Tuesday, 11 February 2020 00:00

ፈረንሳይ በቱሪስቶች ብዛት ከአለም ቀዳሚ ሆናለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ በርካታ መንገደኞችን በማስተናገድ ቀዳሚ ሆኗል

             ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 የተለያዩ የአለማችን አገራትን የጎበኙ አለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር በ4 በመቶ በማደግ፣ 1.5 ቢሊዮን መድረሱንና በአመቱ ከ90 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች የጎበኙዋት ፈረንሳይ፤ በበርካታ ቱሪስቶች የተጎበኘች ቀዳሚዋ የአለማችን አገር መሆኗ ተነገረ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የቱሪዝም ድርጅት ያወጣውን አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ፎርብስ መጽሄት እንደዘገበው፤ በአመቱ በ83.8 ሚሊዮን ቱሪስቶች የተጎበኘችው ስፔን የሁለተኛነት ደረጃን ይዛለች፡፡ በቱሪስቶች እድገት ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን የያዘችው ማይንማር ስትሆን አገሪቱን የጎበኙ የቱሪስቶች ቁጥር በአመቱ የ40.2 በመቶ እድገት ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ የ31.2 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበችዋ ፖርቶ ሪኮ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ላለፉት አምስት ተከታታይ አመታት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው አለማቀፍ መንገደኞችን በማስተናገድ በአለማችን ቀዳሚው አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ሆኖ የዘለቀው የዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ዘንድሮም ክብሩን አስጠብቆ መዝለቁን የዘገበው ገልፍ ኒውስ፤ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ 86.4 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገዱን አመልክቷል፡፡ የእንግሊዙ ሄትሮው አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ 80.4 ሚሊዮን መንገደኞችን በማስተናገድ፣ የአለማችን ሁለተኛው አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ መሆኑንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡


Read 8445 times