Saturday, 08 February 2020 16:00

የጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን ‹‹የአምስት ደቂቃ ታሪኮች›› …

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

     ብዙዎቻችን በምክር አዘል መጻሕፍቱ የምናውቀው ዴል ካርኒጌ የሚታወቅበት ዘርፍ የስነልቡና ሳይንስ ይሁን እንጂ የታላላቅ ሰዎችን የሕይወት ታሪክ ሲጽፍም ተዐምረኛ ነው፡፡ በተለይ ሲያሳጥርና የሕይወት ታሪክ አንጓዎችን ሲመርጥ ለጉድ ነው፡፡ ሰውየው በታሪክ አጋጣሚ ከታላላቅ ሰዎች ጋር ቀረቤታ ስለነበረው ነገሮቹን በታሪክ መዝገብ የሚያሰፍረው በግምት ሳይሆን በአብዛኛው በዐይንና ጆሮ እማኝነት ነበር፡፡
በመሆኑም አጫጭርና ረጃጅም የሕይወት ታሪኮችን አጣፍጦና በርብሮ የመስራት አቅሙን አሣይቷል፡፡ ከረጃጅሞቹ የአብረሃም ሊንከንን ታሪክ የሰራበት ውበትና ጥልቀት ለኔ ተዐምር ነው፡፡ የሚስቱን፣ የጄኔራሎቹን፣ የጠላቶቹን ወገንና የሊነከንን ድክመቶች ሳይቀር አብጠርጥሮ አሳይቷል:: ሜሪ ቶድን እንደርሱ የሳላት ሰው ያለ እስከማይመስለኝ ድረስ እስከዛሬም ለአድናቆቴ መቆሚያ አላገኘሁለትም፡፡
ካርኒጌ አጫጭር ቁመና፣ ግን ጥልቅ ብርበራ ያደረገባቸውን መጻህፍት ቀደም ሲል ማንበቤን ባስታውስም፣ አሁን ግን በቅርቡ ተወዳጁና ድምጸ ወርቃማው ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን፣ ‹‹የ5 ደቂቃ ታሪኮች›› በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ መልሶት አንብቤያለሁ፡፡
ደጀኔ ጥላሁን ከዚህም ቀደም የደራስያንን አስደናቂ ታሪኮች ከሌላ ሰው ጋር ያሳተመ ሲሆን ኢትዮጵያ ሬድዮ በሚሰራበት ጊዜ ‹‹ከመጻሕፍት ዐለም›› በተሰኘው ፕሮግራም እናውቀዋለን:: ሸጋ ድምጹና ለዛ ያለው ንባቡም በልባችን ታትሟል:: ምናልባትም ደጀኔ ለብዙ ደራስያን መፍለቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ ደጀኔ የብዙዎቻችን ባለ ቀለም ትዝታ ነው፡፡
ደጀኔ ስለተረጎመው መጽሐፍ በመግቢያው ላይ ሲነግረን እንዲህ ይላል፡-
…በመጽሐፉ ውስጥ የቀረቡት የሰላሳ ስምንቱን ታላላቅ ሰዎች የሕይወት ታሪክ፣ ከተለያዩ ምንጮች ልታገኙ ብትችሉም፣ የካርኒጌ ግን በፍጹም የተለዩ ናቸው፡፡ ካርኒጌ በዘመኑ የነበሩትን ራሱ በአካል በመገኘትና በሕይወት ያልነበሩትን በነበሩበት አካባቢ ድረስ በመሄድ የቅርብ ሰዎቻቸውን ማለትም ልጆቻችውን ወይም ቤተሰቦቻቸውን ወዘተ ቃለ መጠይቅ በማድረግ ነበር መረጃዎቹን ያሰባሰበው፡፡….››
በርግጥም አንዳንዶቹን ባለታሪኮች ብዙዎቻችን ልናውቃቸው እንችላለን፤ ግን ደጀኔ በሌላ ቦታ መግቢያው ላይ እንዳለው ያልተሰሙ ብዙ ጉዳዮች አሏቸው፡፡
