Saturday, 08 February 2020 15:51

የታላቅነታችን ምስጢር - መንፈሳዊነታችን

Written by  ወልደጊዮርጊስ ይሁኔ-
Rate this item
(1 Vote)

በአክሱም ዘመነ መንግስት ኢትዮጵያ ጠንካራ ኢኮኖሚ ነበራት፡፡ የመገበያያ ሳንቲሞችንም መጠቀም ጀምራለች፡፡ በኢኮኖሚ ጠንካራ እንድትሆን ያደረጋት ቀይ ባህርን በመቆጣጠር ከህንድ፣ ከሮማንና ከሩቅ ምስራቅ ሀገራትና ግዛቶች ጋር የነበራት የንግድ ግንኙነት ነው፡፡
በወቅቱ የነበሩት ነገስታት እጅግ ኃይለኛ ጦረኞች ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት የሰሜን አፍሪካን ጨምሮ የምዕራብ አረብ ሀገራትን ሁሉ በግዛታቸው ውስጥ አስገብተው ያስተዳድሩ ነበር፡፡ በወቅቱ ጠንካራ የሆነ የምድር ጦርና የባህር ኃይል መገንባት ችለዋል:: በኪነ ህንጻ ደረጃ እንደ አክሱምና ላሊበላ አይነት በዓለም ላይ ያልተለመዱ የስነ ህንጻ ውጤቶችን አንጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በዓለም ላይ ከነበሩ ገናና መንግስታት አንዱ እንደነበር እኛም ዓለምም የሚያውቀው ታሪክ ነው፡፡ ምንጩ ደግሞ መንፈሳዊነት በመሪዎችም ሆነ በህዝቡ ውስጥ ሰርጾ የገባ ስለነበር ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ህዝብ እንደ ህዝብ፣ ነገስታትም እንደ ነገስታት ሃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን በፍጹም ቅንነትና ጽናት ይከውኑ ነበር፡፡
ስለ ጥንታዊ ስልጣኔያችን ጎይተኦም ታዲዮስ በመጽሐፉ “ወርቃማ ዘመን” በሚል ንዑስ ርዕስ እንዲህ ሲል አስፍሯል፡- ‹‹በኢትዮጵያ ምድር የተስተዋሉ ስልጣኔዎችን በሁለት ደረጃ ከፍለን ማየት እንችላለን:: ወርቃማ ዘመንና የጨለማ ዘመን በሚል:: ወርቃማ ዘመን ስለመኖሩ ምንም የሚያጠራጥር ነገር የለውም፡፡ የአክሱም ወርቅ ሳንቲሞች፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የጎንደር ቤተ መንግስትና የሐረር ግንብ ስለ ወርቃማ ዘመናችን ህያው ምስክር ናቸው፡፡ ይህ ወርቃማ ዘመን የሆነበት ምክንያት በዋናነት ከወርቅ  ማስገኛ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በወርቅ ሳንቲሞች የሚገበያይ መንግስት ወርቃማ ከመሆኑ ባሻገር አሻራዎቹ በአሁኑ ሰዓትም ጭምር ወርቅን የሚያስገኙ መሆናቸው ነው፡፡››
የዚህን ወርቃማ ዘመን የነበረበትን ምክንያቶች ሲያብራራ፤ ‹‹በአስተዳደር በኩል ጠንካራ እንደነበሩ፤ ህዝብ ፍጹማዊ የሆኑትን የህዝብ ስራዎችን በማከናወን ኃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን መወጣት በመቻላቸው እንዲሁም ንጉስ ወይም ንጉሰ ነገስት፣ የነጋሲነት ግዴታ የሆነውን ሀገርን የማሳደግ፣ ከባዕድ ጠላት መከላከል እንዲሁም ግዛትን ማስፋፋት›› ይገኙበታል በማለት ነው::
