Tuesday, 04 February 2020 00:00

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

  ‹‹የገነባኸው ቢፈርስብህ አሻሽለህ ለመገንባት ሞክር››
                    
            ‹‹ነገ አብረን እንዋል›› አለኝ፡፡… ወዳጄ ዘኔ - እሮብ ምሽት ስልክ ደውሎ፡፡
‹‹የምጽፈው ነገር ባይኖር ጥሩ ነበር›› አልኩት፡፡
‹‹ታዲያ ምን ችግር አለ?... እዚህ መስራት ትችላለህ፣ ሪፈረንስ እንደ ልብ የምታገኝበት ቦታ ነው›› አለኝ፡፡ እውነቱን ነው፡፡ መኖሪያው በምርጥ መጽሐፍቶች የታጨቀ ነው፡፡ ባለፈው ስንገናኝ ሙሉ ኢንሳይክሎፒድያ በብዙ ገንዘብ እንደገዛም አጫውቶኛል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ቦታ ስቀመጥ ይመቸኛል፡፡ አንድ ጊዜ አንድ ሰው አንዱን የመጽሐፍት ወዳጅ፡-
‹‹ለምን ብቸኛ ትሆናለህ?›› ቢለው… ሰውየው እየተገረመ በዙሪያው የተገጠገጡትን መጽሐፍት እያሳየው፡- ‹‹በነዚህ ዓለምን የሚያንቀጠቅጥ ሀሳብ ባላቸው ደራሲያን ተከብቤ እንዴት ‹ብቸኛ› ትለኛለህ?›› በማለት እንደመለሰለት አንብቤያለሁ፡፡
‹‹እሽ እመጣለሁ›‹ አልኩት ወዳጄን፡፡ በማግስቱ ስለምጽፈው ነገር እያሰብኩ መንገድ እንደጀመርኩ፡- ‹‹ተሜ ይቅርታ! አንድ ዘመዴ አደጋ እንደ ደረሰበት ነገረኝ፤ ‹‹አንተን አመቻችቼ ወደዚያው እሄዳለሁ፣ አሁን የት ደርሰሃል?›› ብሎ ደወለልኝ፡፡ ገና ከሰፈር እንዳልወጣሁ ነግሬው፣ ቀጠሮአችንን ለሌላ ጊዜ አዛውረን፣ በድንገት ላጋጠመው ሃዘንም መጽናናትን ተመኘሁና አቅጣጫዬን ቀየርኩ።
ወዳጄ፡- የምትቀጥለው ደቂቃ ምን እንዳረገዘች ማን ያውቃል? ወላጆቻችን ሰው ያስባል እግዜር ይፈጽማል (‹‹Man Proposes God Disposes›› ይላሉ - ሊቃውንቱ፤ ‹‹There is no mathematical Certainly in life›› እንደሚሉት፡፡
ሰውየው ጥሩ ሚስት አለችው - የዋህ የምትባል፡፡ ሁለት ዓመት አብረው ኖረዋል:: እሱ ግን ‹‹አልፀነሰችልኝም›› በሚል ሰበብ ውጭ፣ ውጭውን ማየት ከለመደ ሰነባብቷል:: እንዳይፈታት በመሃላቸው ባለ አንድ የመኝታ ክፍል የጋራ መኖሪያ ቤት አለ፡፡ ትቶላት ቢወጣ እንደሚቸገር ያውቃል፡፡ ወደ ከተማው አዋቂ ዘንድ ሄዶ፡፡ ‹ጉዳዩን›› ዘርዝሮ አስረዳ፡፡
‹‹አንተ አልተመረመርክም? ችግሩ ያንተ ቢሆንስ?››
‹‹አላውቅም ጌታዬ››
‹‹ትመረመራለህ? ወይስ የሕይወት መንገድህ ይነገርህ?››
‹‹ይነገረኝ››
አዛውንቱ መጽሐፋቸውን ገለጡና፡-
