Monday, 03 February 2020 12:00

የምሽቱ ባቡር በዲዬሊ

Written by  ደራሲ - ሩስኪን ቦንድ ትርጉም - ዐቢይ ጣሰው
Rate this item
(10 votes)

   የኮሌጅ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት የክረምት እረፍቴን የማሳልፈው በዳህራ፣ ከሴት አያቴ ጋ ነበር፡፡ ግንቦትን ቀደም ብዬ ሔጄ በሐምሌ አርፍጄ እመለሳለሁ፡፡ ዲዬሊ ከዳህራ ሰላሳ ማይሎች ወዲህ ያለች ባቡር ጣቢያ ነች፡፡ ባቡሩ ወደ ህንዱ ታዋቂ ደን ከመግባቱ በፊት አፋፍ ላይ ትገኛለች፡፡
ባቡሩ ዲዬሊ የሚደርሰው ከንጋቱ አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ ነበር፤ በጣቢያው የኤሌትሪክ አምፖሎችና ፋኖሶች ቢበሩም ድንግዝግዝ ይላል፡፡ የባቡሩን ሃዲድ የሚውጠው ደን በወጋገኑ ይታያል፡፡ ዲዬሊ አንዲት መካከለኛ መሳፊሪያ ሰገነት፣ የጣቢያው ተቆጣጣሪ አንዲት ቢሮና ባቡር መጠበቂያ አንዲት ክፍል ብቻ አላት፡፡ በመሳፈሪያው ሰገነት ላይ አንዲት ሻይ አፍዪ፣ ፍራፍሬ ሻጭና የተወሰኑ የመንደር ውሾች ይታያሉ፡፡ ሌላ የለም፡፡ ምናልባት ባቡሩ ወደ ደኑ ከመስመጡ በፊት ለአስር ደቂቃዎች ብቻ ስለሚቆይ ይሆናል፡፡
ባቡሩ ለምን በዲዬሊ እንደሚቆም አላውቅም፡፡ በዚያ የሚፈጠር ምንም ነገር የለም:: የሚወርድም የሚሳፈርም  የለም:: በሰገነቱም ላይ ዕቃ ጫኝ አውራጆችም (ኩሊዎች) ታይተው አይታወቁም፡፡ ሆኖም ባቡሩ በዚያ ለአስር ደቂቃዎች ይቆማል፡፡ ከዚያ ደውል ይደወላል፤ የጣቢያው ጠባቂም ፊሽካውን ይነፋል፤ ዲዬሊ ወዲያውኑ ትረሳለች፡፡
ሁልጊዜ በዲዬሊ ከባቡር ጣቢያው ግንቦች ባሻገር ምን እንደሚካሄድ ማወቅ እፈልግ ነበር:: ያ ማንም ሊጎበኘው የማይፈልገው ብቸኛው መሳፈሪያ ሰገነት ያሳዝነኛል፡፡ አንድ ቀን በጣቢያው ወርጄ ከተማውን ለማስደሰት ስል ዞር ዞር ማለት አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡
አስራ ስምንት ዓመቴ ነበር፤ አያቴን ለመጎብኘት የተሳፈርኩበት የምሽት ባቡር እንደተለመደው ለአስር ደቂቃዎች በዲዬሊ ቆሟል፡፡ ዘንቢል የምትሸጥ አንዲት ልጃገረድ ከሰገነቱ ጫፍ መጣች፡፡ ጠዋቱ ብርዳማ ነበርና ጀርባዋ ላይ ሻርፕ ደርባለች፡፡ እግሮቿ ጫማ የላቸውም፤ ልብሶቿ አርጅተዋል፡፡ እርሷ ግን ከታላቅ ግርማ ሞገስ ጋር በኩራት የምትራመድ ወጣት ሴት ነበረች፡፡
የኔ መስኮት አጠገብ ስትደርስ ቆመች:: በአትኩሮት እያየኋት እንደነበር አውቃለች፤ እንዳላየ ግን ሆናለች፡፡ ጥቁር ጸጉሯ የገረጣውን ቆዳዋን ይበልጥ አሳጥቶታል፤ ዓይኖቿ ጥቁር የተረበሹ ናቸው፡፡ እነዚያ ፈላጊና ተናጋሪ አይኖች፣ ከኔ አይኖች ጋር ተገናኙ፡፡
