስለ አገር በደንብ  ለመግለጽ ሞክረናል:: የፍቅር ዘፈኖች ሆነው እንኳን በውስጣቸው የአገር እና የወገን ፍቅር ይንፀባረቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ‹‹ልቤ ሰው ይወዳል›› የሚለውን ዘፈን እይው፡፡
ጥርስ አልሰንፍ አለ እንጂ ቀድሞ ለመሳቁ
እኔን ባይ አይጠፋም ተገፍተው ሲወድቁ… የሚለው ስንኝ በጣም ገርሞኛል…
በደንብ አድምጠሽዋል ማለት ነው፡፡ ባላገሩ ቁጥር 4፣ የክብር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰን ብትሰሚው… እሱም ጥልቅ ሀሳብ ነው ያለው፡፡ አብዛኛው በአገር ፍቅር ላይ ያተኮረ፣ የቀደሙ የአገር ባለውለታዎች የተወደሱበት፣ ለአገራችን ምን እንደሚጠበቅብን ሀላፊነት የሚሰጥ ነው:: ሰውም በብዛት ወድዶ የተቀበለው በዚህ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ዘመኑን ይዋጃል ብዬ አምናለሁ፡፡
‹‹ዝና ባለጌ ነው›› ይባላል፡፡ ምክንያቱም በዝና ሰክረው መንገዳቸውን በመሳት በየሙያ መስኩ ብዙ እንቁዎችን አጥተናል፡፡ ከዚህ አንፃር ዳዊት ዝና ሊያሰክረውና ከመንገድ ሊወጣ ይችላል ብለው ለሚሰጉ አድናቂዎችህ ምን ትላቸዋለህ?
በዝና ደረጃ ሰው የሚለግሰኝን አድናቆት በፀጋ እቀበላለሁ፡፡ ነገር ግን ወደ ውስጤ የማስገባው ባህሪዬን ሰብዕናዬን በሚቀየር መልኩ አይደለም… አድናቆቱን አክብሮቱን ያገኘሁት እግዚአብሄር በሰጠኝ ፀጋ መሆኑን አምናለሁ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው ላይም “ዝና ትፈራለህ ወይ” ብላ አንዲት ጋዜጠኛ ጠይቃኝ ነበር፡፡ አዎ ውስጤ ፍርሃት አለ፡፡ በውድድሩም ጊዜ እፈራ ነበር፡፡ ውድድሩ ካለቀ በኋላ ያገኘሁት ተቀባይነት ከፍተኛ ነበር፡፡ መቶም ሰው ይሁን መቶ ሺህ ሰው ከተቀበለሽ፣ ራስሽ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለብሽ፡፡ ወደ አልበሙም ገብቼ ሰው ተቀብሎኛል፡፡ በተቀበለኝ ልክ የሚመጥን ስራ ሰርቼ መቅረብ አለብኝ በሚል ፍርሃትና ጥንቃቄ ላይ ነኝ፡፡ ይህ ውጤት የተገኘው ከጥንቃቄ.. ለአድናቂ ክብርና ትኩረት ከመስጠት ነው፡፡ በአልበሙ በኩል የሚመጡት ግብረ መልሶች በጣም ትልልቅና ከምጠብቀው በላይ ናቸው፡፡ እነዚህ ግብረ መልሶች ለሌላ ትልቅ ሥራ ካላዘጋጀኝና አስተያየት ተቀብዬ ብቻ ከተቀመጥኩኝ፤ ትልቅ አደጋ ውስጥ ነው የምወድቀው፡፡  በዚህ መልኩ ዝናን ማስተናገድ ተገቢ ነው፡፡
ወደ ግል ሕይወትህ እንምጣ… ባለትዳር ነህ?
ጓደኛ አለችኝ፤ ግን አላገባሁም፡፡ በአልበሙ ሥራ ላይ ተወጥሬ ነበር፡፡  አሁን ደሞ በኮንሰርት ደረጃ ሰፊ ስራዎች ይጠብቁኛል፡፡ ከዚያ በኋላ እንግዲህ፣ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ወደ ትዳሩም አመራለሁ ማለት ነው፡፡
እንግዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስለ አልበሙ የምሰማው አስተያየት፣ እየመጣ ያለው አድናቆት በጣም የሚያስደስት፣ ለቀጣይ ስራ ሞራል የሚሆንና ከጠበቅነው በላይ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ በአልበሙ ስራ ላይ የተሳተፉት ሁሉ ውጤት ነው፡፡ በግጥምና ዜማ ወደ 8 ያህል ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ በቅንብሩ አብዛኛውን አበጋዝ ክብረ ወርቅ ሰርቶልኛል፡፡ በጣም ሰፊ ጊዜና ትዕግስት ሰጥቶኛል፡፡ ሌሎች አቀናባሪዎችም… አብርሃም ወልዴም… ብቻ ዘርዝሬ አልጨርሳቸውም… አቤል ጳውሎስ… ሚካኤል ሀይሉና ዲጄ አሃዱዎችን… እነ ፀጋዬ ደቦጭ፣ ያሬድ አበበ ብርሃኔ፣ ናትናኤል ግርማቸው፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ታመነ መኮንን፣ ቴዲ አፍሮ፣ ያሬድ ጫካ… ‹‹አማን አማን›› ከሚለው ዘፈኔ ጀምሮ አብሮኝ ነበር፡፡ የኢምር አድቨርታይዚንግ ኤርሚያስንም እጅግ አመሰግናለሁ፡፡ ስማችሁ ያልተጠራ በዚህ ሥራ ላይ የተሳተፋችሁትን በሙሉ በአክብሮት አመሰግናለሁ! ሚዲያውንና የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡ ከውድድሩ ጀምሮ እዚህ ያደረሰኝ ሕዝቡ ነውና ክብር ይስጥልኝ እላለሁ!   

Read 546 times