Saturday, 08 February 2020 15:06

የእሳት ሐብል!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ
Rate this item
(4 votes)

    “ ከተከተልነው … ዘረኝነት፣ ቂምና በቀል በአንገታችን የተጠለቀ የእሳት ሐብል ሆኖ እየለበለበ፣ ለዝንተዓለም እርሱም ይከተለናል--”
                      እንደ ወንፊት ከተበሳሳው ጣሪያ መለስ ብዬ ቤቴን አስተዋልኳት፡፡ ከፍራሼና ከልብሶቼ በቀር ምንም አልነበረባትም፡፡ ከመውጫ በሩ አቅራቢያ መደገፊያ ክራንቼ ቆሞ አንድ እግር አልባ መሆኔን ያስታውሰኛል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የደቡብ አፍሪካ ወጣቶች ቀጥቅጠው ከጣሉኝ በኋላ፣ ዋጋ የለውም ስለተባለ አንድ እግሬን ተሰናብቼዋለሁ፡፡ የሚገርም ነው፡፡ ትናንት እንደ አብዛኛው ሰው ሁለቱም እግሮቼ ከወገቤ ጋር ተጋምደው ሰውነቴን ይሸከሙ ነበር፡፡ ትናንት ተሸክመው በረሃ አሻግረውኝ ነበረ፡፡ አሁን ግን እንዲያ አይደለም፡፡ ረዳት የእግር ብረት አስፈለገኝ፡፡ ፍራሼ መሬት ላይ የተነጠፈው ጭንቅላቴን ወደ ምስራቅ አድርጌ እንድተኛ ሆኖ ነው /አያቴ ድሮ ሲያስተምረኝ፤ ህይወት ያለው ሰው የሚተኛው ትራሱን ወደ ምስራቅ አድርጎ ነው ይል ነበር፣ እንደ ሞተ ሰው ተስፋ ላለመቁረጥ ወደ ምስራቅ እንተራሳለሁ/:: በስተግራዬ ካለው ግድግዳ ላይ “Becareful when you follow the Masses, Sometime ‘M’ is silent!” የሚል ከጋዜጣ የተቀደደ ጥቅስ ተለጥፎበታል፡፡ ከእለታት አንዳንድ ቀን፣ ትዝ ትዝ ባለኝ ማለዳ፣ ወደ ውጪ ከመውጣቴ በፊት አነበውና ለሰከንዶች ቆዝሜ ወደ መንገዴ እዘልቃለሁ፡፡ የበሩን የታችኛውን ደፍ ስረግጥ፣ “አቤቱ ወደ መንጋ እንዳልገባ እርዳኝ!” የሚል ፀሎት አደርሳለሁ፡፡
ከቆርቆሮው መዝጊያዬ ላይ ደግሞ፤ በግራ በኩል ትንሽዬ መስተዋት /በርግጥ ፊቴን ማየት አልወድም፡፡ ግማሹ የተቃጠለ ነው፤ ግና ልቤ ትዕግስት አላደርግ ካለኝ ፊቴን በማየት ልቦና እገዛበታለሁ/፣ በቀኝ በኩል ከላይ በእሳት የተያያዘ ወጣት የሚያሳይ የጋዜጣ ምስል፣ ከታች ደግሞ የፍቅረኛዬ የሩቢን ውብ ፎቶ በወረቀት ላይ አሳድጌ ለጥፌዋለሁ፡፡ መቼም ገጠር ገብቼ እንደማንጋባ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ቢያንስ ላሳለፍነው የፍቅር ወቅት መታሰቢያ ማድረጉ አይከፋም ብዬ ነበር፡፡ ከዓመታት በፊት ክንፈሮቿን ቀምሼ ወደ ስደት ከተሰናበትኳት በኋላ በስልክ እንጂ በአካል አግኝቻት አላውቅም:: ወንድሟ /ጆጆ/ ከሞተ በኋላ ደግሞ ጭራሽ በስልክም መገናኘት አቆምን፡፡ በቃ ተለያየን፡፡ እኔ ህይወትን ከእርሷ ውጪ አይቼው አላውቅም ነበርና የማይዋጥ እብደትና ብቸኝነት ውስጥ ገባሁ፡፡ አሁን በዚህ የአካል ጉድለት ውስጥ ከገባሁ በኋላ ግን እንኳን ለፍቅረኝነት ይቅርና ጭራሽ አይኗን ለማየት አልፈልግም፡፡