የታሪኩ መጀመሪያ ላይ ያለው ሰው ታላቁ ሩስያዊ ደራሲ ሌዎ ቶልስቶይ ነው:: ቶልስቶይ ደግሞ የሩሲያ ዜጋ ብቻ ሳይሆን ታሪክዋም ነው:: ‹‹ከእንግሊዝ ታሪክ 85 ፐርሰንቱ የሼክስፒር ታሪክ ነው›› እንደሚባለው፣ በይፋ ባይነገርም፣ በታሪክ ገጾች ላይ የሰፈረው ገድሉ ይህንን ያረጋግጣል፡፡
በመጽሐፉ እንደምናየውም  ቶልስቶይን በሚመለከት ብቻ ሃያ ሶስት ሺህ ያህል መጻህፍት ተጽፈዋል፡፡ ሃምሳ ስድስት ሺህ መጽሄቶችና ጋዜጦች ስለ ቶልስቶይ ጽፈዋል:: እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ታሪክ መሆን ከየት ይመጣል!! ታዲያ ቶልስቶይ እንደ ብዙዎቹ የዐለማችን ደራስያን፤ በድህነት ጎጆ የተወለደ፣ በእንጀራ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ የባተተ አልነበረም፡፡ ይልቅስ ከናጠጡ የሩስያ መኳንንት ቤተሰብ የተወለደና  በወርቅ መሃል የተገኘ ሞልቃቃ ነበር፡፡
መጽሐፉ እንደሚለው፤ በወጣትነቱ ዘመን በመኳንንት ዘርነቱ የሚኮራ፣ ጥጋበኛና ለአረማመዱ እንኳ ቄንጥ የነበረው ነው:: አለባበሱም በቅንጦት የተሞላ ነበር፡፡ ይህ ግን በሕይወቱ ማምሻ አብሮት አልዘለቀም:: አለባበሱም ግድ የለሽ፣ አመጋገቡም እንደ ተርታው ሰው ሆኖ ነበር፡፡ ይህንን ያደረገው ደግሞ ህይወቱ በኢየሱስ አስተምህሮ ስለተለወጠ ነው፡፡ ሃብት ከማከማቸት ይልቅ ሃብቱን ለደሆች በማከፋፈል ራሱን ባዶ አድርጎ በመጨረሻም የሞተው፣ በተወለደበት ቤት ዐይነት ያሸበረቀ ቪላ ውስጥ ሳይሆን፣ በባቡር ጣቢያ በደሃ ገበሬዎች ተከብቦ፣ በሳምባ ምች በሽታ ታሞ  ነበረ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ተደናቂ ያደረጉት “አና ካራኒና” እና “ዋር ኤንድ ፒስ” ሲሆኑ እሱ ግን በነዚህ መጻሕፍት ደስተኛ አልነበረም:: በሕይወቱ መቋጫ አካባቢም የሚጽፋቸው ጽሑፎች ድህነትን ስለ ማስወገድ፣ስለ ፍቅር፣ስለ ሰላም የሚሰብኩ  ነበሩ፡፡
ሌላው በመጽሐፉ ውስጥ የተካተተው ከ1858 እስከ 1919 ዓ.ም የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበረው ቴዎዶር ሩዝቬልት ነው፡፡ ሩዝቬልት፤ እንደ ቢን ለንደን ጆንሰንና መሰል አጋጣሚ ገጥሟቸው በምክትል ፕሬዚዳንትነት ዋይት ሀውስ ገብተው፣ በሟቹ ፕሬዚዳንት እግር የተተኩ ነበሩ፡፡ ሩዝቬልት ዐይኖቹ ከሩቅ ማየት የማይችሉ ቢሆኑም፣ በአልሞ ተኳሽነቱ ግን የተዋጣለትና አፍሪካ መጥቶ አናብስት ማደን የቻለ ነበር፡፡ ሌላው ጠባዩ ዐሳ ማጥመድ ያለመውደዱ ነው፤ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ አሰልቺ መሆኑ ነው፡፡ ወፍ ለማደን ደግሞ ለወፎች ያለው ፍቅርና ርህራሄ ከልክሎታል፡፡
