Saturday, 15 February 2020 11:01

ከዚህ በኋላ በሞጣ በተቃጠሉ መስጂዶች ስም የሚጠየቅ እርዳታ የለም ተባለ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  - እስካሁን ከ209 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል
      - የተጠቀሰው ገንዘብ በውጪ አገር የተሰበሰበውንና በአይነት የተገኘውን ድጋፍ አይጨምርም ተብሏል
                 
        በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ ከተማ ታህሳስ 10 ቀን በተፈፀመው ጥቃት የተቃጠሉ መስጂዶችንና ንብረታቸው የተቃጠለባቸውን ወገኖች ለመደገፍ በተሰበሰበው የድጋፍ ገንዘብ ከ209 ሚ.ብር በላይ መገኘቱን የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡ ምክር ቤቱ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ገንዘቡ በውጭ አገር የተሰበሰበውንና በአይነት የተገኘውን ገንዘብ እንደማይጨምር ገልጿል፡፡
ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በሞጣ ከተማ በተፈፀመው የሽብር ጥቃት በከተማዋ የሚገኙ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶች፣ ቁርዓንና ሀይማኖታዊ መጽሐፍን የያዙ አራት መስጂዶች፣ የመስጂድ ኢማሞች መኖሪያ ቤቶችና ሙስሊሞች በአክሲዮን የገነቧቸው የተለያዩ የገበያ ማዕከላት፣ ሆቴሎች ሱቆች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ በውስጣቸው የነበሩ ንብረቶች፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ጥሬ ገንዘብና ሌሎችም ንብረቶች ሙሉ መቃጠላቸውንና መዘረፋቸውን ያስታወሰው ምክር ቤቱ፣ ይህ ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ የዚህ ጥቃት ሰለባዎች ለአስከፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች በመጋለጣቸው ድጋፍ ማሰባሰብ የግድ በመሆኑ በሚገኘውም ድጋፍ መስጂዶችን መልሶ ለመገንባት ተጎጂዎችን ለማቋቋም የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ አዋቅሮ በአፋጣኝ ወደ ሥራ መግባቱንም የምክር ቤቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል::
በመሆኑም አርብ ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም በአገር ውስጥና በተለያዩ የአለም አገራት በይፋ የተጀመረው የገቢ ማሰባሰብ ንቅናቄ 2ሚ. ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን ገልጸው ጋዜጣዊ መግለጫው እስከተሰጠበት እስከ ሐሙስ ረፋድ ድረስ 208.939 ሺህ 962 ብር 90 ሳንቲም በጥሬ ገንዘብ መገኘቱ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ ይህም ከእቅዱ በላይ መሆኑንና በዓይነት የተሰበሰበውን ገንዘብ የማይጨምር ሲሆን፣ ከ750ሺ ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ ከወርቅ፣ ከብር፣ ተሰሩ ጌጣጌጦች፣ የእጅ ሰዓትና የሞባይል ቀፎዎች ገቢ መደረጋቸውም ታውቋል፡፡
በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ከሕጻን እስከ አዋቂ የተሳተፉበት የድጋፍ ገቢ ማሰባሰቢያ እጅግ ሰላማዊና የኢትዮጵያን አንድነት አጉልቶ የሚያሳይ የሀይማኖትና የብሄር ልዩነት ያልተደረገበት ከመሆኑም በላይ ስጦታዎቹ የተገኙት በልመና ከሚተዳደሩ፣ እንደ ልብ መንቀሳቀስ ከማይችል ወንድም እንደ እግር የሚገለገልበትን ክራንች በማበርከት በጨረታ መሸጡን፣ ሙሽራዋ የቃል ኪዳን ምልክት የነበረውን የጋብቻ ቀለበቷን፣ ከ40 ዓመት በላይ የተቀመጠውን የቤተሰብ ቅርስ ሙዳይ ከነጌጣጌጡ መለገሱንና በርካታ ታሪካዊ የሆኑ ስጦታዎች ገቢ መሆናቸው ልባቸውን እንደነካው የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ እድሪስ ገልጸው ሁሉንም አመስግነው መርቀዋል፡፡
ይህ የገቢ ማሰባሰብ ሥራ በአጭር ጊዜ ከእቅድ በላይ እንዲሳካ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉትን ሁሉ አመሰግነው በተሰበሰበው ገቢ ተጎጂዎችን በአፋጣኝ ለማቋቋምና መስጂዶችን ለመገንባት ሁኔታዎችን የሚያመቻች ኮሚቴ አዋቅሮ በፍጥነት ወደ ሥራ እንደሚገባ የተናገሩት ሀላፊዎቹ በተጨማሪም በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በተከፈተው የዶላር አካውንት ቁጥር (1137526/2/3410/0 በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ኦዳ ቅርንጫፍ በcode ORIRETEA) እስከ የካቲት 24 ቀን 2012 ዓ.ም የሰበሰቡትንና ገንዘብ ገቢ እንዲያደርጉ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡    


Read 906 times