Print this page
Saturday, 08 February 2020 15:45

“የፕሮፌሰሩ መቀስ” በወፍ በረር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

      “ቅንጅትን ያፈረሰው የነሃይሉ ሻውል፣ ብርሃኑ ነጋ እና የነልደቱ አያሌው የስልጣን ጥማት ነው”
                        
         በብዙዎች ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትና አክብሮት የሚቸራቸው ጐምቱው የሰብአዊ መብት ተሟጋችና ምሁር፣ የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ህይወትን ከልጅነት እስከ አዋቂነት ዕድሜያቸው (ሙያና አገልግሎታቸውን ጨምሮ) የሚዘክር “የፕሮፌሰሩ መቀስ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ባለፈው ጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር ተመርቋል፡፡ በዚህ የዘጋቢ ፊልም የምረቃ ሥነ - ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም የፕሮፌሰሩ ጓደኞችና አድናቂዎች ታድመው ነበር፡፡ ክሩቤል ከበደ፣ ዳግማዊ አዱኛና ጥላሁን ሰማው የተባሉት ወጣቶች ናቸው፡፡ ዘጋቢ ፊልሙን ያዘጋጁት:: ፕሮፌሰሩ ከልጅነት እስከ እውቀት አድርባይነትና አስመሳይነት ተጭኗቸው ስሜታቸውን ከመግለጽ ወደ ኋላ ብለው እንደማያውቁ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ተንፀባርቋል::
በምረቃው ላይ የተለያዩ ስጦታዎችና ምስጋናዎች የቀረቡላቸው ፕ/ር መስፍን፤ ባደረጉት ንግግር “በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ለሰራሁት ሥራ ለተሰጠኝ ምስጋናና አክብሮት እግዚአብሔር ይመስገን፤ ነገር ግን እኔ የማዝነው ከኔ በላይ ለሀገራቸው የሠሩ በውትድርና ደማቸውን ያፈሰሱ፣ ብዙ አስታዋሽ ያጡ ሰዎች፣ በየስርቻው ወድቀው የቀሩ፣ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በከፍተኛ ስቃይ ላይ የሚገኙ አሉ፤ ስለ እነሱ በጣም አዝናለሁ፡፡ እባካችሁ ለእኔ ከሰጣችሁኝ አክብሮትና ምስጋና ቀንሳችሁ ለእነሱ ስጡልኝ” ብለዋል፤ ሳግ እየተናነቃቸው፡፡
ፕሮፌሰሩን በሶስቱ መንግሥታት የሥልጣን ዘመን የሚያውቋቸው ጓዶቻቸው በዘጋቢ ፊልሙ ላይ በምስክርነት የተካተቱ ሲሆን ከነዚህም መካከል ኃይሉ አርአያ (ዶ/ር)፣ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ የደርጉ ሁለተኛ ሰው ኮ/ል ፍሰሐ ደስታና ያዕቆብ ሃ/ማሪያም (ዶ/ር) ይገኙበታል፡፡