በየማለዳው ከወለሉ ጋር የተጣበቀ የቆርቆሮ መዝጊያዬን ገፋ አድርጌ፣ ሰማዩን ለማየት፣ እንደ ዶሮ ውሃ ጠጪ አንጋጥጣለሁ፡፡ የቀን ውበት ጠዋትና ማታ ብቻ ነው ብለው የአድማስ ስር የፀሃይ ስርቅታ ከሚመለከቱ ውስጥ አይደለሁም:: ከሞት እንደተነሳ ሰው ሁለተኛ እድል ተሰጥቶኝ እየኖርኩ ስለሆነ፣ በጸሃይ የሚንገበገበውም ይሁን በዝናብ የሚታጠበው ቀን ለእኔ ውብ ነው፡፡ በህይወት የመኖር ሌላ ተጨማሪ ቀን! በሁለቱ የብረት ቋሚዎቼ ላይ እየተወዛወዝኩ ጉዞ እጀምራለሁ፡፡ ታክሲ አልጠቀምም፡፡ ከራስ ደስታ ሆስፒታል እስከ ሰሜን ማዘጋጃ ድረስ በእግሬ እሄዳለሁ (በእግሬና በክራንች!):: ሁለቱ የእጅ ጡንቻዎቼ፣ በቀን ውስጥ ለብዙ ሰዓት ተደግፌ ስወዛወዝባቸው ስለምውል እየፈረጠሙ መሄዳቸው ይታወቀኛል፡፡ ክንዴ አጎልድሟል፡፡ ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ግን ተለውጫለሁ፡፡ እግሬን ከተቆረጥኩ ጀምሮ አስተሳሰቤ ተቀይሯል፡፡ የድሮው ግልፍተኝነትና ፀበኝነት ከአንድ እግሬ ጋር ተቆርጦ የተወገደ ይመስል በሚያስገርም መልኩ ሰክኛለሁ:: በእርጋታ ነገሮችን አከናውናለሁ፡፡ ዝምታ ማብዛቴ ለራሴም ይታወቀኛል፡፡
ጥቂት እንደተጓዝኩ እንደተለመደው ቁርስ ቤት ጎራ እልና የተለመደችውን ቁርስ እቀምሳለሁ፡፡ ህይወት ቁርስ ቤት ገብቼ እንደተቀመጥኩ ‹‹እስቲ የጣፈጠች ፉል ከሁለት ዳቦ ጋር…›› እላለሁ:: ባልናገረውም ያንኑ እንደሚያዙልኝ ከልምድ አውቃለሁ:: አስተናጋጁ በመጋረጃ ወደተዘጋው ምግብ ማዘጋጃ ጠጋ ብሎ “ቆንጆ ፉል፣ የቤተሰብ…” ብሎ እንደሚጮህ እጠብቃለሁ፡፡
ምናልባት ሞቅ ስላላለ ሊሆን ይችላል በቤቱ ውስጥ በጠዋቱ ሁለት ሰዎች ብቻ ነበርን የተገኘነው፡፡ ከፊት ለፊቴ የተቀመጠው ሰውዬ፤ አንባሻውን ሻይ ውስጥ እየነከረ ይገምጣል፡፡ ሻዩ ቢጫ ሆኗል፡፡ የተጨማደደ ፊቴን የበለጠ ጭምድድ አድርጌ አስተዋልኩት፡፡
‹‹…እንብላ ጌታው…›› እጁን ዘርግቶ አንባሻውን ጋበዘኝ፡፡
‹‹ብላ የተባረከ ይሁን  … እደርሳለሁ!…›› ስል መለስኩ፡፡ በረጃጅሙ ካሳደጋቸው የጣቶቹ ጥፍሮች ውስጥ የተመረገውን ቆሻሻ ስመለከት የራሴን ጥፍሮች አስተዋልኩ፡፡ ጥፍሮቹ የአእምሮ ህመምተኛ ጥፍሮች ይመስላሉ፡፡ ቁርስ የመብላት ፍላጎቴ ሲሸሸኝ ታወቀኝ፡፡
‹‹…ፊትህን ምንድነው እንዲህ ያደረገው በሞቴ?…›› ሲል ፍጥጥ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ዝም አልኩት፡፡ አብሮ አደግ ወንድሜ አሲድ አስደፍቶብኝ ነው ማለት አስጠላኝ፡፡ እንዲህ ፍጥጥ ብሎ ምን አቃጠለህ ብሎ የጠየቀኝ አንድም ሰው አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ሰውዬው ቀውስ ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ፊቴን ወደ ውጪ መለስ አድርጌ መንገዱን ማስተዋል ጀመርኩ፡፡