‹‹እነዚህን ቁጥሮች ልብ በል፡፡ ያንተ ሕይወት ልማቱም ሆነ ጥፋቱ የሚወሰነው በነሱ አቀማመጥ ነው፡፡ ከሌላ ጋር ሳይቀላቀሉ ብቻቸውን ተደርድረው ባየህበት ቦታ ሁሉ ደስታና ሲሳይ አለ፡፡ ሁሉም ልክ ሆነው የመጨረሻው ከተቀየረ ግን አደጋ ነው፡፡›› አሉትና በቃሉ እንዲያጠናቸው ጽፈው ሰጡት:: የባለቤቱም ጉዳይ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረዱት፡፡
ሰውየው የተነገረው ነገር ‹እውነት› መሆኑን አልተጠራጠረም፡፡ ማጥናትም አላስፈለገውም:: ምክንያቱም ቁጥሮቹ ከተወለደበት ቀን፣ ወርና ዓመተ ምህረት ጋር ተመሳሳይ ነበሩ፡፡ በዛው ሰሞን ከተወለደበት ቀን ጋር የተመሳሰለ ቁጥር ያለው የሎተሪ ትኬት ባጋጣሚ በማግኘቱ እየተገረመ ቆረጠ፡፡ አንደኛው ዕጣ ወጣለት፡፡ ‹ችግር አገሩ ገባ› ሲል አሰበ፡፡ ሚስጥሩን ሸሽጎ፣ ሚስቱን ሥራው እንዳልተመቸውና ቤተሰቦቹ ጋ ተመልሶ መኖር እንዳለበት በማሳመን ለፍቺ አመቻቻት፡፡ አንድ ቀን ጠዋት፡-
‹‹ፍ/ቤት ሄደን ጉዳያችንን እንቋጭ›› አላት
‹‹ነገ እናድርገው ዛሬ እራሴን አሞኛል›› ብትለው
‹‹ነገ ጉዳይ አለኝ፣ ዛሬ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ›› ብሎ ወተወታት፡፡ ተነስተው ሄዱ::  ሰማኒያቸውን አውርደው፣ እሷ እየከፋት፣ እሱ በውስጡ እየፈነጠዘ ሲመለሱ፣ የነበረው ሁሉ በድንገት እንዳልነበረ ሆነ፡፡ ወዳጄ፤ የምትቀጥለው ደቂቃ ምን እንዳረገዘች ማን ያውቃል?
* * *
በማወቃችን ውስጥ ጥርጣሬ እንዳለ ሁሉ ባለማወቃችን ውስጥ ተስፋ አለ፡፡ ተስፋ የሌለበት ምንም ነገር የለም (There is no a totally hopless situation)፣ ‹‹የታላቅነት ሚስጥር  መድረስ ሳይሆን መሄድ አለማቆም ነው›› ይላሉ ሊቃውንት፡፡   
‹‹አልሳካ እያለ ካስቸገረህ ለምን አትተወውም?›› ሲሉት
‹‹I have not failed, I have just found 10,000 ways that will not work›› በማለት ነበር የመለሰው… ታላቁ ኤዲሰን፡፡
ወዳጄ፡- ‹ፎረስት ጋምፕ› የሚለውን ፊልም አይተሃል?... run forest! run… run!.. run!  እንዳትቆም፡፡ መቆም መሸነፍ ነው፡፡… እጅ መስጠት፡፡›› የሚለውን ማለቴ ነው፡፡  
‹‹ወደ ነፃነት የሚያደርሱ መንገዶች አስቸጋሪ ናቸው፡፡ ሀሳባችን ተሳክቶ ዛሬ ላይ የደረስነው እዚህም እዛም በተደነቀሩ የሞት ዋሻዎች ውስጥ ያለማቋረጥ ተጉዘን ነው፡፡›› ይልሃል ኔልሰን ማንዴላ፡፡ ወዳጄ አትቁም!!