ከመስኮቴ አጠገብ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ብትቆምም፣ ከአንዳችንም ምንም ቃል አልወጣም:: ስትንቀሳቀስ ግን ራሴን ከመቀመጫዬ  ተነስቼ  ወደ  በሩ  ስሄድ አገኘሁት:: በሩ ላይ ቆሜ አይታኝ፣ መልሳ ወደ ሌላ አቅጣጫ እያየች፣ በሰገነቱ ላይ ቆማ ጠበቀችኝ፡፡ ወደ ሻይ መሸጫው አመራሁ፤ አነስ ባለ ምድጃ ላይ አነስተኛ ጀበና ትንሰረሰራለች፡፡ ባለቤቱ ሌሎች የባቡሩን ተሳፋሪዎች እያስተናገደ ነበር፡፡ ልጅቷ ተከትላኛለች፡፡
“ዘንቢል ትፈልጋለህ? ከጠንካራ ሸንበቆ ነው የተሠሩት…” ብላ ጠየቀችኝ፡፡
“አልፈለግም” አልኳት፤ “ሳጠራ አልፈልግም::”
ረዘም ያለ ለመሰለኝ ጊዜ እየተያየን ቆምን፡፡
“እርግጠኛ ነህ ዘንቢል አትፈልግም?” አለችኝ፡፡
“እሺ፤ አንድ ስጪኝ” አልኳት፡፡ ከላይ ያለውን አንዱን ወስጄ አንድ ሩፒ ሰጣኋት፡፡ ጣቶቿን ልነካቸው ብፈልግም አልቻልኩም፡፡
ልትናገር ስትል የጣቢያው ጠባቂ ፊሽካውን ነፋው፡፡ የሆነ ነገር ብትናገርም በደውሉ ድምጽና በባቡሩ ሞተር ጩኸት ተዋጠ፡፡ ወደ ባቡሬ መሮጥ ነበረብኝ፡፡ ፉርጎው ተንገራግጮ ወደፊት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡
የመሳፈሪያው ሰገነት ከአይኖቼ እስኪጠፋ ድረስ አያየኋት ነበር፡፡ በሰገነቱ ላይ ብቻዋን እንደቆመች ነው፤ አልተንቀሳቀሰችም፣ ነገር ግን በፈገግታዋ ታጅባ እያየችኝ ነው፡፡ የባቡር ምልክቱ ወደ ውስጥ እስኪያስገባኝ አየኋት:: ከዚያ ደኑ ጣቢያውን ሸፈነው፡፡ ሆኖም ግን ብቻዋን እንደቆመች እያሰብኳት ነበር፡፡
ከዚያ ቀጥሎ ባለው ጉዞ ፈጥጬ ቁጭ ብያለሁ፡፡ የልጅቷን ፊት፣ እንደ ኮከብ የሚያበሩትን ጥቋቁር አይኖቿን ፈጽሞ ልረሳቸው አልቻልኩም፡፡
ደህራ ስደርስ ጭንቅላቴን ሌሎች ነገሮች ሲወሩት አጋጣሚው ደበዘዘ፡፡ ከሁለት ወራት ቆይታ በኋላ ስመለስ ነበር ልጅቷን ያስታወስኩት፡፡
ባቡሩ ወደ ጣቢያው እየቀረበ ሲመጣ፣ በመሳፈሪያው ሰገነቱ ላይ በአይኖቼ ፈለግኋት፡፡ ወደ ሰገነቱ ስትወጣ ሳያት ያልጠበቅሁት ጥልቅ ደስታ ተሰማኝ፡፡ ባቡሩ ሳይቆም አርፋ ወርጄ እጆቼን አውለበለብኩላት፡፡ ስታየኝ ፈገግ አለች:: ስላስታወስኳት ደስ ብሏታል፤ ስላልረሳችኝ ደስ ብሎኛል፡፡ ሁለታችንም ደስተኞች ነበርን:: ተጠፋፍተው እንደተገናኙ የድሮ ጓደኛሞች ሆንን ማለት ይቻላል፡፡
