Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 30 June 2012 12:06

“ቀጣይ ዕጣ ፋንታችን መታገል ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በዓመቱ መግቢያ ላይ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በመያዝ ክስ በተመሰረተባቸው በእነ አንዷለም አራጌ ላይ ሰሙኑን ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ የ”አንድነት” አመራሮች ከትናንት በስቲያ በፅ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች የሰጡትን መግለጫና ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን መልሶች እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ስለ ፍ/ቤት ውሳኔ  (አቶ ግርማ ሠይፉ)

ትላንት (ረቡዕ ማለት ነው) የተሠጠው የፍርድ ውሳኔ በሀገራችን ያለው የፍርድ ሒደት ገለልተኛ አለመሆኑን አስመስክሯል፡፡ ፍ/ቤቱ፤ አቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃ እንዲያቀርብ በቂ ጊዜ ከሠጠው በኋላ ተከሳሾች ግን ሀሳባቸውን የመግለፅና ለህዝብ የመደመጥ መብታቸውን ተነፍገዋል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ ዛሬ (ሃሙስ ማለት ነው) ተከሳሾቹ መብታቸውን በመጠየቃቸው ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና ቀድመው ከነበሩበት ቦታ ተነስተው ወደ ጨለማ ቤት የመሔድ እጣ እንደደረሳቸው ሰምተናል፡፡

ሐምሌ 6 የሚሠጠው የቅጣት ውሳኔ ምንም ይሁን ምን ለፓርቲያችን ትርጉም የለውም፡፡ ዋናው ትርጉም የነበረው ጉዳይ እነዚህ ሠዎች ጥፋተኞች ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን መወሠን ነበር፡፡ እነዚህ ንፁህ ሠላማዊ ታጋዮች ጥፋተኛ ናቸው የሚል እምነት አልነበረንም፤ የለንም፡፡ ተከሳሾቹ ወደ ፍርድ ቤት በሚሔዱበት ጊዜ ላለመከራከር ወስነው ነበር፡፡ ፓርቲያችን ለህግ ካለው ክብርና አመኔታ አንፃር የፍርድ ሒደቱን መሞገት ስለነበረብን፣ በማግባባት ወደ ክርክሩ እንዲገቡ ግፊት አድርገናል፤ ያደረግነውም ነገር ተሳክቶልናል፡፡ ብትከራከሩ ኖሮ እኮ የተሻለ ውጤት ታገኙ ነበር የሚል ሃሳብ ላላቸው ሰዎች ተከራክረን ለማሳየት ተጠቅመንበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ከፍርድ ሂደት በፊት ተከሳሾቹን በአደባባይ ወንጀለኞች ብለዋቸው ነበር፡፡ ፍ/ቤትም እሳቸው ያሉትን ነው  በፅሁፍ ያረጋገጠው፡፡ ይሔ ደግሞ አስፈፃሚውን አካል ሊቆጣጠር የሚችል የፍርድ ስርአት እንደሌለን በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንጀለኞች ያሏቸውን ተከሳሾች፤ ነፃ ናቸው የሚል ፍ/ቤት ቤት ብናገኝ ኖሮ ጮቤ በረገጥን ነበር፡፡ ይሔ ግን ሳይሆንልን ቀርቷል፡፡ በዚህ ፍርድ ሒደት ውስጥ የሚያሳዝነው ነገር፣ አንድ ቀን እንኳ አብረው ሻይ ጠጥተው የማያውቁ፣ የማይተዋወቁ ሠዎች በጋራ፤ አንድ ላይ በማበርና በመስማማት በሚል ጥፋተኞች ተብለው እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣት የሚወሰንባቸው መሆኑ ነው፡፡

ይሔንን ዝርዝር የህጉን ሒደት በመጨረሻ ላይ ታሪክም የሚመዘግበው ሲሆን “አንድነት” በቂ ትኩረት ሰጥቶ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ጉዳዩን በቅጡ እንዲረዳው ያደርጋል፡፡ ሌላው የተረዳነው ነገር ፍ/ቤቱም ያረጋገጠልን፣ ክሱ ከአሸባሪነት ጋር የተያያዘ እንዳልነበረ ነው፡፡