የዚህ ፕሬዚዳንት ሌላው ገራሚ ነገር፣ ንባብ መውደዱ ሲሆን አንዴ ካምፕፋይር ላይ ሆኖ የሼክስፒርን ሐምሌት እያጣጣመ ሳለ፣ ሸንጦት ለከብት ጠባቂው ድምጹን ከፍ አድርጎ አንብቦለት ነበር፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ አንዱ የሚገርም ገጠመኝ፤ አንዱን የዋሽንግተን ፖስት ጋዜጠኛ ዋይት ሃውስ የጋበዘበት አጋጣሚ ነው፡፡ ጋዜጠኛውም የተለየ ዜና አግኝቶ ለመዘገብ በመጓጓት ደርሶ ነበር፡፡ ሩዝቬልትም ጋዜጠኛውን ይዞ ዋይት ሃውስ ግቢ ውስጥ ወዳለ አንድ የተቦረቦረ ዛፍ ወስዶ ያገኘውን የአንድ ጉጉት ጫጩት አሳይቶታል፡፡ ሌላ ይህን መሰል ጉዳዮችም አሉት፡፡ በተለይ እስትንፋሱ ሊያበቃ ሲል የተናገረው ነገር ይጠቀሳል፤ ‹‹እስቲ መብራቱን አጥፉት›› ነበር ያለው፡፡
ሼክስፒርም መጽሓፉ ካካተታቸው ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ስለ ሼክስፒር ከተጻፈው አሳዛኙ ነገር ትዳሩ እክል የገጠመው መሆኑ ነው:: የወደዳትን ሳይሆን ያልወደዳትን እንዲያገባ ተደርጎ ነበር፤ በዚያ ላይ ያገባት ስምንት ዐመት ያህል በዕድሜ ትበልጠው ነበር::
የሼክስፒር እናት፣ አባት፣ እህት ትንሽ ልጁና ትልቅዋ ልጁም ማንበብና መጻፍ አይችሉም ነበር፡፡ ሼክስፒር በሕይወት ያልነበረ ሰው መሆኑን የሚናገሩ ሰዎችም ብዙ እንደነበሩ መጽሐፉ ይነግረናል፡፡ ሼክስፒር በሞት ሲለይ በዘመኑ መለኪያ ሀብታም ከሚባሉት ጎራ የሚመደብ ነበር:: ተዋናይ ሆኖም ጠቀም ያለ ገንዘብ አግኝቷል፤ የሁለት ቤተ-ተውኔት ድርሻም ነበረው፤ በሪል ስቴት እንደተሳተፈና አራጣ ያበድር እንደነበርም ተጠቁሟል፡፡ ይሁንና ለሚስቱ ከአንድ አልጋ በቀር አንዲት ሳንቲም አልተወላትም፤አልጋውንም የተወላት በኋላ ሃሳቡን ቀይሮ ነው፡፡
ቀደም ባለው ዘመን ስመ ገናና የነበረው የዓለማችን ቱጃር ሮክ ፌለርም፣ የደጀኔ መጽሐፍ ውስጥ ተካትቷል፡፡ ሮክ ፌለር ድሃ ሳለ፣ ሚስት ተከልክሎ እንደነበር ስንገነዘብ፤ ‹‹አትመልከቺ ሱፍ፣ አትዪ መኪና፣/እኔም እገዛለሁ እድሌ ሲቃና/ ሲል ያቀነቀነው ከያኒ ይታወሰናል፡፡
ታዲያ ይህ ደሃ የነበረ ሰው በልግስናው ዓለምን ጉድ ያስባለ ሆኗል፡፡ ሰውየው በእራሱ ደረጃ ከነበሩ ቱጃሮች በተሻለ ሁኔታ እድሜ ጠግቦ ነው የሞተው፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ የማስፈራሪያና የግድያ ዛቻ ደብዳቤዎች ቢደርሱትም፣ ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ጤናና ዕድሜ አጣጥሟል፡፡ በመጨረሻ ያሸለበውም በ97 ዓመት ዕድሜው ነበር፡፡ በሰው ልጆች ታሪክ የመጀመሪያው ቢሊየነር ነበር፤ ሮክ ፌለር:: መጽሐፉ የሄለን ኬለርን ሕይወትም ያስቃኛል፡፡


Read 1773 times