ሰሜን ማዘጋጃ አደባባዩ አጠገብ ከምትገኘው የደላላ ቢሮዬ (ያው የቆርቆሮ ቤትም ቢሮ ነው! ጆጆ የድለላ ስራ ትባላለች፡፡ የተሰየመችው በጓደኛዬ ስም ነው፡፡) ገብቼ የእለቱን ስራ ለመጀመር እየተጣደፍኩ … ዝንተዓለሜን በሚመስል መልኩ በባላዎቹ መሃል ተወዛውዤ ስደርስ፣ የተኮለኮሉ ብዙ ኮረዶች ይጠብቁኛል:: ብዙዎቹ ሲያዩኝ እንደሚሳቀቁ ስለማውቅ አጎንብሼ በፊት መከለያ ስካርፔ መካከል እጠልቅና በቶሎ ወደ ቢሮዬ እገባለሁ (የፊቴ ጠባሳ እንደሚያሸማቅቅ አውቃለሁ፡፡ እኔ ለራሴ በመስተዋት ሳየው’ንኳ በየእለቱ እደነግጣለሁ:: አልተቀበልኩትም፡፡) የቤት ሰራተኛ፣ የቡና ቤት፣ የሆቴል ወይ የኬክ ቤት አስተናጋጅ …  ወይ ደግሞ ትዳር ፈላጊ ወይም ሌላ ነገር፣ ቤት፣ ቦታ፣ እቃ … የሚገዛ የሚሸጥ…:: እግዚአብሔር ይመስገን ስራ ሞልቶኛል፡፡ ሰዎች “እርሱ ታማኝ ሰው ነው!” ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ምን ያህል ታማኝ እንደሆንኩ እኔ ራሴ አላውቅም፡፡ ምናልባት የዋህነት ጨርሶ በነጠፈበት አለም፣ እንጥፍጣፊ እዝነት በልባቸው ከቀረ ሰዎች መሃል ሳልሆን አልቀርም፡፡ ለሰዎች ይቅርታ በማድረግ፣ ለራሴ ሰላም ለማግኘት የምታትር ሰው ነኝ፡፡
ጨለም ካለው የክፍሉ ጥግ ገብቼ ወንበሬ ላይ ከተደላደልኩ በኋላ ለምዝገባ እዘጋጃለሁ፡፡ የስራ ፕሮግራሜ ጠዋት ስራ ፈላጊዎችን መመዝገብ ሲሆን ከሰዓት ደግሞ ወደየፈላጊዎቻቸው ማድረስ ወይም በቀጠሮ ለሚመጡት ማስረከብ ነው፡፡ ለጥቆ የመጀመሪያዋ ልጅ ትገባለች፡፡ የመጀመሪያዋን ነጭ ወረቀት አውጥቼ ፎርም መሙላት እጀምራለሁ፡፡ (በርግጥ ፎርሙን ማንበብ አያስፈልገኝም፤ ገና ድሮ በቃሌ ሸምድጄዋለሁ፡፡)
‹‹ሙሉ ስምሽ?…›› (እጠይቃታለሁ)
‹‹ምንትዋብ ዋለ … በደምብ አትታየኝም ግን::›› ወደ ጭለማው ጥግ እያጨነቆረች .. ‹‹ክፍሉ መብራት የለውም’ንዴ? ጨለማ ውስጥ ሆነህ ያስፈራል!›› (ለራሴ ፈገግ እላለሁ፤ የውስጤን ጨለማ ለማብራት እየለፋሁ ስለሆነ ነው ብዬ በሃሳቤ እመልሳለሁ፡፡)
‹‹መብራቱን ስላልፈለግሁ ነው፡፡ መታወቂያ ኮፒ ይዘሻል አይደል?››
‹‹ይሄው ኮፒ አድርጌያለሁ!›› (እጇን እየዘረጋች...)፡፡ በአየር ላይ የተዘረጉ ጣቶቿን አስተውላለሁ፡፡ በጥንቃቄ ተከርክመው ባደጉ ጥፍሮች ላይ ደብዛዛ ቀይ ቀለም የተቀቡ ውብ ጥፍሮች፡፡ የደግ ሰው ጥፍር ይመስላሉ! እላለሁ በሃሳቤ፡፡ የሩቢን ጣቶች ይመስላሉ፡፡
‹‹የምትፈልጊው የስራ ዓይነት!?…››
‹‹ለሶስት ወር ጥሩ የሚከፍሉ ሰዎች ጋር የቤት ሰራተኝነት፡፡›› ቀና ብዬ አስተውላታለሁ፡፡ ቀልዷን አልነበረም፡፡