ይልቁኑም የአረብ አገራትና የሰሜን አፍሪካ የህዝብ ንቅናቄዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመጡ ለመከላከል የተመሰረተ ክስ ነው፡፡ ትንተናውም የሚያሳየን ይሔንን ነው፤ ስለዚህ እዚህ አገር ውስጥ ስለ አረብ አገሮች ህዝባዊ እንቅስቃሴ መወያየትና መነጋገር ወንጀል መሆኑን አረጋግጠንበታል፡፡

መንግስት አሁን በወሠደው ህጋዊ በሚመስል ህገ መንግስቱን የሚንድ እርምጃ፣ “አንድነት” እንደተቋም፣ ደጋፊዎች ደግሞ በግል ፈርተው ከትግሉ ይሸሻሉ የሚለው ግምት የተሳሳተ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ገዢው ፓርቲና መንግስት ማወቅ ያለበት ትግሉ የሚቆመው በአዋጅ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተከለከለ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ማንኛውም አፈናና ክልከላ አንድነትን እንደ ፓርቲ፣ አባላቶችን በግል ሊያፍናቸውና ሊያስቆማቸው እንደማይችል ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡ መንግስት በወሠደው ኢ-ህገመንግስታዊ እርምጃ ተጠቃሚዎቹ በሠላማዊ መንገድ ላለመንቀሳቀስ የሚወስኑት መገንዘብ አለበት፡፡ እናም በሠላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ ለወሰነው አንድነትና ሌሎች ፓርቲዎች መድረኩን ማስፋትና የወሠዳቸውን  እርምጃዎች ማረም ይኖርበታል፡፡ ሃዘናችን ትክክለኛውን የፍርድ ሒደት በማጣታችን እንጂ የታሠሩት ሠዎች ከዚህም የከፋ ነገር ሊገጥማቸው እንደሚችል እነሱም እኛም እናውቅ ነበር፡፡ ፈተናውን የወደቀው ግን ገዢው ፓርቲ፣ መንግስትና የፍትህ ስርአቱ መሆኑን ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡ “አንድነት” ከምንም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ ስራውን ይቀጥላል፡፡

ታሳሪዎች ወደ ጨለማ ክፍል መዛወራቸው

ዝርዝር ሁኔታውን የታሳሪዎቹ ቤተሠቦች እዚህ ስላሉ እነሱን ማነጋገር ትችላላችሁ፡፡

አንዷለም አያሌው ከፍርድ ቤት ሲወጣ ኩላሊቱ ላይ ተረግጦ ከፍተኛ ህመም እየተሠማው እንደሆነ፤ ለናትናኤልና እስክንድር ምግብ ማስገባትና መጠየቅም እንዳልተቻለና ከነበሩበት ክፍል ወጥተው ወደ ጨለማ ክፍል መዘዋወራቸውን፤ ሊጠይቋቸው ሔደው የነበሩ ሠዎች አረጋግጠውልናል፡፡ አንዷለምን በተመለከተ ቤተሠቦቹ ዛሬ ወህኒ ቤት ስላልሔዱ ያለበትን ሁኔታ ማረጋገጥ አልተቻለም፤ የተለየ እጣ ይኖረዋል ብለን ግን አናምንም፡፡

በአንድነት አባላት ላይ ወደፊትም እስሩ ይቀጥላል ወይ የሚለውን በተመለከተ ይሄን መጠየቅ ያለበት የኢህአዴግ ደህንነት ነው፡፡ እነማንን ያስር እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

ከዚህ በፊትም እነ አንዷለም እንደሚታሰሩ ወሬዎች ይናፈሱ ነበር፡፡ ከዛም ታሠሩ፡፡ ጋዜጠኞች ናቸው ይሔንን ማጣራት ያለባቸው፡፡ ከአንድነትም ሆነ ከሌሎች የግል ጋዜጦች የተለያዩ ሠዎች ሊታሠሩ እንደሚችሉ አንዳንድ መረጃዎች  አሉ፡፡ የኢትዮጵያ የደህንነት ስራ ይሔንን ነው የሚመስለው ወይ በሚያስብል ሁኔታ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያስደነግጣሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ የባለፈው ሳምንት የ”ፍትህ” ጋዜጣን ማንበብ ከበቂ በላይ ነው፡፡

 

