Saturday, 15 February 2020 11:19

ዶ/ር ደብረፅዮን ከኤርትራ መሪዎች ጋር መወያየት እንፈልጋለን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው የድንበር ችግር በዘላቂነት መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው መሪዎች ተገናኝተን፣ በህግና በስርአት ተቋማዊ በሆነ መልኩ መፍትሔ ስናበጅለት ነው ያሉ ሲሆን፤ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ በበኩላቸው፤ የድንበር ጉዳዩ መቋጫ እንዳያገኝ እንቅፋት የሆኑት የህወኃት መሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ህወኃት የትጥቅ ትግል የጀመረበትን 45ኛ አመት ምክንያት በማድረግ “መቐሌ ትግራይ” ከተሰኘ የድረ ገጽ ጋዜጣ ጋር ሰሞኑን ልዩ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ዶ/ር ደብረ ፂዮን በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የድንበር ችግር በተፈለገው ፍጥነት መፍትሔ ያላገኘው መሪዎች ተገናኝተን፣ ባለመወያየታችንና በህግና ስርአት ጉዳዩን ለመቋጨት ባለመቻላችን ነው ብለዋል፡፡
የድንበሩን ጉዳይ እልባት ለማበጀት የኛ የመሪዎች ተገናኝቶ መነጋገር አስፈላጊ ነው ያሉት ዶ/ር ደብረፂዮን ከፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ አመራር ጋር ውይይት የማድረግ ፍላጐት እንዳላቸውም ገልፀዋል፡፡
“በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረውን ሠላም ያደናቀፈው ህዝብ ሳይሆን መንግስታት ናቸው” ያሉት ም/ርዕሰ መስተዳድሩ፤ “ህዝብ ሁሌም ሠላም ፈላጊ ነው፤ ችግር ያለው መሪዎች ጋ ነው” ብለዋል፡፡
በጦርነት መፍትሄ የሚያገኝ ጉዳይ እንደሌለ የተናገሩት ዶ/ር ደብረፅዮን በሁለቱ ሀገራት የተጀመረው ሠላም ዘላቂ ሆኖ ዝምድናችን ወደ መደበኛነት እንዲሸጋገር በመጀመሪያ ያልተቋጩ የድንበር ጉዳዮች በህግና በስርአት፣ ተቋማዊ በሆነ መልኩ እንዲቋጩ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከሀገረ ኤርትራ መሪዎች ጋር የመገናኘት ፍላጐት እንዳላቸው የጠቆሙት ምክትል ር/መስተዳድሩ፤ አሁን ችግር የሆነው መገናኘቱ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ፤ ሰሞኑን ከሀገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በባድመና አካባቢው ጉዳዩ በሠላም እንዳይፈታ የህወኃት አመራሮችና ጥቂት የውጭ ሃይሎች እንቅፋት መሆናቸውን በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ ያለው የብሔር ፌደራሊዝምን ተገን በማድረግ ህወኃት ጉዳዩን እድሜ መግዣ እያደረገው ነው ብለዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት በባድመ ያለው ሁኔታ ከምንጊዜውም የባሰ አስቸጋሪ ሆኗል ያሉት ፕሬዚዳንቱ ነገሩን በትዕግስት እያየን ያለነው ችግር ፈጣሪዎቹ ጠባብ አዕምሮ ያላቸው ጐጠኞች መሆናቸውን ስለምንረዳ ነው” ብለዋል የኤርትራው ፕሬዚዳንት፡፡
አወዛጋቢ በሆነው ባድመ አካባቢዎች መኖሪያ ቤቶች እንደ አዲስ እየተገነቡ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤ ጉዳዩን በትዕግስት እያየን ያለነው በጠ/ሚ  ዐቢይ የተጀመረውን የሪፎርም ሂደት የማደናቀፍ እቅድ መሆኑን ስለምንገነዘብ ነው ብለዋል፡፡      

Read 15180 times