Sunday, 09 February 2020 00:00

ትራምፕ ከስልጣን እንዲነሱ ከቀረቡባቸው ክሶች ነጻ ሆኑ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀምና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ ከስልጣን እንዲነሱ ከቀረቡባቸው ሁለት ክሶች በሴኔቱ ውሳኔ ነጻ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ሪፐብሊካኑ አብላጫ ወንበር የያዙበት ሴኔት ባለፈው ረቡዕ በትራምፕ ላይ በተመሰረቱት ሁለት ክሶች ላይ ድምጽ የሰጠ ሲሆን፣ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም የቀረበባቸውን ክስ 52 ለ48፤  የአገሪቱን የምክር ቤት ስራ አደናቅፈዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ደግሞ 53 ለ47 - ሁለቱንም ክሶች በአብላጫ ድምጽ ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡
ምንም አይነት ጥፋት አልፈጸምኩም በማለት ሲከራከሩ የቆዩት ዶናልድ ትራምፕ፤ በአገሪቱ ታሪክ ሴኔት ፊት ቀርበው ክሳቸውን እንዲከላከሉ የተወሰነባቸው ሶስተኛው ፕሬዚዳንት ቢሆኑም፣ ሴኔቱ በሰጠው ድምጽ ስልጣናቸውን ከመልቀቅ እንደታደጋቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ትራምፕ የዩክሬን አቻቸው ቭላድሚር ዘለንስኪን በቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምርጫ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን እና በልጃቸው ላይ የሙስና ምርመራ እንዲያደርጉ በመደለልና ጫና በማድረግ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም፤ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሚደረግባቸው ምርመራ መረጃዎችን ባለመስጠትና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱ በቀረበባቸው የውሳኔ ሃሳብ ዙሪያ የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ወር በፊት ለአስር ሰዓታት ያህል ክርክር ካደረገ በኋላ እንዲከሰሱና ሴኔት ፊት ቀርበው የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው ረቡዕ ሴኔቱ በሰጠው ድምጽ ከሁለቱም ክሶች ነጻ ሊወጡ መቻላቸውንም አመልክቷል፡፡
የቀረበባቸውን ክስ የአክራሪ ግራ ዘመሞች ነጭ ቅጥፈትና በሪፐብሊካን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሲሉ በአደባባይ ያጣጣሉት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከስልጣን እንዲለቁ በዲሞክራቶች የተጎነጎነባቸውን ሴራ በመበጣጠስና ራሳቸውን ነጻ በማውጣት ያስመዘገቡትን ድል ለሁለተኛ ዙር የስልጣን ዘመን በሚወዳደሩበት ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመድገም መዘጋጀታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ በኮንግረስ ውሳኔ ሴኔት ፊት ቀርበው ክስ እንዲመሰረትባቸው የተወሰነባቸው ሁለት የአገሪቱ መሪዎች አንድሪው ጆንሰንና ቢል ክሊንተን እንደነበሩ ያስታወሰው ዘገባው፣ ያም ሆኖ ግን ሁለቱም ከስልጣን እንዲለቅቁ እንዳልተወሰነባቸውም አክሎ ገልጧል፡፡


Read 2970 times