ፕሮፌሰሩ ትግል የጀመሩት  በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ (1928) ወቅት በህፃንነታቸው እንደነበር ይገልፃሉ - በዘጋቢ ፊልሙ፡፡ እዚሁ በመዲናዋ ጉለሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልደው ያደጉት እኚህ ጎምቱ ምሁር፤ በጣሊያን ላይ ሲፎከርና ሲሸለል እየሰሙ ነው ያደጉት፡፡ በወቅቱ አሁን ስፔይን ኤምባሲ ያለበት ቦታ፣ አንድ ቡና ቤት በራፍ ላይ አንድ ጣሊያናዊ እግሩን አነባብሮ መቀመጡን ያስታውሳሉ፡፡ ከዚያም ድንጋይ አንስተው ቅልጥሙን ሲሉት፣ ጣሊያናዊው ተንፈራፍሮ ተንፈራፍሮ ይነሳል፤ ሲሻለው ሊደበድባቸው ይሮጣል፤ እሳቸው ሮጠው አንድ ሱቅ ውስጥ ለመደበቅ ቢሞክሩም ባለ ሱቁ አላስገባም ብሎ ይከለክላቸዋል፡፡ “አቤት! አቤት!  በዚያ ጫማው እስኪበቃው ተጫወተብኝ” በማለት ገጠመኛቸውን ያጋራሉ:: በዚያን ወቅት የዘጠኝ ወይም አስር ዓመት ልጅ ቢሆኑ ነው፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ፣ ወደ ህንድ አገር ሄደው ጂኦግራፊ መማራቸውን፣ በ21 ዓመታቸው ክብርት ስንዱ ገብሩ በሚመሩት እቴጌ መነን ት/ቤት ያስተምሩ እንደነበር፣ ዳይሬክተሯ ለህክምና ውጭ ሲሄዱ ቦታው ክፍት በመሆኑና ብዙ የሥራ ብልሽቶች በመፈጠራቸው ራሳቸውን ዳይሬክተር አድርገው በመሾም፣ ስራውን ማስተካከላቸውን፣ ስንዱ ገብሩ ከውጭ ተመልሰው ሲመጡ ግን፣ ቦታቸውን ወርሰው ስለጠበቋቸው ማኩረፋቸውን… ከዚያም ት/ቤቱን ለቀው መውጣታቸውን… ፕሮፌሰሩ ይገልፃሉ፡፡
አሜሪካን አገር ለትምህርት በሄዱበት ወቅት የነጭ የበላይነት እየተሰበረ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ  ጥቁሩ በባቡርም ሆነ በአውቶብስ ውስጥ ከነጮቹ ጋር እኩል መቀመጥ የቻለበት፤ ግን ደግሞ ነጮቹ ይህን መቀበል ተስኗቸው የሚበሳጩበት ወቅት እንደነበር የሚያስታውሱት ፕሮፌሰሩ፤ “እኔም ይህን ስለማውቅ፣ አውቄ አይ አይና… ቆንጆ ነጭ ሴት የተቀመጠችበትን ቦታ መርጬ ቁጭ ስል… ደሟ ሲንተከተክ ስመለከት እስቅ ነበር” በማለት ያስረዳሉ፡፡
ወደ አገራቸው ተመልሰው በአዲስ አበባ በዩኒቨርስቲ ማስተማር ከጀመሩ በኋላ በ66 በተከሰተው የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ድርቅና ረሃብ ውስጣቸው በመነካቱ፣ ክስተቱን ለአለም ለማጋለጥ ቡድን አቋቁመው ጥረት ያደረጉ ቀዳሚው ሰው ቢሆኑም “የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ” እንዲሉ፤ በኋላ ድርቁን በማጋለጥ ረገድ እነ ጆናታን ድንቢልቢ ቀዳሚ ተብለው ምስጋናና ዕውቅናውን መውሰዳቸውን አርቲስት ደበበ እሸቱና ሌሎች ጓደኞቻቸው በዘጋቢ ፊልሙ ላይ መስክረዋል፡፡  “በዚህም ስራቸው ፕሮፌሰሩ አደባባይና ሀውልት ሊሰየምላቸው ይገባ ነበር” ሲሉ በቁጭትም ተናግረዋል፡፡ ለነገሩ ራሳቸው ፕሮፌሰሩም ኢትዮጵያ የሰራ ሰው የሚመሰገንባትና የሚሸለምባት አገር እንዳልሆነች ይገልፃሉ፡፡ “አንድ ጊዜ አንድ ድርጅቱ የሰራሁትን ሳይገልጽ በረጅም ጊዜ የሥራ ቆይታ ልሸልምህ ነው አለኝ ከኔ ይልቅ እዚህ ግቢ ይቺ ኤሊ በጣም ስለቆየች ሸልሟት አልኳቸው” በማለት ታዳሚውነ አስቀውታል፡፡
