Saturday, 15 February 2020 11:01

አገራዊ ምርጫው ነሐሴ 23 ይካሄዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 - ቦርዱ ቅስቀሳ የጀመሩ ፓርቲዎችን አስጠነቀቀ
      - የምረጡኝ ዘመቻ ከግንቦት 21 እስከ ነሐሴ 18 ይሆናል

             የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ነሐሴ 23 ቀን 2012 እንዲካሄድ የወሰነ ሲሆን ለምርጫ ቅስቀሳ ከተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ቀድመው ቅስቀሳ የሚያደርጉ ፓርቲዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ቦርዱ አስጠንቅቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከህግ አግባብ ውጪ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ፓርቲዎች እንዳሉ የጠቆመው  እነዚህን ፓርቲዎች ከዚህ በኋላ እንደማይታገስና እንቅስቃሴያቸውን በህግ እንደሚቆጣጠር አሳስቧል፡፡
እስካሁን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ ፓርቲዎችን በዝምታ ያለፈው ቋሚ የጊዜ ሰሌዳ ባለመጽደቁ እንደነበርም የገለፀው ቦርዱ፤ ትናንት ይፋ ባደረገው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ቀደም ብሎ ነሐሴ 10 እንደሚካሄድ የተነገረው ምርጫው ወደ ነሐሴ 23 ያስተላለፈ ሲሆን ሌሎች ሽግሽጎችንም በጊዜ ሰሌዳው ላይ አድርጓል፡፡
በዚህ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ የመራጮች ምዝገባ ከሚያዝያ 14 እስከ ግንቦት 13 ቀን 2012፣ የእጩዎች ምዝገባ ጊዜ ከግንቦት 5 እስከ ግንቦት 19፣ የምረጡኝ ዘመቻ ጊዜ ከግንቦት 21 ቀን እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2012፣ የድምፅ መስጫ ቀን ነሐሴ 23 እንዲሁም የመጨረሻ የምርጫ ውጤት የሚገለጽበት ከነሐሴ 24 እስከ ጳጉሜ 3 ቀን 2012 ይሆናል፡፡
በተያያዘ ዜና ቦርዱ አዲሱን አርማውን አስተዋውቋል፡፡ አዲሱ አርማ ቦርዱ በአዲስ መልክ እያከናወነ ያለውን ተቋማዊ ግልጽነትና እና ተአማኒነት የሚያሳዩ እንዲሁም የተቋም ማንነት ለውጥን የሚወክሉ መገለጫዎችን በማካተት ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡  

Read 930 times