‹‹ለምን ሶስት ወር?!›› እጠይቃለሁ፡፡
‹‹ከሶስት ወር በኋላ ዩንቨርሲቲ ስለሚከፈት ትምህርት እገባለሁ፡፡›› ግንባሬን ከስክሼ አስተውላታለሁ፡፡ በማፈር አንገቷን ትሰብራለች:: ጣቶቿን እያፋተገች … ‹‹ግን!… ኩት ብሔር የሆነ ሰው ቤት ብታስቀጥረኝ ደስ ይለኛል፣ አለ አይደል! ሌላ ቦታ ያስፈራል፡፡ ዩንቨርሲቲ ግቢ ያስመረረኝን ዘረኝነት ድጋሚ ማየት አልፈልግም!…››
ትክዝ ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለ ድህነትና ስለ ዘረኝነት፣ ስለ ቂምና ስለ በቀል፣ ስለ መማርና ስለ መሃይምነት፣ ስለ ክፋትና ስለ ደግነት …  ምናምን ውሉ የማይታወቅ ሃሳብ አዕምሮዬ ውስጥ ይንቀዋለላል፡፡ ደቂቃዎችን በራሴ መንገድ እባትላለሁ፡፡ በመሃል ዛሬን እተውና በሃሳቤ ወደ ጨለማዬ የሚመልስ ሌላ ሃሳብ ይመጣብኛል፡፡
***
አንድ ቀን፤ የቤት አከራዬን የመግቢያ በር ጉበን ወደ ምድር ጎንበስ ብዬ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡ /ወደ ምድር ከመጎንበሱ የተነሳ እንኳን እኔ ቀርቶ የመንደሩ አጫጭር አሮጊቶች ሲገቡ ይጎብጣሉ፡፡/  … አባባ ከድንክ መኝታቸው ላይ ጥቅልል ብለው ነበር፡፡ ወደ መሬት ከሰረጎደችው ድንክ መሃል አንድ ሽማግሌ ተኝተዋል ብሎ ለመገመት ይከብዳል፡፡ (እኔ ራሱ በየቀኑ ከዚያች አልጋ መሃል የመገጣጠሚያ ዘይታቸው አልቆ አጥንታቸው የሚንቋቋ ሽማግሌ እንዳሉ ካላየሁ አላምንም፡፡) ገና ቁጭ እንዳልኩ ጭንቅላታቸው ላይ ጣል ያደረጓትን ጥቁር (በፊት ነጭ የነበረች!) የጋቢ ቁራጭ ዝቅ እያደረጉ ጥያቄያቸውን ያከታትሉ ይጀምራሉ፡፡
‹‹ባለፈው ጥቁሩ ሰውዬ ምን አለኝ ነበር ያልከኝ?!›› በአይኖቻቸው ዙሪያ እንደ ተጠቀለለ ፌስታል የተጣጠፈውን ቆዳ እየዘረጋጉ በአንክሮ ያስተውሉኛል፡፡ በስደት ከምኖርበት ደቡብ አፍሪካ ከተመለስኩ ሁለት አመት አልፎኝ ነበር:: ጥቁሩ ሰውዬ የሚሉኝ ደቡብ አፍሪካዊው ጓደኛዬን ታቦን ነበር፡፡ ፎቶውን አሳይቻቸዋለሁ:: (ጥቁረት፣ ቅላት፣ ነጭነት ወይም ቢጫነት ምን ዋጋ አለው! ፊትህን አንድ ቀን አሲድ ወይ እሳት ካገኘው ቀለምህን ያጠፋዋል፡፡ እያልኩ አስባለሁ፡፡)
‹‹ስለምን?…›› አልኳቸው የወጋችንን ጫፍ ለማግኘት፡፡ ብዙ ነገር አውርቻቸው ነበር፡፡ አሁን የሚጠይቁኝም ገብቶኛል፤ ነገር ግን ሽማግሌው ነገሮችን ስለሚረሱ እንዲያረጋግጡልኝ ፈልጌ ነበር፡፡ በዚህ ሰፈር ቁጭ ብዬ ላወራቸው የምችል ሰዎች እነዚህ ሽማግሌ አከራዮቼን ብቻ ነበር፡፡ ህጻናት ፊቴን ሲፈሩት፣ አዋቂዎች ይጠየፉታል፡፡
‹‹ስለ ነጻነት፣ ስለ ዘረኝነት …አደጋው እንዴት እንደደረሰ?›› ወደ ጨለማዬ ይስቡኛል:: አልጠላውም፣ አልወደውምም፡፡ ምላስ ላይ እንደተቀመጠ የሃሞት ጠብታ ይሰማኛል፡፡ ጭብጥ ኩርምት ብዬ ማውራት እጀምራለሁ፡፡