በድርቁ ወቅት በህዝቡ ላይ የደረሰውን ሰቆቃ የሚያስቃኝ ኤግዚቢሽን በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ማሳየታቸውን ተከትሎም የተማሪ ቁጣ መቀስቀሱን ፕሮፌሰሩ ያስታውሳሉ፡፡
የዘመኑን የተማሪዎች ንቅናቄ ይደግፉት የነበረ ቢሆንም፣ በኋላ መልኩን እየቀየረ “ፋኖ ተሰማራ እንደ ሆች ሚኒ… እንደ ቼ ጉቬራ” የሚባል ነገር ሲመጣ፣ አላማው ስለተቀየረ ከተማሪዎቹ ጋር በሀሳብ መለየታቸውንም ይናገራሉ፡፡ እነ ዋለልኝን በወቅቱ “ምንድን ነው ዓላማችሁ? ምንድን ነው የምትፈልጉት? አላማችሁን እወቁ” ሲሉ መክረዋቸው እንደነበርም አልሸሸጉም፡፡
የ66ቱን ድርቅ የደበቁትንና አስተዳደራዊ በደል ያደረሱትን ሰዎች እያጣሩ ለመክሰስና ለፍርድ ለማቅረብ የተቋቋመውን አጣሪ ኮሚሽን በሊቀ መንበርነት የመሩት ፕሮፌሰር መስፍን እንደነበሩ፣ ለ60ዎቹ ትልልቅ የአገሪቱ ሰዎች መገደል የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር ከነበሩት ዶ/ር በረከተአብ “መሳሪያው በእጃችሁ ነው” የሚል ሀሳብ መስማታቸውን፣ ፕሮፌሰሩም ቃል በቃል ባይሆንም፣ በዚሁ ሀሳብ መስማማታቸውን በመጽሐፋቸው የገለፁት ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታ፤ በዘጋቢ ፊልሙም ይህንኑ ቃላቸውን ደግመውታል:: ፕ/ር መስፍን ግን ፈጽሞ አይቀበሉትም፡፡  ‹‹ኮሎኔል ፍስሃ የፃፈው መጽሐፍ አሉባልታና አሉሽ አሉሽ የሞላበት ነው፤ እከሌ እንዲህ አለኝ፤ እንዲህ አለኝ… ከማለት ውጭ አንድም እውነትነት የለውም:: ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ ግን ይህን ሆኜ፣ ይህን አድርጌ በማለት በራሱ ታሪክና እውነታ ላይ የተመሰረተ መጽሐፍ ነው የጻፈው” ሲሉም ይተቻሉ፡፡ “ከአጣሪ ኮሚሽኑም ጋር በተያያዘ በመጽሐፉ የተፃፈው” ሀሰት ነው፤ እኔ ይሁንታም ሆነ ምንም ያልኩት ነገር የለም፤› እኔ እንኳ ሰው ይገደል ብዬ ልመክር፣ የሞት ፍርድ የማልቀበል  ሰው ነኝ” ሲሉ ውንጀላውን ውድቅ ያደርጉታል::
በደርግ ጊዜም ቢሆን ከኮሎኔል መንግሥቱ ሀይለማርያም ጋር እንደተናነቁ ነው የኖሩት:: ‹‹አካሄዳችሁ ትክክል አይደለም፤ ጥፋት እየጠፋ ነው፤ ይህን ማስተካከል አለባችሁ” በሚል ፊት ለፊት ቀርበው በግልጽ ሲሞግቱ፣ ኮሎኔል መንግስቱም በብስጭት ሲጦፉ በዘጋቢው ፊልም ላይ ይታያል፡፡ ‹‹ያኔ እኔም በሰላም እመለሳለሁ አላልኩም ነበር›› ይላሉ ፕሮፌሰሩ፡፡ ህወሃት ኢሕአዴግ እየገፋ ሲመጣ፣ የሽማግሌዎች መንግሥት ተቋቁሞ ምርጫ እንዲካሄድ ያደረጉት ጥረትም ተወስቷል፡፡
