Saturday, 08 February 2020 14:54

‹‹ቆመን ጠበቅናቸው ጥለውን አለፉ!››

Written by 
Rate this item
(7 votes)


             ከዕለታት አንድ ቀን በርካታ የተራቡ ጅቦች በአንድ ገደል አፋፍ እየሄዱ ሳሉ፤ አንድ እጅግ ግዙፍ ዝሆን እገደሉ አዘቅት ውስጥ ወድቆ ሞቶ አዩ፡፡
አንደኛው ዝሆን፤
‹‹ጎበዝ አዘቅቱ ውስጥ የወደቀው ዝሆን ይታያችኋል?›› አለና ጠየቀ፡፡
ሁለተኛው ዝሆን፤
‹‹ፍንትው ብሎ ተጋድሞ ይታየኛል››አለና መለሰ፡፡
ሦስተኛው ዝሆን፤
‹‹እኔ አንድ ሀሳብ አለኝ››
አንደኛው ዝሆን፤
‹‹ምንድን ነው ንገረና?››
ሦስተኛው ዝሆን፤
‹‹ለምን ገብተን አንበላውም? በጣም የሰባ ምርጥ ጮማ ያለው ዝሆን እኮ ነው፡፡››
ሁለተኛው ዝሆን፤
‹‹ይሄ ምርጥ ሀሳብ ነው፡፡ ቶሎ እንግባ እባካችሁ?››
አንደኛው ዝሆን፤
‹‹ዕውነት ነው እንግባ ጎበዝ!››
ሁሉም ‹‹ይሁን፣ ይሁን›› አሉ፡፡
ሁሉም የገደሉን ቁልቁለት ወረዱት፡፡
ያንን ጮማ ዝሆን እያሽካኩ ተቀራመቱት፡፡
ሁሉም ሆዳቸው ሞላ፡፡ ግን አንድ ችግር ተፈጠረ፡፡
በሞላ ሆድና በዝሆን ግዝፈት ማን ገደሉን ወደ ላይ ይውጣው?
ዋሉ፡፡
አደሩ፡፡
ረሀብ መጣ፡፡
ጥቂት ቀናት ቆይተው አንድ ሌሊት ላይ አንዱ ዝሆን ጭልጥ አድርጎ እንቅልፍ እንደወሰደው ሌሎቹ ዝሆኖች ተሰበሰቡና መከሩ፡፡ በመጨረሻም፤ በሚያንቀላፋው ዝሆን ፈረዱበት - ሊበሉት፡፡
በሉትና ጥግብ አሉ፡፡ በአካባቢው ፈንጠዝያ ሆነ፡፡ ወደ ገደሉ አፋፍ ለመውጣት ግን አልቻሉም፡፡ ስለዚህ አንዱ አንዱን እንኮኮ እያለ፣ ወደ ጫፍ ዘለቁ፡፡ በመጨረሻ ግን አንዱ ተሸካሚ ዝሆን ከታች ቀረ፡፡ ማንም ሊያወጣው የሚችል አልኖረም፡፡
ብቻውን ቀረ፡፡
ቀን እየገፋ መጣ፡፡ አካሉ ሁሉ እየከሳ መጣ፡፡ ረሀቡን መቋቋም አቃተው፡፡ በዚያው ሕይወቱ አለፈ፡፡
*   *   *
ነገ የሚከተለውን ችግር ሳያስቡ መጓዝ መጨረሻው አያምርም፡፡ በተራ ሰው ግምት እንኳ ቢጠናና ቢመረመር ነገን ሳያስቡ መጓዝ፣ የዛሬን አላስተማማኝ መንገድ ማረጋገጥ ነው፡፡ የማያስተማምኑ መንገዶች መድረሻን ወደ አለማወቅ የሚያመሩ በመሆናቸው ለውድቀት ይዳርጋሉ፡፡ ቢያንስ አይቀሬ ወደሆነው የዕለት - ሰርክ የሥጋት ዓለም ውስጥ በሽብልቅ የሚደነጎሩ ይሆናሉ፡፡ የተሸበለቀ ሕይወት፤ የተውገረገረ አመለካከትና እሳቤ ውስጥ ስለሚከት፣ የነገ ብሩህና የጠራ አስተሳሰብ እንዳይኖረን የሚያደርግ ጎልዳፋ ህልውና ላይ ይጥለናል፡፡
የአገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሕልውና ቅጥ አምባር በቀና አመራር ሥር ከተቀነበበ፣ የተስፋና በእቅድ የተያዘ ምንነት ይኖረዋል፡፡ የሕግን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የፍትህ ርትዕ ጥራትና ግዝፈት ይጎላ ዘንድ ይሆን ተብሎ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ያልጠና ዳኝነት ከናካቴው ካልታየው አንድ ነው፡፡ በሙስና ውስጥ የተዘፈቀ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ማንነት ወደ ማህበራዊ ማንነት ማምራቱ አይቀሬ ነው፡፡ የትምህርት ሥርዓት ሲዛባና የጤና ሥርዓት ጤና ሲያጣ፣ ባህል ምስቅልቅል ያለ ሁኔታ ላይ ይወድቃል፡፡ የባህል ወግ ማዕረግ አባ-ከና የሚለውና ባለቤት ያጣ ቤት ሲሆን የሕዝብ ሥነ ልቦና ሳይቀር የሚያዝ የሚጨብጠውን ደርዝ ያጣል፡፡
በመሠረቱ ኃላፊነት የሚሰማው ሕብረተሰብን ለመፍጠር፣ በኃላፊነት የሚቀመጥበትን ቦታ አጥብቆ የተገነዘበ ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ ትክክለኛውን ሹም በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ ምንጊዜም ቢሆን ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ (The right man at the right place እንዲል መጽሐፍ) በጥኑና በጥንቃቄ የተቀመረ መዋቅራዊ ሥርዓት ያሻል፡፡ ነገሮች እንደ ሰንሰለት የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ይህ ሥርዓት በቀናና በሰለጠነ መሰረት ላይ ካልተቀነበበ፣ የላላና ውሽልሹል የሆነ አጥር እንደማለት ይሆናልና በቀላሉ ይደረመሳል፡፡
በተለይ የነቃና የተባ ወጣት ትውልድ፣ ፍሬ ያለው ይሆን ዘንድ ብርቱ ጥረት ይጠበቅበታል፡፡ ከመዋሸት፣ ከመስረቅ፣ የራስን ዕምነት ከማጣት መገላገል ተገቢ ነው:: ምንጊዜም ወደፊትና ወደ ተሻለ ሕይወት ለመጓዝ ዝግጅት ያስፈልገዋል። ወጣቱ በተለያየ ምክንያት እየፈዘዘና እየደነዘዘ ከሄደ እንቅስቃሴው የተዳከመ ይሆናል:: የጥንቱ የስፖርት ባለሙያ ታላቅና መሪ፣ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ሱዳን በኳስ እንዴት ከኛ የተሻለ ሁኔታ ላይ ተገኘ? ሲባሉ፡- ‹‹ቆመን ጠበቅናቸው ጥለውን አለፉ›› ያሉት ይሄንን ዓይነቱን ሁኔታ አስተውለው ነው!!    


Read 13708 times