አንዳንድ ፈተናዎች በሬት እንደተጠቀለለ ማር ውስጣቸው ጣፋጭ ሊሆን እንደሚችልም አትዘንጋ፡፡ መራራውን ከተቋቋሙ ወለላው ይክሳል፡፡  ‹‹Blessing in disguise›› እንደሚሉት፡፡ ያለ ድካም ፍሬ አይገኝምና ተስፋ አትቁረጥ፡፡ የገነባኸው ቢፈርስብህ አሻሽለህ ለመገንባት ሞክር፡፡ በተስፋ ሁሉም ቀላል ነው፡፡
ወዳጄ፡- ከቻይናዋ ውሃን ከተማ ተነሳ የተባለው ቫይረስ፣ አለምን እያመሰ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የፕሮቴስት፣ የጡት፣ የሳንባና የሌሎች በሽታዎች ምክንያትና የብዙሃን ሞት የሆነው የካንሰር ሕመም ፈውስ እንደተገኘለት፣ ከትናንት ወዲያ በቢቢሲ ሰምቻለሁ፡፡ ታላቅ ዜና ነው፡፡ ‹‹በአንዱ ጎን ሲጎድል በሌላው ይሞላል››  ይባል የለ? የምትቀጥለው ደቂቃ ምን እንዳረገዘች ማን ያውቃል?
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሁለቱ የ‹ቀድሞ› ባልና ሚስት ከፍ/ቤቱ ወጥተው፣ ወደ ሰፈራቸው ለመመለስ ተረኛ በነበረው ታክሲ ተሳፈሩ፡፡ እሷ ጋቢና ተቀምጣ እሱ ከሌሎቹ ጋር ታጭቆ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ወደ ካርል አደባባይ በሚያወጣው ቁልቁለት ላይ ፍሬን በመበጠሱ መኪናው ተገለበጠ፡፡ ሰውዬው ጭንቅላቱ በመጎዳቱ ራሱን ሲስት፣ እሷ ቀበቶ በማሰሯ ጭረት እንኳ አልደረሰባትም፡፡
የሕክምናው ማስረጃ፡- በግጭቱ ምክንያት  የሰውየው የማስታወስ ችሎታ መደምሰሱን ያረጋግጣል፡፡ እንደ አልዛይመር ሕመምተኛ፣ ቤተሰቦቹ ወደ መኖሪያቸው ሲወስዱት እንኳ ማንነታቸውን አላወቀም፡፡ ፍቺው በስምምነት በማለቁ፣ ሚስቱን በቀላሉ በማታለሉ ከደስታው ብዛት ልብ አላለም እንጂ የተሳፈሩበት መኪና ሰሌዳ ቁጥር ከተወለደበት ጊዜ ቁጥር ጋር ተመሳሳይ ነበር፡፡… ከመጨረሻው ዲጂት በስተቀር፡፡ የመጨረሻዋ ቁጥር ‹ዜሮ› እንደነበረች ለማሰብ ጊዜ ሳያገኝ መኪናው ፈጠነበት፡፡
ወዳጄ፡- የምትቀጥለው ደቂቃ ምን እንዳረገዘች ማን ያውቃል?
ሰውየው ከሆስፒታል ወጥቶ ወደ ቤተሰቦቹ ከሄደበት ቀን ጀምሮ ከጠዋት እስከ ማታ ‹‹ዜሮ! ዜሮ!›› እያለ ስለሚጮህ የሰፈር ሰዎች በቅጽል ስሙ ‹ዜሮ› እያሉ ይጠሩታል። ከቦርሳው ውስጥ ከእነ ማውጫዋ የደበቃትን ሎተሪ አግኝታ ሀብታም የሆነችው የ‹ቀድሞ› ሚስቱ እየሄደች ትጠይቀዋለች፡፡ እሱ ግን ከ‹ዜሮ› በስተቀር የሚያስታውሰው ነገር የለም፡፡
‹‹ዜሮ… ና ስመኝ እስቲ›› ስትለው ይስቃል፡፡
በነገራችን ላይ ‹ሁሉም ዜሮ፣ ዜሮ› የሚለውን ዘፈን ታስታውሱታላችሁ? አንድ ችግኝ ሳይተክሉ፣ የተተከሉትን እንኳ ሳይጎበኙ ‹ምርጫ! ምርጫ!› እያሉ የሚነዘንዙን ፖለቲከኞች፣ የፕሮግራማቸው ሳውንድ ትራክ ቢያደርጉት ጥሩ ነበር፡፡ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ›› መባሉን ያስታውሳቸዋል፡፡... አገር የሆያ ሆዬ ቤት አይደለምና!!
ሰላም!!   Read 250 times