‹‹እእእ!…›› እንደመባነን እያልኩና ከከንፈሬ ዳርቻ የሚንከባለል የለሃጭ ዝናቤን በእጄ በያዝኳት መሃረብ እየጠረግሁ፡፡ (ከፊቴ መጎዳት ጋር ተያይዞ ከንፈሮቼ በአንድ ጎን የተጎዱ በመሆናቸው እንደ ተቀደደ ኪስ በዚያና በዚህ ጥቂት ጥቂት ምራቆችን አዝረከርካለሁ::) ከዚያም ወሬዬን ለብዙኛ ግዜ በድጋሚ እንደ አዲስ መተረክ እጀምራለሁ ‹‹…አንድ ጊዜ እኔና ታቦ የአፓርታይድ ሙዚየምን እየጎበኘን እያለ፣ ድንገት እንዲህ ሲል ጠየቀኝ … ‹‹ከዚያ ከጓደኛህ (ከጆጆ) ጋር በምን ነበር የተጣላችሁት?››  … ከአገር ቤት አብረን ከተሰደድነው ወዳጄ (አብሮ አደጌና ጎረቤቴ፣ ወንድሜም ነበር፡፡) ከተኳረፍን ብዙ ግዜ ሆኖን ነበር፡፡ ነገርኩት፤ አገር ውስጥ በነበረው ፖለቲካ ምክንያት የእኔና የእርሱ ብሔር የተለያየ ስለነበር ነው፡፡ የበዳይና የተበዳይ ብሔረሰብ ዘሮች ስለተባልን የመጀመሪያው ፍቅራችን ተለውጦ ለመጋደል የሚፈላለጉ ጠላቶች ሆንን!››  አልኩት፡፡
ታቦ በድጋሚ በመገረም አስተዋለኝና ‹‹እናንተ አገር እንዲህ አይነት ሙዚየም አላችሁ?!›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ ሙዚየሙ ለዘመናት በአባቶቻቸውና በአያቶቻቸው ላይ ነጮች ያደረሱትን ግፍ የሚያሳዩበት ነበር፡፡ አሁን ግን የበዳዮቹና የተበዳዮቹ ልጆች በሰላም የሚኖሩበት አገር ፈጥረው መኖር ችለዋል:: እንዲያውም እንደኛ አይነት ስደተኞችን ተቀብለው ይኖራሉ፡፡ (አንዳንዴ የሚነሳው የመጤ ጠል ብጥብጥ ቢያስፈራኝም በእርግጠኝነት አገሬ መጥቼ ከተሰማኝ ፍርሃት የበለጠ እዚያ ሆኜ ፈርቼ አላውቅም ነበር፡፡) እንዲህ አይነት ታሪክም ሙዚየምም የለንም ስል መለስኩለት፡፡
በመቀጠል እንዲህ አለኝ፡፡ ‹‹…እኛ አባቶቻችንና አያቶቻችን ላይ የደረሰውን ሁሉ ይቅር ተባብለን እንኖራለን፡፡ ለዚህም መታሰቢያ ሰርተን እናሳያችኋለን፡፡ በርግጥ በዚህኛው ትውልድ ድረስ ጠባሳው ቢኖርብንና ህይወታችን ያልተቀየረ አያሌ ብንሆንም ቀንበሩን ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አንስብም፡፡ ጀርመኖች ያንን ሁሉ ጥፋት ካደረሱ በኋላ አሁን እንደ ሰው ማሰብ ሲጀምሩ በተፈጸመው ነገር ሁሉ ተጸጽተው ከዓለም የሰው ልጅ ጋር በሰላም ለመኖር ይጥራሉ፣ ለተደረገውም ስህተት መታሰቢያ ሃውልትና ሙዚየም ሰርተው ልጆቻቸውን ለማስተማር ይሞክራሉ፡፡ ሩዋንዳ ላይ ሰላም ለማስከበር እንደዘመታችሁ አውቃለሁ፣ ታዲያ ምን ተማራችሁ? በዘር የመጠፋፋት ልምድ ለመቅሰም ነበር’ንዴ የሔዳችሁት? እናንተ ግን እንደሚባለው የተለያችሁና የተባረካችሁ ህዝቦች እንደሆናችሁ ይሰማችኋል መሰለኝ:: ለዚህም ነው ቶሎ ከሌሎች የማትማሩት:: አማኝ ነን… የአገራችን ስም