Saturday, 08 February 2020 14:42

ኢትዮጵያን በ17ኛው ክ/ዘመን የሚገልፀው ደብዳቤ ተደብቆ ተገኘ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    ኢትዮጵያ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአለም ሀገራት ጋር ያላትን መጠነ ሰፊ ዲፕሎማሲያዊና የንግድ ግንኙነት በዝርዝር ያስረዳል የተባለ ደብዳቤ በእንግሊዝ ሀገር ብሪትሽ ላይብረሪ ውስጥ ተደብቆ መገኘቱን ላይብረሪው አስታውቋል፡፡
ደብዳቤው በ1622 አካባቢ፣ በአፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት፣ ኢትዮጵያ ምን መልክ እንደነበራት ግንዛቤ የሚሰጥ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በወቅቱ አንድ አርመናዊ ነጋዴ የተፃፈው ይሄ የጉዞ ማስታወሻ ደብዳቤ፤ በተለይ ኢትዮጵያና ህንድ የነበራቸውን የንግድ ግንኙነት በሰፊው ያሳያል ተብሏል፡፡
አርመናዊው ነጋዴ መቀመጫቸውን ጐንደር - ደንቢያ አድርገው ኢትዮጵያን ያስተዳድሩ የነበሩትን አፄ ሶስኒዮስን ማግኘቱን በመግለጽ አፄው የነበራቸውን ባህሪና ተክለቁመና በሰፊው ያብራራል - በደብዳቤው፡፡
አፄ ሱስንዮስ በወቅቱ ሃያል እንደነበሩ በየቀኑ 2ሺህ ያህል አቤቱታዎችን እየተቀበሉ የሚያስተናግዱ፣ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ መኳንንቶች በዙሪያቸው ይገኙ እንደነበር፤ አርመናዊው ነጋዴ አመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከተቀረው የአለም ሀገራት ጋር የነበራት የንግድ ግንኙነት ከህንድ፣ ቤንጋል፣ ቻይና እንዲሁም ከጣሊያንና ኦቶማን ቱርክ ጋር የነበራትን ጠንካራ የንግድ ግንኙነት በስፋት እንደሚያትት ታውቋል፡፡

Read 1562 times