ዘንቢሎቿን ለመሸጥ ሁሉንም የባቡሩን ፉርጎዎች አላዳረሰችም፤ ቀጥታ ወደ ሻይ ማፍያው መጣች፡፡ ጥቋቁር ዐይኖቿ በብርሃን ተሞልተዋል፡፡ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ምንም አላወራንም፤ ማውራት ብንፈልግ እንኳ ምላሶቻችን በ’ጅ የሚሉንም አይመስለንም፡፡ አሁኑኑ ባቡሩ ላይ አሳፍሬያት ይዤያት የመሄድ ሃሳብ አደረብኝ፡፡ እየራቀ በሚሄደው የዲዬሊ ጣቢያ ላይ እያየኋት የመጥፋቷን ነገር ልቀበለው አልቻልኩም፡፡ ዘንቢሎቿን ከእጆቿ ተቀብዬ ወለሉ ላይ አስቀምጥኳቸው፡፡ አንዱን ዘንቢል ልታነሳው እጇን ሰደደችው፤ ለቀም አድርጌ ያዝኩት፡፡
“ወደ ደህሊ መሄድ አለብኝ” አልኳት፡፡
ጭንቅላቷን እየነቀነቀች “እኔ ወድየትም መሄድ የለብኝም” አለችኝ፡፡
የጣቢው ጠባቂ ፈሽካውን ነፋው፤ ጠባቂውን እንዴት እንደጠላሁት፡፡
“ተመልሼ እመጣለሁ” ጭንቅላቷን በእሽታ ስትነቀንቅ ደውሉ ተደወለ፡፡ ባቡሩ ተንቀሳቀሰ:: እጄን ከእጆቿ አለያይቼ እያኮበኮበ ወዳለው ባቡር መሮጥ ነበረብኝ፡፡
አሁን አልረሳኋትም፡፡ በተቀረው ጉዞዬም፣ ከዛም በኋላ ባሉት ጊዜያት ከኔ ጋር ነበረች፡፡ ዓመቱን በሙሉ ህያው ሆና ደምቃ ቆይታለች:: የትምህርቱ ዓመት ሲያልቅ ከወትሮው ቀደም ብዬ በችኮላ ሻንጣዬን ሸካክፌ ወደ ደህራ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ሴት አያቴ እርሷን ለማየት ባለኝ ጉጉት እንደምትደሰት ጥርጥር የለውም፡፡
ባቡሩ ወደ ዲዬሊ ጣቢያ ሲቀርብ ነፍሴ ተወጠረች፤ ለልጅቷ ምን እንደምላት አላወቅሁም፡፡ ምን ላድርግ? እየተሰማኝ ስላለው ስሜት ምንም ሳልናገር ወይም አንዳች ነገር ሳላደርግ ተገትሬ እንደማልቆም ወስኛለሁ:: ባቡሩ ዲዬሊ ሲደርስ በሰገነቱ ላይ አይኖቼን ወዲህ ወዲያ ባንከራትት ልጅቷ የለችም፡፡
የፉርጎውን በር ከፍቼ ወረድኩ፡፡ በጣም ተናደድኩ፡፡ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ወዲያውኑ ወረረኝ፡፡ የሆነ ነገር ማድረግ አለብኝ፤ ወደ ጣቢያው ጠባቂ ሮጥኩ፡፡
“እዚህ ዘንቢሎችን ትሸጥ የነበረችውን ልጅ ታውቃታለህ?” ስል ጠየቅሁት፡፡
“አላውቃትም፡፡ ባቡሩ እንዳያመልጥህ ቶሎ ብትሳፈር ይሻላል” አለኝ፡፡
ነገር ግን በመሳፈሪያው ሰገነት ላይ ወዲህ ወዲያ ሮጥኩ፤ ሃዲዶቹን ተመለከትኩ፡፡ ከማንጎ ተክሎችና ወደ ደኑ ገብቶ ከሚጠፋ አቧራማ መንገድ ውጭ የሚታየኝ ነገር የለም፡፡ መንገዱ ወዴት ነው የሚወስደው? ባቡሩ ከጣቢያው እየወጣ ነበር፤ ወደ ፉርጎዬ ሮጥኩ፡፡ ባቡሩ ፍጥነቱን ጨምሮ ወደ ጫካው እየሮጠ ገባ፡፡
በሃዘን እንደተዋጥኩ መስኮቱ ላይ አፍጥጬያለሁ፡፡
ሁለቴ ብቻ ያየኋትን፣ ከተወሰኑ ቃላት ውጭ ያላወራችኝን፣ ስለ እርሷ ምንም የማላውቅ… ነገር ግን ከዚህ በፊት ተሰምቶኝ የማያውቀውን ስሜት እንዲሰማኝ ያደረገችኝን ልጅ ለማግኘት ምን ማድረግ አለብኝ?