በመፅሃፍ ቅዱስ ብዙ ግዜ ተጠቅሷል ምናምን ትላላችሁ (እየሳቀ) … ያልገባችሁ ነገር በመፅሃፍ ቅዱስ የተጠቀሰ አገር ሁሉ ዘልዓለም በቸርነቱ አይኖርም፡፡ እንዲያውም ብዙዎቹ አሁን የሉም:: አገሪቱን ዘልዓለማዊ የሚያደርጓት ትውልዶች ናቸው’ኮ:: ከተላለቃችሁ በኋላ የሚቀሩት ዜጎቻችሁ ትልቅ ሙዚየም ሰርተው ጥፋታችሁን ያስጎበኙ ይሆናል፡፡ ብዙ ዩኒቨርሲቲ ከሰራችሁና ትውልድ ካስተማራችሁ ወጣቶቻችሁ ታዲያ እንዴት ከዘረኝነት አልወጡም?...››
‹‹ሲገባኝ ዘረኝነት ትምህርት የሚያሻሽለው ነገር አልመሰለኝም፡፡ ዘረኝነት በሰው ዘረመል ውስጥ የመሸገ ቫይረስ ስለሆነ በሆነ ግዜ ከተደበቀበት ብቅ እያለ ያስጨንቀናል፡፡ ልናጠፋው ሳይሆን አስተሳሰቡን ልናደበዝዘው ነው የምንሰራው፡፡ አስተሳሰብህ ከፍ ሲል መንደራዊነትን እየተውክ፣ አለማዊ ትሆናለህ እንጂ ቀለም በመቁጠርና ክፍል በመሻገር ብቻ አይቀየርም፡፡›› ስል መለሰኩልት፡፡ ‹‹ብዙ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች የመጠፋፋት እቅድ ነዳፊዎች ሆነው ብዙ ቦታ ይታያሉና ከዪንቨርሲቲ መመረቅ ትርጉም የሚሰጥ ነገር አልመሰለኝም ታቦ፡፡ አሁን እኔ አልተማርኩም፤ ግና በዘር ለመጫረስ የሚቀሰቅሱ መንጋዎች መሃል አልገባም፡፡›› ስል አስረግጬ ነገርኩት:: ከዚህም የሚልቅ ብዙ መልስ የነበረኝ ቢሆንም ዝም አልኩ፡፡ ስንቱን ላስረዳው? የአሳ ማስገር ስራ ውስጥ ለኖረ ሰው፣ የአሳው ግማት የሚጀምረው ከጭንቅላቱ መሆኑን ላስተምረው አይቻለኝም፡፡
በመጨረሻ በመተከዝ እንዲህ አለኝ፤ ‹‹ይልቅ ከጓደኛህ ጋር ይቅር ተባባሉና ሰላም አውርዱ፤ በወጣቶች መሃል እንዲህ አይነት ነገር ይደብራል:: የአንድ አገር ልጆች እንዲሁም ደግሞ በሰው አገር የምትኖሩ ስደተኞች ሆናችሁ እንዲህ መሆን የለባችሁም፡፡›› በሃሳቡ ወዲያው ተስማማሁ፡፡ ድሮስ መቼ ጠላኋቸው፤ እነሱ ናቸው ያገለሉኝ፡፡ እናም ታቦ የመከረኝን ያን ዕለት ሳወጣ ሳወርድ አድሬ በማግስቱ ጓደኛዬን ይቅርታ ልጠይቀው አስቤ ወደሚሰራበት መንደር ሄድኩና በሰው አገር እንደ እባብ ተቀጠቀጥኩ፡፡
ሰላይ ነው ብለው የአገሬ ሰዎችና ወንድሜ የምለው ጓደኛዬ አስቀጠቀጡኝ:: ለአገሬው ጎረምሶች ጥቂት ራንድ ከፍለው መጫወቻ እንድሆን ተደረገ:: የነቃሁት ኦክላንድ ፓርክ ከሚገኘው ሄለን ጆሴፍ ሆስፒታል ራሴን ስቼ ለቀናት ከተኛሁ በኋላ ነበር፡፡ አንድ እግሬ በቦታው አልነበረም:: ፊቴም አሲድ ተረጭቶበት ስለነበር ግማሹ አይሆኑ ሆኗል፡፡ ለቀናት አምርሬ አለቀስኩ:: እግሬ ስንቱን በረሃ ተሸክሞ እዚህ ያደረሰኝ አልነበረምን?! ፊቴስ ከሰዎች ፊት መቅረቢያዬ ብዬ የምመካበት ውብ ፊት አልነበረምን?! (ሙሉ አካል ያለን ቢመስለን በማንኛውም ሰዓት ልናጣው እንደምንችል የተረዳሁት ያን ጊዜ ነበር፡፡) አራት ወር በሆስፒታል ስተኛ ግን ሁሉንም ሰዎች ይቅር ለማለት ወስኜ ነበር:: እንዲህም ሆኜ የምትቀረኝን ጥቂት ህይወት (ከኖርኩ!) በጸጸት ላለመኖር ወስኜ ነበር፡፡ ያንን እቅዴን ለታቦ ስነግረው፣ በጣም ተደስቶ አቅፎ.፣ ስሞኝም ነበር፡፡ ግና ውጤቱ እንደዛ አልሆነም፡፡