ኢህአዴግ ከገባ በኋላም ከዩኒቨርሲቲ ከተባረሩት 44 ምሁራን አንዱ ነበሩ፡፡ ‹‹ዋና ዋና ምሁራንን ከላይ ግፍፍ አድርገው አስወጡን፤ ዝቃጭ ብቻ እንደቀረ የሚያሳየው እኛ ስንባረር ተቃውሞ አለመኖሩ ነው›› ይላሉ ፕሮፌሰር መስፍን፡፡ ከዩኒቨርሲቲ መባረራቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያንና ሕዝቡን በምን ላገልግል ብለው ሲያስቡ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ››ን ለጡረታ ብለው ባጠራቀሙት ገንዘብ ማቋቋማቸውን የሚገልፁት ፕሮፌሰሩ፤ የዚህ ጉባኤ ዋና አላማ ኢትዮጵያዊያን የመጨረሻ ትንሽ የሚባለውን መዋጮ እያዋጡ ከውጭ ዕርዳታና ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ነበር ይላሉ፡፡ ነገር ግን ያሰቡት ባለመሳካቱ የግድ የውጭ ድርጅቶችን በር ማንኳኳት አስፈለገ፡፡ የውጭ ድርጅቶቹ ምላሽ ግን ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ‹‹እንድንረዳችሁ ከፈለጋችሁ መስፍን ከጉባኤው መሪነት ይነሳ›› ነበር ያሉት፡፡ ሌላ አማራጭ በመጥፋቱም ከመሪነት መልቀቃቸውን ይገልፃሉ፡፡
የ97ትን ምርጫ በተመለከተ የቅንጅት አመሰራረት፣ የእስር ቤት እንግልት፣ ቀስተ ደመና የተባለው ድርጅት እንደነ ኢዴፓ ያሉትን ፓርቲዎች አቀራርቦ ለማጠናከር ያለመ እንጂ ራሱን የቻለ ፓርቲ እንዳልነበርና በኋላ ፓርቲ እንደሆነ… ሁሉንም በዝርዝር ያብራራሉ፡፡ ቅንጅት ተጠናክሮ መቀጠል ሲገባው ሁሉም ወደ የራሱ ፓርቲ እየጎተተ፣ በስልጣን ጥማት መፈራረሱን ያጋለጡት ፕሮፌሰሩ፤ እርሳቸው የስልጣን ጥማት ኖሮባቸው እንደማያውቅ ይናገራሉ ከህወሃት ኢሕአዴግ በስተቀር ሁሉም መንግስት ለሹመት እንደጠየቃቸውና እንዳልተቀበሉ በመግለጽ ‹‹ለቅንጅት መፍረስ የስልጣን ጥማት በነበረባቸው ሰዎች” ምክንያት እንደሆኑም ይገልፃሉ፡፡ የስልጣን ጥመኞቹም “ነፍሱን ይማረውና ሀይሉ ሻውል (ኢ/ር)፤ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና ልደቱ አያሌው ናቸው›› በማለት፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ይሄንን የሰሙት ከፕሮፌሰር መስፍን ጎን ተቀምጠው ነው፡፡
‹‹ጊዜው ዘወርዋራ ነውና እኛ ታስረን በቆየንበት በ97 ታስረው እስር ቤት ተገናኘን፤ እናም እርሶ ሀይለስላሴንም፣ ደርግንም ኢሕአዴግንም ሲቃወሙ ነው የኖሩት፣ ምንድን ነው ነገሩ ብዬ ብጠይቃቸው ካጠፋ ቅንጅትንም እቃወመዋለሁ አሉኝ›› ሲሉ ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ በሰጡት ምስክርነት ገልፀዋል፡፡
 የ1 ሰዓት ከ55 ደቂቃ ርዝመት ያለው ዘጋቢ ፊልሙ፤ በሶስቱ ወጣት የፊልም ባለሙያዎች ያለ ማንም ድጋፍ የተሰራ ሲሆን በአቅም ውስንነት ሳያካትቷቸው የቀሩ ሰነዶች እንዳሉ ጠቁመው ለጥናትና ምርምር ስራ መነሻ እንዲሆን በማሰብ ያቅማቸውን እንዳበረከቱ ተናግረዋል ወጣቶቹ፡፡ አቅም ቢፈቅድላቸውና ቢችሉ ኖሮ ለውዝግቦቹ ጥርት ያሉ ምላሾችን የሚሰጡ መረጃዎችን በማካተት ከክርክር መውጣት ይቻል ነበር ያሉት ወጣቶች፤ እንዲያም ሆኖ ይህ ዘጋቢ ፊልም ለቀሪው ትውልድ ማስተማሪያ፣ ለጥናትና ምርምር ደግሞ መነሻ ሆኖ ስለሚያገለግል ጠቃሚነቱ የሚያጠራጥር አይደለም ብለዋል፡፡   


Read 13129 times