Saturday, 08 February 2020 14:51

“ባልደራስ” ነገ መስራች ጉባኤውን ያካሂዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

   የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ምክትሉ ይመረጣሉ

          በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ10 ሺህ በላይ አባላት መመዝገቡን ያስታወቀው ‹‹ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ›› (ባልደራስ)በነገው እለት መስራች ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሂዳል፡፡ በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራው ‹‹ባልደራስ›› በነገው ዕለት በአዲስ አበባ የመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፅ/ቤት ውስጥ በሚያካሂደው መስራች ጉባኤው ላይ የፓርቲው የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ይፀድቃል ተብሏል፡፡
ፓርቲው በዋናነት በአዲስ አበባ በሚያደርገው የምርጫ ተሳትፎ ላይም ምክክር ይደረጋል ሲል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
በእለቱ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ፣ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትና የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ም/ፕሬዚዳንት እንደሚመረጡም ለማወቅ ተችሏል:: “ፓርቲውን በምንመሠርትበት ወቅት በተለይ 10ሺህ ፊርማ ለማሰባሰብ ጥረት ስናደርግ የህዝቡ ተሳትፎ ከጠበቅነው በላይ ነው” ያለው ጋዜጠኛ እስክንድር፤ ፓርቲው በአዲስ አበባ ላይ ትኩረት አድርጐ ይንቀሳቀሳል ብሏል፡፡

Read 12092 times