ተከሳሾቹ እንዲከራከሩ ግፊት ስለመደረጉ

እነዚህ ሠዎች በዚህ ስርአት ውስጥ እንዲያልፉ በማግባባታችንና እነሱም በማመናቸው የፍትህ ስርአቱ ያስቀመጥንለትን ፈተና ማለፍ አለመቻሉን አይተንበታል፡፡ ስለዚህ ይሔንን ፈተና የወደቀው ነው ልክ ያልሆነው፡፡ እኛ ፈተና አውጥተን ወድቋል፡፡

እንዲከራከሩ ማድረጋችን “ብትከራከሩ እኮ ጥሩ ነበር” ለሚሉ ሰዎች አፍ መዝጊያ ነው፡፡

አሁን ወደ ሌላ ደረጃ እንሸጋገራለን፡፡ ደረጃ በደረጃ ሁሉም ነው የሚፈተነው፤ ፈተናውን የመውደቅ ያለመውደቅ ሀላፊነት የሚፈተኑ ሠዎች ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ እኛ ለህዝብ ነው የምንሠራው የሚለው ነገር አንድ ጥግ ይዟል፡፡ እኛ እዚህ ውስጥ የተሠባሰብን ሠዎች ነፃነት ጠቃሚ መሆኑን አውቀን፣ እያንዳንዱ ሠው እያንዳንዱ የህብረተሠብ ክፍል ለነፃነቱ እንዲታገል የማድረግ ሀላፊነት አለብን፡፡

ሞዴል የመሆን ሀላፊነት ስላለብን፤ ሞዴል ለመሆን እንሠራለን፡፡ ይህንን ለማድረግ እኛ የምንችለውን እየሰራን ነው ያለነው፡፡ “አንድነት” ጋዜጣ አለው፤ ህዝባዊ ስብሠባዎችን በምንችለው አቅም እያከናወንን ነው፡፡ የተከለከልነው ህዝቡ ጋ የምንደርስበት መንገድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ይሔ ሀላፊነት የጋዜጠኞችም ጭምር ነው፤ አዲስ ዘመንን ጨምሮ፡፡

 

አቶ አስራት ጣሴ እንዲከላከሉ ስለመደረጉ

በአንድ ወቅት ትክክል የሆነ ነገር በሌላ ወቅት ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡ ምናልባት ይሔ ጥያቄ ከ1997 የቅንጅት እስረኞች ጋር  አያይዘነው ከሆነ ጊዜው የተለያየ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንዲከራከሩ መደረጉ ግን በጣም ተገቢና ትክክል ነው፡፡ እየኖርን የምናውቀውንና ብዙ ጥናቶቹም በማስረጃ  ያሳዩትን አንድ ተጨማሪ እውነታ ነው ያሳየነው፡፡ አንድ ጥናት በቅርቡ አይቻለሁ፡፡

ጥናቱ የተካሔደው ኪሊማንጃሮ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን ሊሚትድ በተባለ የታንዛኒያ ተቋም ሲሆን በገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የአለም ባንክ ነው፡፡

ጥናቱ እንዲጠናለት ያደረገው የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲሆን በ6ሺህ ሠዎችና በ27 መ/ቤቶች ላይ ነው ጥናቱ የተካሔደው፡፡ የጥናቱ ውጤት ምንድነው የሚያሳየው… በከፍተኛ ደረጃ የህብረተሠቡን አመኔታ ያጡ ተቋማት ከተባሉት ውስጥ የመጀመርያው ተቋም ፍርድ ቤት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ፖሊስ፡፡ የትላንትናው ውሳኔ ምን ያህል ፍርድ ቤት ላይ አመኔታ እንደሌለ ያሳያል፡፡ ህዝቡ ተረድቷችኋል ወይ?

እኛ እርስ በእርስም እንጠያየቃለን፡፡ እኛን አይደለም ህዝብ መረዳት ያለበት፤ ከኑሮው እኮ ነው መረዳት ያለበት፡፡ የሚታየው ድህነትና መማቀቅ ነው፣ የኑሮ ውድነቱ ምን ያህል ንሯል? ህዝቡ ያውቀዋል፡፡ እናንተ ስለፃፋችሁት እኛ ስለተናገርን አይደለም ህዝቡ ነገሩን የሚረዳው፡፡

የእኛ ጩኸት የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት፣ ፍትህ ይፈልጋል፤ የሚል ነው፡፡ ይሄ ጥያቄ የለውም፡፡ ህዝብ ይሔንን ስርአት ማስወገድ አለበት፤ በሠላማዊ ህዝባዊ ትግል፡፡ ሌላ አማራጭ የለም፤ ደግሞም ይደረጋል፤ መቼ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ለነቢያትም ያስቸግራቸዋል፡፡