ህዝብ በስርዓት ከተመራና ግዴታውን ከተወጣ እንዲሁም ነገስታት ህዝባቸውን በቅንነትና በአገልጋይነት መንፈስ ማስተዳደር ከቻሉ፣ ሀገር በሁለንተናዊ መስክ እንደምታድግ፣ ሰላሟና ነጻነቷ የተጠበቀ እንደሚሆን እርግጥ ነው፡፡ ስለ ህዝብና የመንግስት ስርዓት መሰረታዊና አስፈላጊ መሆን ‹‹የነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ስራዎች” በሚል ርዕስ የታተመው መጽሐፍ፤ ‹‹አዕምሮ የሌለው ህዝብ ስራት የለውም:: ስራትም የሌለው ህዝብ የደለደለ ኃይል የለውም፡፡ የኃይል ምንጭ ስራት እንጂ የሰራዊት ብዛት አይደለም፡፡ ስራት ከሌለው ሰፊ መንግስት ይልቅ በሕግ የምትኖር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሰራለች፡፡››
ስለ ስርዓት ጠቀሜታና ህዝብንም በስነ-ምግባር የተገነባና ለሀገሩ መልካም ስራ እንዲሰራ ለማድረግ መሪዎች በህግና በህግ ብቻ መመራትና ማስተዳደር እንደሚገባቸው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋሪያት ተክለ ማሪያም ‹‹ኦቶባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ )›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ሲያብራሩ፡- ‹‹ንጉስነት ከተፈጥሮ ላንድ ሰው የተሰጠ ዕድል አይደለም:: በሰዎች ኑሮ ላይ በስምምነት የተፈቀደ የውል አገባብ ነው፤ ወኪሎች የሚመርጡት በሕዝብ ፈቃድ መሆኑ ቀርቶ፣ በንጉሱ ፈቃድ እንደ ሹመት ይመርጣሉ ተብሎ ህጉ ተለወጠ ፡፡ ተደላዳይነትና ከንቱ አወዳሽነት በሕዝቡ ባህሪ ውስጥ እንዲለመድ ተደረገ፡፡ ስለዚህ፣ ንጉስ ምንም ቢያጠፋ አልምተሃል ይሉታል እንጂ፣ አጥፍተሃል ለማለት የሚደፍር አይገኝም:: ቢገኝም እንኳ ፣ በከንቱ መከራ መቀበል ይተርፈዋል እንጂ ምንም ማድረግ አይችልም::›› ሲሉ ንጉስና ሹመት በህግና በስርዓት ብቻ መመራት እንደሚገባቸው ያስገነዝባሉ፡፡
‹የዓሳ ግማቱ ከጭንቅላቱ› እንዲል የሀገራችን ህዝብ፣ የመሪዎች ሰብዕና ከተበላሸ ህዝብም ይበላሻል፡፡ ‹‹መኳንንቱ እና መሳፍንቱ፤ ነገስታቱም ህይወታቸውን ለጠጅ፣ ለጮማና ለፍትወት አሳልፈው ሲሰጡ ታላቋ ኢትዮጵያ ጸሐይ እንደነካው በረዶ እየሟሟች ሄደች:: ‹ውሃ ከምንጩ ይደፈርሳል› እንደሚባለው፤ የታላላቆችን አርአያ በመከተል፣ ሕዝቡ ሥነ ምግባር የሌለው ስድና ባለጌ ሆነ፡፡ በገዥዎችም እምነት አጥቶ ተስፋ ቆረጠ፡፡›› (የቴዎድሮስ እንባ፣ 403- 4) ከዚህ ሃሳብ የምንረዳው ፍሬ ነገር፣ ንጉስ ወይም የሀገር መሪ ሰብዕና ለህዝቡ የስነ ምግባር ደረጃ፣ የስራ ተነሳሽነት መንፈስ፣ የአገልጋይነት ባህሪና ለመሳሰሉት ጠባዮች ሁሉ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ነው፡፡ በዚሁ መጽሐፍ ላይ አጼ ቴዎድሮስ ደግሞ ስለ መሪነት ስነ ልቦና እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት እንደመሆናችን መጠን የሚጠቃ ህዝብ መሪ ለመሆን አንፈልግም፡፡ የተራበ፣ የተከፋ፣ የደንቆሮ ህዝብ ንጉስ መሆን አንሻም::… የትልቅ ህዝብ መሪ ልቅ ይሆናል፡፡ የጎስቋላ ህዝብ ገዥም ትንሽ ነው፡፡››
