Saturday, 08 February 2020 15:55

በሃሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

   ‹‹እውነተኛው ሰይጣን ድንቁርናችን ነው››
                                    


              አንድ ጓደኛችን ሲያጫውተን፡-
“አንተ እንደዚህ አርገሃል”
“ያንቺ ግን ይብሳል”…እየተባባሉ ባልና ሚስት ይጨቃጨቃሉ አሉ፡፡ ሁለት ሰይጣኖች ደግሞ ከደጅ ሆነው ያዳምጣሉ፡፡
“ገብተን ብናሟሙቅ ይሻላል” ሲል አንደኛው
“ምን አስቸኮለን? ራሳቸው ይጠሩናል” አለው ጓደኛው፡፡
ጭቅጭቁ ቀጠለና አቶ ባል ተበሳጭቶ፡-
“በቃ ሰይጣኔን አመጣሽው” በማለት ቱግ አለ፡፡
ይህን የሰማው ሁለተኛው ሰይጣን፣ ምን እንዳለ ታውቃለህ? መጨረሻ ላይ እነግርሃለሁ፡፡
***
“እንግዳ ከሚሆንብኝ የብዙ ሰዎች አስተሳሰብ አንደኛው፡- መሆን የሌለበት ነገር እንዳይሆን መከላከል እየቻሉ ዝም ብለው ይቆዩና፣ ያስከተለውን ጉዳት ተመልክተው ‹ኡኡ!› ይላሉ፡፡ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ (The dog barked after the Lara van passed) እንደሚባለው፡፡” ይለናል ናይቲንጌል፡፡
ወዳጄ፡- የበለፀገ ብሔራዊ ቋንቋ ባላቸው ሀገራት፣ ለቁጥር የሚያታክቱ የታሪክና የአንትሮፖሎ፣ የሳይንስና የጥበብ፣ የፍልስፍናና የሌሎች ዕውቀቶች ማዳበሪያ መፃሕፍት ይታተማሉ፡፡ ቀደም ብለው የተዘጋጁትም በጥንቃቄ ይቀመጣሉ፡፡ በሌሎች ቋንቋዎች የተፃፉትም እየተተረጐሙ ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ በቋንቋቸው ውስጥ የሚመላለሱትን ስነቃሎች፣ አባባሎች፣ ተረትና ምሳሌዎችንም በመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች ለሚማሩ ህፃናት ቀለል ባለ መንገድ (በስዕል፣ በተረት፣ በመዝሙር ወዘተ) እያሰናዱ ያቀርቡላቸዋል፡፡
ይህን የሚያደርጉት ቀጣዩ ትውልድ በሰላምና በነፃነት ለመኖር በሚያደርገው ውጣ ውረድ ውስጥ ሊያጋጥመው የሚችለውን ፈተና አስቀድሞ በመገመት፣ ተጠንቅቆ እንዲራመድና ሳይደናገጥ እንዲወጣው ለማድረግ ነው፡፡ በኛም ሀገር “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ፣ ሳይርቅ በቅርቡ፣ ሳይደርቅ በርጥቡ፣ ሳይቃጠል በቅጠል ወዘተ” እንደሚባለው ማለት ነው:: የሰይጣን ጆሮ አይስማና፣ የሰለጠኑ አገሮች ሃብታምና ጠንካራ ከሆኑበት አንደኛው ምክንያት ከስነቃል መማራቸው ነው፡፡ ህመምና ባህሪ ስር ከሰደደ በኋላ ወደነበረበት ለመመለስ ፈተናው ይበዛል፡፡ የሚከፈልበት ዋጋም ቀላል አይደለም:: የማንነት ባህሪ መሠረት ከአስተሳሰብ ይጀምራል፡፡ ታላቁ ላዖፁ፡-
Watch your thoughts; they become words
Watch your words; they become actions
Watch your actions; they become habits
Watch your habits; they become character
Watch your character; it becomes your destiny. ….በማለት ይመክረናል፡፡
ወዳጄ፡- ሰው የሁለት ተቃራኒ መንፈስ ውሁድ ነው፡፡ የበጐና የክፉ፡፡ አንደኛው ሰብዓዊነቱን ሲያጐለብት ሌላኛው ይፈታተነዋል፡፡ ይኸ ተለዋዋጭ ባህሪው በስራው፤ በጓደኝነት፣ በቤተሰብ፣ በስጋዊና መንፈሳዊ ጥቅሞቹ፣ እንዲሁም በፖለቲካና ዲፕሎማሲ ስርዓትና ሌሎች ማህበራዊ ትስስሮች ውስጥ በሚያደርገው ተሳትፎና ግንኙነት ላይ ይንፀባረቃል፡፡ በሚሳሳትበት ጊዜ ተፈጥሮ ባደለችው የመታረም፣ የመፀፀትና ይቅር የመባባል ፀጋ ካልተጠቀመ ግን ዕኩይነት በውስጡ ይሰለጥናል፡፡ ዕኩይነት “እያጠፋ መኖር”ን እያለማመደ፣ ድብቁን የአውሬነት ፀባይ ይፋ ያወጣል፡፡ ቀስ በቀስም በራስና በሌሎች ላይ እንዲጨክን ያደፋፍረዋል፡፡ ይኼን ጉዳይ የሰይጣን ጆሮ አይስማ!!