 

ተከሳሾቹ ከፍ/ቤት በፊት ወንጀለኞች መባላቸው

በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምር ማስረጃ አለን ብለው ተከሳሾቹን ፍ/ቤት አቅርበዋቸዋል - ከደህንነት በደረሳቸው መረጃ መሠረት፡፡ ከምር ማስረጃ ያላቸው ሊመስል ይችላል፡፡

በመጀመሪያ ሠዎቹን ወንጀለኞች ናቸው ብሎ በይፋ መናገር ስህተት ነበር፤  እዚህ ጋ ነበር ጉዳዩ መቆም የነበረበት፡፡

ተከሳሾቹ በታሠሩ ጊዜ የሠጠነው መግለጫ አለ፡፡ መንግስት በጉዳዩ ላይ መረጃ ካለው ቢሠጠን እኛም ልንተባበራቸው እንደምንችል ምክር ቤትም አንስቼዋለሁ፤ ግን ከምር ማስረጃ እንዳልነበረ መረጃም እንደሌለ ነው ያየነው፡፡

ከቅጣት ውሳኔ በኋላስ?

እነዚህን ነገሮች የሚወስኑት ተከሳሾቹ ራሳቸው ናቸው፤ ይግባኝ እንጠይቃለን ይቅርታ እንጠይቃለን ወይም ደግሞ ሌላ አማራጭ ካለ የእነሱ ውሳኔ ነው፤ በእኛ በኩል  አማራጮቹን ከሚመለከታቸው የህግ ባለሙያዎች ጋር ተነጋግረን የምንወስነው ነው የሚሆነው፡፡

 

ከአረቡ አመፅ አገር ጋር ምን አገናኘው?

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እዚህ ቦታ እንዲህ አድርገው የሚል አላቀረበም ወይም ፈንጂ በሚቀመምበት ቦታ እንዲህ አድርገው አላለም፤ በአረብ አገር ስለተፈፀመው የህዝብ አመፅ ነው የተነገረው፡፡ ነገሩ እኛም አገር ሊሆን ይችላል፡፡ በድጋሚ የሚያሳስር ከሆነ እኔ ዛሬ ለመታሠር ዝግጁ ነኝ፡፡ አረብ አገር ያሉት ሁኔታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከአስር እጥፍ በላይ አሉ፡፡

እነዚህ ሠዎች ምን መደምደሚያ ላይ ነው የደረሡት የሚለውን ነገር ማየት አልተቻለም፡፡ የደረሱበት መደምደሚያ ምንድነው? “ኢትዮጵያ 50 አመት ባልሞላ ጊዜ ሦስት ጊዜ ውስጥ አብዮት ማካሔድ የለባትም ይበቃናል፡፡ አንድም ሠው መሞት የለበትም፤ እረብሻ ብጥብጥ ይቅርብን” ብለው ውሳኔ ያደረጉ ሠዎችን ነው ፤ ቢሆንም አስባችኋል ተብሎ ትንተና የተሠጠባቸው፡፡ የአረብ አገራትን በተመለከተ አንድነት ውይይት አድርጐ በአቋም የተነጋገረበት ነው፡፡ አላማው ሠላማዊ ትግል እንዴት ይካሔዳል ነው? ብጥብጥና ፀብ እዚህች አገር ላይ እንዴት ይቁም የሚል ነበር፡፡

አንቀፅ 29 ማንኛውም ሠው ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመሠለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል ይላል፡፡ ትላንትና ፍ/ቤት እንደ ጭብጥ ተይዞ ውሳኔ የተሠጠበት፤ አለማቀድ አለማዘጋጀት አለማሴር አለመሞከር የሚሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ህገ መንግስቱ የሚለው ምንድነው… የአመለካከትና ሀሳብን በነፃ የመያዝና በነፃ የመግለፅ መብትን ይደነግጋል፡፡ ሌላው ቢቀር ጭንቅላት ውስጥ ሁሉ አሸባሪ መሆን የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በህገ መንግስቱ መሠረት በተግባር አለማድረግ ነው የሚለው፡፡