ከላይ በተነሳሁት ሀሳብ መሰረት፣ መሪዎች ትልቅ ሀሳብና ርዕይ አንግበው መስራት እንደሚገባቸው መገንዘብ የመሪዎቹም ሆነ የተመሪዎች ግዴታ ነው፡፡ ትልቅ ራዕይና አዲስ ነገር ይዘው የሚነሱ መሪዎች፣ በርካታ ፈተናዎች (ተግዳሮቶች) እንደሚያጋጥሙት የታወቀ ቢሆንም፣ ራዕያቸውን ለመተግበር ወደ ኋላ ማለት ግን ከመሪነት ሰብዕና አይጠበቅም፡፡ ‹‹መብራት ሳይነድ አይበራም” እንደሚባለው፤ የዓለምን ታሪክ ብንመለከት አዲስ ሥርዓት የሚያወጣ ንጉስ ሁሉ በሕይወቱ  ሳለ መከራ አይለየውም፡፡ አውራ ደመኛው ያየዋልና፡፡ ደግነቱም ከሞተ ከብዙ ዓመታት በኋላ ነው፡፡›› (ነጋድራስ፣13) ካሉ በኋላ ቀጥለውም አጼ ቴዎድሮስ የሀገራቸውን ህዝብ በእውቀትና በስራ ሊለውጡ ቆርጠው በተነሱ ጊዜ የገጠማቸውን መከራ ለአብነት በመጥቀስ ያነሱትን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡
‹The Barefoot Emperor › የተሰኘውን በፊሊጵ ማርስዲን የተጻፈውን መጽሀፍ ብሩክ በቀለ መኮንን ‹የቴዎድሮስ ዕዳ - አንዲት ኢትዮጵያ› በሚል ርዕስ ተርጉሞ ባሳተመው መጽሐፍ፤ አጼ ቴዎድሮስ ለለውጥ በተነሱበት ወቅት ህዝባቸው እንዴት እንዳልተቀበላቸውና በዚህም ተበሳጭተው በህዝቡ ላይ ስለ ወሰዱት እርምጃ አስረውት ለነበረውና ለሚያቀርቡት እንግሊዛዊው ሃርሙዝ ራሳም፣ የሚከተለውን ተስፋ በመቁረጥና በሀዘን ስሜት ውስጥ ሆነው እንደነገሩት ተጽፏል፡፡
‹‹ህዝቡ ህይወቱና ኑሮው ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን ሞከርኩ፡፡ እንደሰለጠነው ዓለም ሰዎች ህይወታቸው የተሻሻለ እንዲሆን መንገዱን ላሳያቸው፣ ስለ ሀገሬና ለህዝቤ የማስበው ይሄ ነው ብዬ አላማዬን ገለጽኩላቸው፡፡ ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው ህይወት የተሻለ ተስፋ እንዳለ ላሳያቸው ጣርኩ፡፡ እነሱ ግን ክፉ በመሆናቸው ሀሳቤን ሳይቀበሉት ቀሩ፡፡ … ይሄ ጭንቅላቱ የደነደነ ዙሮ የማያስብ ህዝብ እኔ ለሀገሬ የማስበው ምን እንደሆነ አልገባውም:: ስለዚህ ይህ ህዝብ እየሄደበት ካለው ጠማማ መንገድ ለመመለስና ሀገሩን ወደ ተሻለ ህይወት የሚቀይረውን ራዕይ እንዲያውቅ ለማድረግ መቅጣት፣ መቀጥቀጥ ማስተካከል አለብኝ፡፡›› በማለት ነግረውታል፡፡
በመሪዎች ሰብዕና ብቻ አንድ ሀገር ልታድግ እንደማትችል ከላይ ለማንሳት ሞክሬያለሁ:: ምክንያቱም የህዝብ ምግባር፣ የታማኝነት፣ የመስዋዕትነት፣ ከተፈጥሮ በሚገኝ የግብረ-ገብነት ኃይል በመነሳት ካልሰራ ሀገር ልታድግ ስለማትችል ነው፡፡ ይህን ሀሳብ በደንብ የሚያስረዳልኝ የደራሲ ከበደ ሚካኤል “ስልጣኔ ማለት ምንድን ነው?” በሚል ርዕስ የተጻፈ ሀተታ ነው፡፡