አያቴ በዚህኛው ክረምት ቆይታዬ አልተደሰተችም፡፡ ከሁለት ሳምንታት በላይ ከእርሷ ጋ ማሳለፍ አልቻልኩም፡፡ ረፍት የለሽ ሆንኩ፤ ታመምኩምም፡፡ እናም ባቡር ተሳፍሬ ወደ ዲዬሊ፣ ስለ ልጅቷ ከጣቢያው ጠባቂ ይበልጥ ለማወቅ፡፡
ዲዬሊ ስደርስ ግን አዲስ ጠባቂ ነበር የተቀበለኝ፤ የበፊቱ ጠባቂ ባለፈው ሳምንት ወደ ሌላ ጣቢያ ተዘዋውሯል፡፡ አዲሱ ጠባቂ ዘንቢል ስለምትሸጠዋ ልጅ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ የሻይ ማፊያውን ባለቤት አገኘሁት፤ አነስ ያለ ጠውላጋ ነው፤ በዘይት የተጨማለቀ ኮት ለብሷል፡፡ ዘንቢል ስለምትሸጠዋ ልጅ የሚያውቀው ነገር ካለ ጠየቅሁት፡፡
“አዎን፤ የምትላት ልጅ እዚህ ነበረች:: በደንብ አስታውሳታለሁ…” ትንሽ ዝም ካለ በኋላ “አሁን ግን መምጣት አቁማለች” አለኝ፡፡
“ለምን? ምን ገጠማት?” ስል ተጣድፌ ጠየቅሁት፡፡
“እንዴት ላውቅ እችላለሁ? ለኔ’ኮ ምኔም አይደለችም” አለኝ፡፡
አሁንም ባቡሬ እንዳያመልጠኝ መሮጥ ነበረብኝ፡፡
የዲዬሊ ጣቢያ ከዐይኖቼ አየራቀ ሲሄድ፣ አንድ ቀን በጣቢያው ወርጄ፣ በእይታዋ ብቻ ልቤን የሰረቀችውን ልጅ መፈለግ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡
በዚህ ሃሳቤ የተቀረውን የመጨረሻ ዓመት ቆይታዬ ተጽናናሁ፡፡ ክረምት ሲመጣ ወደ ደራህ ጉዞ ጀመርኩ፡ ሊነጋጋ ሲል ባቡሩ ወደ ዲዬሊ ጣቢያ እየቀረበ ሲመጣ፣ ልጅቷ ምልክቷ እንኳ ቢኖር በሚል በሰገነቱ ላይ አፈጠጥኩ፡፡ ተስፋ ቢኖረኝም ልቤ ግን እንደማያገኛት አውቆታል፡፡
ምንነቱን በማላውቀው ምክንያት ዲዬሊ ላይ ጉዞዬን ማቋረጥ አልቻልኩም፡፡ (ፊልም ወይም ልቦለድ ቢሆን ግራ ቀኙን አስቤ፣ ጣቢያው ላይ ወርጄ፣ ምስጢሩን ፈትቼ የሆነ መደምደሚያ ላይ እንደርስ ነበር፡፡) የፈራሁ ይመስለኛል፤ ልጅቷ ምን እንደሆነች ማወቅ የምር ፈርቻለሁ:: ዲዬሊን ለቃ ሄዳ፤ አግብታም ይሆናል፡፡ ምናልባትም ታማ…
ባለፉት ዓመታት በዲዬሊ ባለፍኩባቸው በርካታ ጊዜያት ከተቀመጥሁበት በመስኮቱ አሻግሬ በግማሽ ልብ ያንን ያልተለወጠ ፈገግተኛ ፊት ፈልጌያለሁ፡፡ ከዚያ ጣቢያ ግድግዳ ባሻገር ባለችው ዲዬሊ ምን ይካሄድ ይሆን ስል አሁንም አስባለሁ፡፡
ዲዬሊ ላይ ግን አልወርድም፡፡ ተስፋ ማድረግና ማለም መርጫለሁ፡፡ በመስኮቱ ባሻገር ያንን ብቸኛ ሰገነት እየተመለከትኩ፣ ዘንቢል የምትሸጠውን ልጅ እጠብቃለሁ፡፡
ዲዬሊ አልወርድም፤ በተቻለኝ መጠን ግን በጣቢያው ቶሎ ቶሎ አልፋለሁ፡፡


Read 2628 times