ከዚህ ጋር የሚፃረር አነስ ያለ ነገር እንኳን ህግ ሆኖ ቢወጣ ተቀባይነት የለውም፡፡

አሁን ከዚህ ያለፈ መመሪያና ደንብ እየወጣ ትልቁ ህገመንግስት እየተሻረና እየተሸራረፈ ነው፡፡

አንቀፅ 30 ፤ የመሠብሠብ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብትን ነው የሚገልጸው፡፡

ሠላማዊ ሠልፍ እናደርጋለን፤ ህዝባዊ ስብሠባ እናደርጋለን ብለው የጠየቁን ሠዎች መደገፍ ወንጀል ነው? አንድነት ስብሠባ ላይ የመኢዴፓ አባል ከተገኘ ወንጀል ይሆናል፤ ሌላ የፓርቲ አባል ያልሆነ ሠው አንድነት ፓርቲ ላይ ምን አግብቶት ተገኘ ተብሎ ነው ትንተና የተሠጠበት፡፡

ስለዚህ ህገመንግስቱ፤ የመሠብሠብ እና ሠላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት ብሎ የደነገጋቸው ናቸው የተጣሱት፡፡ አንቀፅ 31 ላይ ስለ መደራጀት መብት ነው የሰፈረው፡፡ የተደራጀነው እኮ ፅዋ ልንጠጣ አይደለም፡፡

መንግስት ልንቀይር ነው የተደራጀነው፡፡ ፅዋ ጠጥተን ፅዋ ልናዞር አይደለም፤  ይሔንን መንግስት ልንቀይር ነው፡፡ ስለዚህ መደራጀት ትክክል አይደለም፤ ሊባል አይቻልም፡፡ የሚያስቅ ነገር ልንገራችሁ፡፡ ለምሳሌ አንድ አክሲዮን ለማቋቋም መጀመሪያ ስለ አክሲዮኑ መደራጀት መሠብሠብ አለብን፤ ማህበሩን ስናቋቁም እንዴት እንደምናቋቁመው መሠብሠብ አለብን፤ ይሔ ትክክል አይደለም ተባለ፡፡ ፍርድ ቤቱን በፈተና ጥለነዋል፡፡ ከባድ ፈተና ነው ያወጣንበት፡፡ ወድቋል፡፡ ምንም ልንረዳው አንችልም፡፡

 

የዶ/ር ነጋሶ ህመምና የህክምና ወጪ

ዶ/ር ነጋሶ አሁን ህክምና ጀምረዋል፡፡ ህክምናቸው የመጨረሻው ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል አናውቅም፡፡

የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ የደረሰባቸው የእግር ህመም በፓርላማ መነሳት ነበረበት፤ ግን በፓርላማ ምንም ነገር ለማንሳት አጀንዳ መያዝ አለበት፡፡ አጀንዳ ለማስያዝ ደግሞ አንድ ሠው አይችልም፡፡ ባልተያዘ አጀንዳ ላይ ደግሞ መነጋገር አይቻልም፡፡

ምናልባት ኢቴቪ የሚያስተላልፈው ከሆነ በዚያ እንሞክራለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይሄ ለኢትዮጵያ እንደ አገር ውርደት ነው፡፡ ፕሬዚዳንቷን ማሳከም አልቻለችም፤ አንድና ሁለት መቶ ሺህ ብር ከፍላ ማሳከም አቅቷት አካላቸውን አጡ ቢባል ውርደት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት መልስ ባይሰጥበት የኢትዮጵያ ህዝብ መልስ ይሠጠዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 

ዶ/ር ሀይሉ አርአያ

ትላንትና ችሎት ቆም ብዬ ሳዳምጥ የገረመኝ አንድ ነገር አለ፡፡ የመሀል ዳኛው የፍርድ ትንታኔ ሲሠጡ፤ በሰሜን አፍሪካና በአረቡ አገር የተካሔደው እንቅስቃሴ በሠው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሠ፣ ደም ያፋሠሠ እንቅስቃሴ እንደነበር ነው ሲያነቡ የነበረው፡፡