‹‹ታላቅ ዓላማ ለመድረስ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የግል ጥቅሙንና የግል ሀብቱን ለጠቅላላው ያገር ሀብትና ለጠቅላላው የስልጣኔ እርምጃ ሲል መስዋዕት ማድረግ የግድ ይሆንበታል፡፡›› (ከበደ፣ 108 ) ስለዚህ ለለውጥ በንጉስ ወይም በመሪ ሰብዕና እና ተግባር የሚጀመር ቢሆንም መሪውን የማይሰማ፣ አንዱ ለሌላው የማያስብ ከሆነ፣ ለለውጥና ለእድገት ያለው እሳቤና የመንፈስ መነሳሳት፣ በህዝቡ ላይ ካላደረ ሀገር ልትለወጥ አትችልም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት፣ ከኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ስለ ቀደሙት ነገስታት ሰብዕና በማጉላትና በማክበር የገለጹትን ሀሳብ አጠር አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
‹‹አጼ ምኒልክ እና አጼ ኃይለ ስላሴ ከኛ በምን ያህል እንደሚሻሉ አማርኛ አይገልጸውም፡፡ ሀይለኛ የሆነ (wisdom) እውቀትና ጥበብ አላቸው፡፡›› በማለት የአጼ ምኒልክን ቤተ መንግስት አሰራር እንደ አብነት ጠቅሰዋል፡፡ ቀጥለውም ‹‹ እነዚህ መሪዎች (spiritualy connected) መንፈሳዊ እንደነበሩ፣ ለአካባቢ (environment) ያላቸው መረዳት፣ ከቦታ አመራረጥ ጀምሮ ከኔ ጋ እንኳን አላነጻጽረውም፤ በስሜት አንድን ነገር ቶሎ የመገንዘብ ወይም የመረዳት ችሎታ ነበራቸው›› ብለዋል፡፡
የቀድሞ ነገስታት ስለ ጥበብ የነበራቸውን ዋጋ ሲያነሱ፤ ‹‹አጼ ዳዊት በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቅዱስ ያሬድ አስደምሟቸው፣ ሊቅነቱ አስደንቋቸው ሁሌ እንደሚባለው እጃቸውን በአፋቸው እንደጫኑና ይሄ ድርጊት ደግሞ የሊቁን የጭንቅላት ውጤት እንዲወጣ እንዳገዘ፤ ከዛም አልፎ ንጉሱ ቅዱስ ያሬድ ከአክሱም ቤገ ምድርና ጣና በሄዱበት ጊዜ ሁሉ አግዘዋል፡፡ ላሊበላን የወሰድን እንደሆነ ለኪነ ህንጻ ባላቸው ፍቅር ነው ትንሽቷን እየሩሳሌም ለመገንባት አልመው፣ ይህን ድንቅ ስራ ሰርተውልን ያለፉት፡፡ አጼ ዳዊትን ብንወስድ ለጥበብ ቦታ ስለነበራቸው፣ ለማሲንቆ ተጫዋቾች ሰገነት አሰርተዋል:: ሠርጸ ድንግልን ብናይ የቅዱስ ያሬድ የድጓ ምልክት ተሟልቶ እንዲወጣ ድጋፍ አድርገዋል፡፡›› ከዚህም የነገስታት ሰብዕና፣ ምኞትና መንፈሳዊነት ከፍተኛ እንደነበረ እንረዳለን፡፡
የእሳቸውን ሀሳብ የሚያጠናክርልን የሚከተለው የፍቅሬ ቶሎሳ ሀተታ ነው፡፡ ‹‹ የጥንት ነገስታት ልክ እንደ አባታቸው የሳሌሙ ንጉስ እንደ መልከጼዴቅ ንግስናና ክህነትን (ፖለቲካን እና ቅስናን) አጣምረው ይዘው ህዝባቸውን በፍትህና ርትዕ ያስተዳድሩ ነበር::›› (ገጽ 64 )
ከላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርና በደራሲው ከተገለጹት ሀሳብ የተገነዘብኩት ፍሬ ነገር፣ አያቶቻችንና አባቶቻችን በህዝባቸው ላይ ጉዳት የማያደርሱት፣ በፍቅርና በርትዕ ይመሩ ስለነበረ ነው፡፡ ከእነሱ በላይ የሚጠይቃቸው ሌላ አካል እንዳለ ስለሚያስቡ፣ በህዝባቸው ላይ መከራና ስቃይ አላደረሱም፡፡
የመሪዎች ሰብዕና የተበላሸ ሲሆን ሙሰኞችና ጥፋት የሚያደርሱ ሆነው ሲገኙ ‹የማህበረሰቡ ውጤት ናቸው ፡፡› በማለት ለጥፋታቸው መከላከያ የሚሆን ብሂል አይሰራም፡፡
