Saturday, 08 February 2020 16:01

8ኛው የበጐ ሰው ሽልማት የዕጩዎች ጥቆማ የካቲት 1 ይጀመራል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 የሽልማት ድርጅቱ ቋሚ ጽ/ቤት ከከተማ አስተዳደሩ አግኝቷል
                                 

               ለአገርና ለወገን አርአያነት ያለውን ታላቅ ተግባር ያከናወኑ ኢትዮጵያውያንን በየዓመቱ እያከበረ የሚሸልመው የበጐ ሰው ሽልማት” ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ ለሚያካሂደው ሽልማት የእጩዎችን ጥቆማ ከየካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ መቀበል እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡ የሽልማት ድርጅቱ ኃላፊዎች ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በሰጡት መግለጫ ድርጅቱ ቋሚ ፅ/ቤት ከከተማ አስተዳደሩ ማግኘቱንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ለሽልማቱ የሚታጩት ግለሰቦች በ10 ዘርፍ የሚቀርቡ ሲሆን ዘርፎቹም በመምህርነት፣ በሳይንስ (በህክምና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፊዚክስ ምህንድስና ኬሚስትሪ አርክቴክቸር ወዘተ) በኪነ ጥበብ (ሥነ - ጥበብ፣ ወግ፣ ድርሰት) በጐ አድራጐት (እርዳታና ሰብአዊ አገልግሎት)፣ በቢዝነስና ሥራ ፈጠራ፣ በመንግስታዊ የስራ ተቋማት ሃላፊነት፣ ቅርስና ባህል፣ ማህበራዊ ጥናት፣ ሚዲያና ጋዜጠኝነት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ዲያስፖራዎች ናቸው፡፡ ከባለፈው አመት ማለትም ከ7ኛው ሽልማት ጀምሮ የተካተተው “ለአገራችን ዕድገት አርአያነት ያለው አስተዋጽኦ ያረከቱ ዲያስፖራዎች” ዘርፍን ጨምሮ የሽልማት ድርጅቱ እስካሁን ስራ ላይ ባዋላቸው ዘርፎች በሙሉ ጥቆማ እንደሚቀበል የገለፁት ኃላፊዎቹ፣ በተለይ በ “ማህበራዊ ጥናት” ዘርፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት በቂ እጩዎች ባመጠቆማቸው ሽልማቱ ያልተካሄደ ሲሆን፤ በዚህ የሙያ ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ ያላቸውን ለማክበርና አርአያነታቸውን ለማጉላት ህዝቡ በተለይም ለሙያው ቅርበት ያላቸው ሁሉ የዘርፉን ሰዎች እንዲጠቁሙ የሽልማት ድርጅቱ በአጽንኦት ጥሪ አቅርቧል፡፡ ጠቋሚዎች ዕጩ በሚያቀርቡበት ጊዜ የሰሩትን ስራ በዝርዝር እንዲገልፁና አድራሻቸውንም አብረው እንዲልኩ አሳስቧል፡፡ የዕጩ ጥቆማውም እስከ የካቲት 30 ቀን 2012 ዓ.ም ለአንድ ወር ይቆያልም ተብሏል፡፡
በተያያዘ ዜና የበጐ ሰው ሽልማት ድርጅት ባገኘው ህጋዊ የስራ ፈቃድ መነሻነት ተቋማዊ መሰረት ኖሮት ለማደራጀት ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ይረዳው ዘንድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፒያሳ በሚገኘው አራዳ ፖስታ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኝ ታሪካዊ ቤት አድሶ እንዲገለገልበት የተበረከተለት ሲሆን ለዚህ ትልቅ ድጋፍ የከተማ አስተዳደሩንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮን የሽልማት ድርጅት ሃላፊዎች አመሰግነዋል፡፡


Read 221 times