እኔ እንደገባኝ የዚህ አይነት ክርክር ሊቀርብ የሚችለው በአቃቤ ህጉ ነበር፡፡ አቃቤ ህጉ የሠዎችን ወንጀል ሲተረትር ወንጀል ከሆነ ከአረቡ አገር የተያያዘውን እንቅስቃሴ አንስቶ “ያንን መደገፍ ወንጀል ነው፤ ምክንያቱም ጉዳት ያደረሠ ነው በሠው ህይወትና ንብረት ላይ” ብሎ ክርክር ያቀርባል እንጂ ዳኛ ትንተና አይሠጥም፡፡ ይሔ  ችሎት የአቃቤ ህግ ነው ወይስ የዳኝነት ቦታ ነው ብዬ ግራ ገብቶኝ ነበር፡፡

አቶ ዳንኤል

የፍርድ ቤቶች ገለልተኛነት እና የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ላይ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡

ከዛ በፊት ግን አንድ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ ሠላማዊ ትግሉንና ፕሬሱን ለማፈን መጀመሪያ ህግ ነው የሚያዋጣው፡፡ ከእሱ በፊት ግን የንድፈ ሀሳብ መፅሔት አለች፤ እዛ የንድፈ ሀሳብ መፅሔት ላይ ቁጭ ይደረጋል፡፡ ከዛ ከንድፈ ሀሳብ መፅሔት ላይ ህዳሴ ትባላለች፡፡ አዲስ ዘመንና አይጋ ፎረም የመንግስት ሚዲያ ሆነው ህዝብን ማገልገል ሲገባቸው፤  ፓርቲ ወደ ማገልገል ደረጃ ወርደው የመንግስት ተቋማት ይሁኑ የፓርቲ በማይለይበት ሁኔታ ከመስመር ይወጣሉ፡፡ ይሔ ቅብብል ከተደረገ በኋላ ጠ/ሚኒስትሩ ይናገራሉ፤ ጠ/ሚ የተናገሩት ደግሞ ይፈፀማል ማለት ነው፡፡

አንድ ምሳሌ ልናገር፡፡ ባለፈው ጠ/ሚኒስትሩ መምህራን ወላጆቻቸውና ተማሪዎች የማስተማር ችሎታ የሌላቸውን እንድናባርርላቸው እየጠየቁን ነበር፡፡ የእኛ ስህተት እሱን አለማድረጋችን ነው ብለዋል፡፡ ልብ አድርጉ እኔ የማባረሪያ ስትራቴጂ ነው  ብዬ የማምነው፡፡ ጠ/ሚ ይሔን በተናገሩ በአንድ ወር ውስጥ በጣም በርካታ መምህራን የማስተማር አቅም የላችሁም እየተባሉ እየተባረሩ እዚህ መጥተው ሪፖርት ያደረጉ አሉ፡፡ ሌላው ትላንት ለምሳሌ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ናችሁ ከተባሉ በኋላ አቃቤ ህጉ የቅጣት ማክበጃ አቀረበ፡፡

ከዛ በኋላ እዛው ፍርድ ቤት እነእስክንድር ለምንድነው የቅጣት ማቅለያ እንዳያቀርቡ የተከለከሉት? “እኛ እራሳችን ሀሳባችንን እንገልፃለን” ሲሉ እኮ ይሔ መብታቸው ሊከበርላቸው አልቻለም፡፡ ምንድነው የተደረገው… የጥበቃ ሠራተኛ ተጠርቶ ማይኩን ተነጥቀው ህዝቡ ቀነ ቀጠሮ መቼ እንደሆነ ሳያውቅ ነው ተነስተው የሔዱት፡፡

እንደዚህ አይነት ሚዛናዊ እና ገለልተኛ ያልሆነ ነገር እያየን እንዴት እንመን? እኛ ቀጣይ እጣ ፈንታችን መታገል ነው፤ ስርአቱ እስከሚቀየር ድረስ ዲሞክራሲያዊ የሆነች፣ የሁሉም ኢትዮጵያ እስከምትፈጠር ድረስ ቢያስሩንም ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ ቢገሉንም እርግጠኛ ነን አንድ ቀን ለውጥ ይመጣል፤ በቅርቡ ይሆናል፡፡ የህዝቡ ዝምታም ኩርፊያ እንጂ እኛን መረዳት አይደለም፡፡ ኢህአዴግም ያስጨነቀው ዝምታው ነው፤ ለዚህም የሆነ ነገር ማድረግ ይፈልጋል፡፡ የህዝቡ ዝምታ፤ መልስ ነው የሚያስፈልገው፡፡

 

 

Read 17302 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 12:16