ወዳጄ፡- ኑሮህ አስተሳሰብህን ይወስነዋል (The way you live determines the way you think) ይላሉ ሊቃውንት፡፡ ጥቃት፣ መገለል፣ ጭቆናና በጥቅም መደለልን ባህሉ ባደረገ፣ የሞራል ልዕልናው በላሸቀ (Corrupt ባደረገ) ማህበረሰብ ውስጥ በስነምግባር ሳይኮተኮት፣ ከአረም ጋር እየታገለ የሚያድግ ዜጋ፣ ፍርሃትና ይሉኝታን አያውቅም፡፡ በስሜታዊነት ስለሚሰክር በኑሮ መስታወት ውስጥ የሚያየውን የሌሎችን ገጽ ከራሱ ጋር እያነፃፀረ ፍላጐቱን ለማርካት ሲል የማይሞክረው ነገር የለም፤ የማይገለብጠው ድንጋይ፤ ወንጀል መስራትን ጨምሮ፡፡ ይህንንም የሰይጣን ጆሮ አይስማ!!
ወዳጄ፡- በብዙ ማህበራዊ ኑሯችን ላይ ብልጭ ድርግም ሲሉ ቸል ያልናቸው፣ ግብረ ሰብዓዊ ዕፀፆች እየደረጁ መጥተው እንደ ስርዓት ሊቆሙ ምንም ያህል አልቀራቸውም፡፡ ዜጐች በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር ሆነዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፏል፤ የአምልኮ ነፃነትና የቀደምት ስልጣኔ ምልክቶች አድርገን የምንቆጥራቸው ባህላዊ ቤተ እምነቶቻችን ተደፍረዋል፡፡ ምዕመን ያለ ርህራሄ ተጨፍጭፈዋል፡፡ እዚህ ጋ “የሰይጣን ጆሮ አይስማ” ብንል ሰይጣን ራሱ ይታዘበናል፡፡
ወዳጄ፡ ዳዴ የሚለውን ለውጥ አሽመድምዶ፣ ተስፋ የጣልንበትን የዕድገትና የስልጣኔ ጭላንጭል ደርግሞ፣ የህዝባችንን አእምሮ ወደ አረመናዊነትን ለመመለስ የሚደረገው ውንብድናና አጉል ምኞት በዚህ ዘመን ተቀባይነት የለውም፡፡ ይኸን ስል ጮክ ብዬ ነው:: ሰይጣኑ በደንብ እንዲሰማ!
ወዳጄ፡- በዚህ ዘመን ህግጋቱን ቀይሮ ጊዜ ያለፈበትን አሮጌ ጨዋታ እንደገና ለመጫወት መሞከር ሞኝነት ነው፡፡ ምክንያቱም የጨዋታው ዓይነት ተቀይሯል፡፡ ጨዋታው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሆኗል፡፡ ኦሳማ ቢንላደንን ጨምሮ የብዙ አሸባሪ ድርጅቶች መሪዎች እንዴት ያሉበት እንደታወቀ ልብ ይሏል፡፡ የሰይጣኑም ዕጣፈንታ እንደዛ ነው፤ እስከነመረቡ፡፡ አሁን አሁን በቴክኖሎጂ ሻይረሶችንና ባክቴሪያዎችን በቀላሉ መለየት የመጨረሻ ትንሽ ጉዳይ ነው፡፡ እንኳን የግመል ሌባን!!
ወዳጄ፡- የኔትወርክ ነገር ሲነሳ፣ ጓደኛዬ የነገረኝ ትዝ አለኝ፡፡ ዘወትር ረፋድ ላይ እንደሚያደርገው መኖሪየው አካባቢ ከሚገኘው የቀበሌ መዝናኛ የጀበና ቡና ሊጠጣ ጐራ ይላል፡፡ አንድ ቀን ግን ቡና ከምትቀዳው ልጅ ራቅ ብሎ፤ ፊቱን አዙሮ ከተቀመጠው ሰው በስተቀር ማንም ባካባቢው አልነበረም፡፡ ዘበኛ፣ አስተናጋጅ፣ በቦታቸው የሉም፡፡
“ምነው ጭር አለ?” አላት
ዓይኗ በእንባ እንደተሞላ ዝም አለች፡፡ እሱ አገልግሎት እንዳያገኝ የተደረገ “ሴራ” ነበር:: አገልግሎት ለማግኘት መጀመሪያ ተከፍሎ ደረሰኝ ይቆረጣል፡፡ ካሸሯ ደግሞ ተደብቃለች፡፡ ዞር ብሎ ቡናውን እየተንቀባረረ የሚጠጣውን ሰው ሲያስተውል፣ በግል ጉዳይ የተጣላው የ“ዘመኑ” ፖለቲካ አጋፋሪ ነው፡፡ ዓላማው “ከፈለግን እንዲህ እናደርግሃለን፣ ሁሉም ነገር እንደ ትናንቱ በቁጥጥራችን ስር ነው” ለማለት ነው፡፡ በሱ ቤት ኔትዎርኩን ተጠቅሞ ማንነቱን ማሳየቱ ነው፡፡ አላዋጣውም እንጂ፡፡ ያልገባው ነገር “እንዲህ የምናደርገው እኛ ነን” ባይልም፣ ማን ምን እንደሚያደርግ ቀድሞ የታወቀ ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ ጓደኛዬ አያኮርፍም፡፡
“በኔና በለፍቶ አደሮች መሃል እንኳን ሰይጣን ነፋስ አይገባም” ይለኛል፡፡ በኔና ባንተ መሃከልም እንዲሁ፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፣ የጥንዶቹ ጠብ ተባብሶ ባልየው፡-
“በቃ ሰይጣኔ መጣ!” ብሎ ቱግ ሲል ቅድም “ራሳቸው ይጠሩናል፣ አትኸኩል” ያለው ሰይጣን
ጓደኛውን፡- “አላልኩህም! ይኸው ጠሩን!” አለውና ገቡ፡፡ ጠቡን አካርረው አጋደሏቸው:: የሆነው ሆኖ ወዳጄ፡- እውነተኛው ሰይጣን ድንቁርናችን አይመስልህም? ወይስ…?
ሠላም!!

Read 282 times