***
‹‹ታዲያ ስራውን መቼ ታገኝልኛለህ?!…›› ስትል ከሃሳቤ አናጠበችኝ፡፡ የዓለም ድራማ የሚገርም ነው፡፡ አንዳንድ ሰው በበጋ ለሚማርበት በክረምት ሰው ቤት ተቀጥሮ ለመስራት ያስባል፤ ሌላው ደግሞ አስተማሪው ከቤቱ ደጃፍ ቢመላለስ እንኳ አይፈልገውም፡፡ ‹በጣም የምትፈልገው ይርቅሃል፣ የምትጠላው በዙሪያህ ያንዣብባል!› እንዲሉ፡፡
‹‹ምኞትሽ እንደዛ ከሆነ ለምን ኬክ ቤት አትሰሪም፡፡ ጥሩ ቲፕ ታገኛለሽ፣ የተሻለ ብር ማጠራቀም ይሳካልሽ ይሆናል፡፡›› ስል ምክር ቢጤ ጣል አደረግሁ፡፡
‹‹…አይ አይሆንም፤  እሱንም ሳላስበው ቀርቼ አይደለም፡፡ ማደሪያዬንና ጠዋት ማታ የምበላውን ማሰብ አልፈልግም፡፡ የዚህ አገር ቀጣሪ ደግሞ በስትሮው እንደሚመጠጥ ጭማቂ ነው ጉልበትህን የሚመጠምጠው፡፡ አምና እንደዛ ነበር የሰራሁት፣ ግን ለትምህርት የሚሆን ምንም ጉልበት ሳይተርፈኝ ነበር የወጣሁት፡፡ ጥሩ አልነበረም፡፡ ትንሽ የተሻለ የሚከፍሉ የኩት ብሔረሰብ የሆኑ ቤተሰቦች ጋር ብታገኝልኝ ይሻለኛል፡፡ ወንደላጤም ባይሆን ጥሩ ነው፡፡›› እየፈገገች፡፡
ቀና ብዬ አየኋት፤ እንደ ቅቤ ቅል የሚያብረቅርቅ ጠይም ውብ ፊትና የጸዱ የጣት ጥፍሮች አሏት፡፡ ራሴን ታዘብኩት:: ምንም ያህል ውብ ብትሆን በእኔ በረዶ ገላ ውስጥ የሞቀ ደም እየዞረ አልነበረም፡፡ (አሁን ደግሞ ሌላው ችግሬ የቀጣሪዎችን ብሔር መጠየቅ ሊኖርብኝ ነው፡፡ መቼም የልጅቱ ጥያቄ ሳይገባኝ አልቀረሁም፡፡ ለራሴ ፈገግ ብዬ ሳበቃ እንደምደውልላት ነግሬ አሰናበትኳት፡፡ ተረኛዋም እስክትገባ ወደ ራሴ ሀሳብ ተመለስኩ…)
***
(Necklacing) በደቡብ አፍሪካ በ1980ቹ ሰዎችን (በተለይ በእነሱ የተቃውሞ ትግል ወቅት ለፖሊስ ይሰልላሉ ብለው የሚጠረጥሩትን የራሳቸውን ሰው) አሰቃይተው የሚገድሉበት መንገድ ነበር፡፡ የእሳት ሐብል ማለት ነው፡፡ በሰውየው አንገት ላይ ቤንዚን የተሞላ ጎማ ያጠልቁና ይለኩሱታል፡፡ ሰውየው ለመሞት በአማካይ ከሃያ ደቂቃ በላይ የስቃይ ጊዜ ይወስድበታል፡፡ የሰው ስጋ እንደ ጧፍ እየተንቦገቦገ ሰዎች ጥብሱን እያሸተቱ በዙሪያው ይጨፍራሉ፡፡ የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ባለቤት ዊኒ በዚያን ወቅት ‹‹..በክብሪት እንጨታችንና በሐብላችን አገራችንን ነፃ እናወጣለን!…›› ብላ ንግግር አድርጋ ነበር ይባላል፡፡ በወቅቱ ብዙዎች ቢቃወሙትም ድርጊቱ ዘመን ተሻግሮ አሁንም ይፈጸማል፡፡  