‹ መሪ › ማለት በራሱ የሚሰጠው ትርጉም ከሚመራው ህዝብ የሚቀድም፣ ከህዝቡ የተሻለ የማሰብ ችሎታና ብቃት ያለው ማለት ነው፤ … መሪነት በራሱ መክሊት ነው፡፡ መክሊት ማለት ሰው በተፈጥሮ ያለው የተለያዩ ሀብታት ሲሆኑ እነዚህም በትምህርት፣ በልምድና በጥረት እየካበቱ የሚሄዱ ናቸው:: እንደ እግር ኳስ ተጫዋች፣እንደ አትሌቶችና እንደ ድምጻዊያን ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ የጥንት ኢትዮጵያዊያን በንጹህ ህሊናቸውና በጥልቅ የመንፈሳዊነት ስሜት በመመራት ከዋክብትን የመረመሩ፣ ስነ - ፍጥረትን በመዳሰስ ባህረ ሐሳብን  የጻፉ፣ መሬት እንደምትዞር ሳይንስ ሳይደርስበት ያመኑና ያስተማሩ፣ እንደ አክሱምና ላሊበላ አይነት ያልተለመዱ ስነ ህንጻዎችን ያነጹ፣ ቅዱስ ያሬድ ከአውሮፓውያን 700 ዓመታት ቀድሞ የዜማ ምልክቶችን መፈልሰፍ የቻለ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊያን በክርስትና ክንፍ (ክርስትና የሚለውን እኔ ጥልቅ መንፈሳዊነት ብየዋለሁ) ላይ ሆነው አየር አየራት ወጥተው፣ እመቀ እመቃት ወርደው፣ የነገሮችን ባህርይ ለመመርመርና ለመረዳት፣የሕሊና ጥረት አድርገው፣ ከብዙ የሐሳብ ትክክለኝነትና ጽርየት ደርሰዋል፡፡›› ( እጓለ፣ 73)
ጥንታዊ ስልጣኔያችንን የቀድሞ ዘመን የግሪክ ታሪክ ጸሀፊዎች፣ ከሆሜር ( 850 ዓ.ዓ ) ጀምሮ እንደ ሄሮዱተስ ባሉ የታሪክ ሊቃውንት፣ ጥንታዊ ኢትዮጵያዊያን የታወቁ መርከበኞች፣ ከዓለም ቀድመው በፈጣሪ ያመኑ፣ ጠቢባንና ሰው አክባሪ እንደነበሩ ተጽፎላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ድንቅ የሆነው ‹የመንፈሳዊነት› ፍልስፍና በተጠናና በተደራጀ መልክ እንደ ሌሎች ሀገራት ስያሜ ተሰጥቶት (ካፒታሊዝም፣ ኮምኒዝም…) በመጽሐፍ ተሰንዶ ስላልቀረበ  ‹ኢትዮጵያ ፍልስፍና የላትም › አያስብልም፡፡ በኑረታችን ውስጥ ተግባብተን አምነንበትና እንደ ገዢ ሀሳብ ወስደን እስከተገበርነው ድረስ ፍልስፍና አለን:: ምክንያቱም የአንድ ህዝብ የስነ ምግባር ህግጋት፣ እሴቶች፣ ባህሉና በጠቅላላው በህይወታቸው ያሉ ጥንተ ነገሮች ( principles) መልክ ይዘው የሚገኙ፣ የአንድ ህዝብ መንፈስ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ይህ መንፈስ ደግሞ ፍልስፍና ይባላል፡፡
የታላቅነታችን ምስጢር መንፈሳዊነታችን ነበር፡፡ አሁንም የከፍታችን ፍላጎት የሚሳካው በሱ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ የተሳሳተና የእኛ ባልሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ርዕዮት መመራታችን፣ የተሳሳተ የትምህርት ፍልስፍና መከተላችን፣ በውጭና በሀገር ውስጥ የሚዲያና የኪነ ጥበብ አሉታዊ ውጤቶች፣ በተዛባ የታሪክ አስተምህሮትና የመሳሰሉት ችግሮች ይጠበቅብናል፡፡

Read 335 times