ደቡብ አፍሪካዊው ታቦ ከአገሬ ውጪ ያገኘሁት ውድ ወንድሜ ነበር፡፡ ሆስፒታል ተኝቼ እንዳለሁ ተመላልሶ አስታመመኝ:: ማንም የአገሬ ሰው መጥቶ አልጠየቀኝም ነበር፡፡ እኔ ላይ በደረሰው ነገር እጅግ ተናዶ ስለነበር ቀጥሎ ያደረገው ነገር ግን የእብደት ነበር፡፡ ወዳጆቹን አስተባብሮ ጆጆ ከሚኖርበት መንደር ሄዱ:: አፈላልገው ያዙትና አሰቃይተው ደበደቡት:: ኋላም የጎማ ሃብሉን አጥልቀው አቃጠሉት:: ያ ከመግቢያ በሬ ላይ ሰቅዬ በየቀኑ ፎቶውን የማየው የእርሱ ነው፡፡ የአንድ ታዋቂ ጋዜጣ ፎቶግራፈር ያነሳውና በጋዜጣው የፊት ገፅ ላይ የታተመ፡፡ እናም ከቀናት በኋላ ታቦ የጋዜጣውን ቅጂ ከፅሁፍ ማስታወሻ ጋር አድርጎ ሰጠኝ:: ድርጊቱን ያደረገው እርሱ እንደሆነና በነገሩ እንደተጸጸተ ገልፆ፤ የሁለት መቶ ራንድ ኖቶች አክሎ መልካሙን ሁሉ ከተመኘልኝ በኋላ ጥሎኝ ወጣ፡፡
ከወራት በኋላ አገሬ ገብቼ ከባዶ መስራት መለማመድ ጀመርኩ፡፡ ድሮ ስወጣ ሙሉ አካል ነበረኝ፣ ስመለስ ጎድያለሁ፡፡ ድሮ ወንድምና ጓደኛ ነበረኝ፣ አጥቼዋለሁ፡፡ ድሮ የምትጠብቀኝ ፍቅረኛ ነበረችኝ፣ አሁን የለችም፡፡ ድሮ የመኖር ጉጉት ነበረኝ፣ አሁን ተራ ህይወት ምንም ምኞት ሳይጨማመርበት እኖራለሁ፡፡ ድሮ ያልነበረኝ አሁን ያገኘሁት ትዕግስት አለኝ፡፡ ትዕግስት ስጨምር ቂም በቀል አጥፊ መሆኑን ስለተረዳሁ ከውስጤ አጽድቸዋለሁ፡፡ (ወይም መስሎኛል!)
***
የምትለጥቀው ደንበኛ ስትገባ፣ ከገባሁበት የሃሳብ ወጥመድ በድጋሚ ወጣሁና አይኖቼን ጎልጉዬ አፈጠጥኩባት፤ በመቀጠል በአንድ እግሬ ተስፈንጥሬ ከመቀመጫዬ በመነሳት ወደፊት ለፊቴ አሰገግሁ፡፡ ልጅቱ ሁኔታዬንና የተቃጠለ ፊቴን ስታይ ደንግጣ በመጮህ ዘልላ ከቤት ወጣች፡፡ ራሴን መቆጣጠር ተስኖኝ ነበር:: እየተስፈነጠርኩ ተከትያት ወጣሁና በትኩረት አየኋት፡፡ አዎን ራሷ ነበረች፡፡
‹‹….አ ው ቀ ሽ ኛ ል!?…›› አልኳት ድምፄ እየተንቀጠቀጠ፡፡  
‹‹እንዴ!? … ኸረ እኔ አላውቅህም! … በስመአብ!…›› ስትል አማተበችና ወደ ኋላዋ ሸሸች፡፡ ‹‹…ድሮም ከቤቱ ስም ጀምሮ ደብሮኝ ነበር! … ሆሆ!…›› እያለች ጉዞዋን ቀጠለች:: ‹ሩቢ ውዴ!› አልኩ በለሆሳስ፡፡ አዎን በርግጠኝነት ራሷ ነበረች፡፡ እንደ ግንድ ተጎርጄ፣ እንደ ከሰል ነድጄና ተቃጥዬ አይታኝ፣ በርግጥስ እንዴት ታውቀኛለች? ከወለሉ ላይ ዝርፍጥ ብዬ ተቀመጥኩና ፊቴን በመሃረቤ መጠራረግ ጀመርኩ፡፡ ለሃጭ ወይም ላብ አልነበረም የጠረግሁት፣ እምባዬ ከአመታት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ እየተንፎለፎለ ነበር፡፡ ሩቢ እንኳ በማትለየኝ ደረጃ ጠፍቻለሁ፡፡ አሁን ሌላ ሰው ነኝ ማለት ነው፡፡ ከተከተልነው … ዘረኝነት፣ ቂምና በቀል በአንገታችን የተጠለቀ የእሳት ሐብል ሆኖ እየለበለበ፣ ለዝንተዓለም እርሱም ይከተለናል፡፡


Read 1158 times