Print this page
Sunday, 16 February 2020 00:00

የአንድነት ፓርክ - በጉብኚዎች ዓይን

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከአዘጋጁ፡-
Tripadvisor በተሰኘ ድረገጽ ላይ አንድነት ፓርክን በተለያዩ ጊዜያት የጎበኙ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገር ዜጎች አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡ ስለ ፓርኩ የተሰማቸውን ያስደነቀቃቸውን፣ ያስደመማቸውን፣ ያበሸቃቸውን -- በዝርዝር የገለጹ በርካቶች ናቸው፡፡ ለማሳያ ያህል አምስቱን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተርጉመን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡


            የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል
በቅርቡ የተከፈተው ፓርክ ሙዚየም፣ መናፈሻ፣ የክልል ጐጆዎችና የህፃናት የመጫወቻ ሥፍራን የያዘ ነው፤ የምግብና መገበያያ ሥፍራም አለው፡፡ በቅርቡ አንበሶችና የዱር እንስሳት ፓርክም (zoo) ይኖረዋል፡፡ ፓርኩ በቅጡ ታቅዶ የተሰራ ነው፤ ፍተሻው ግን ጠንካራና ጥብቅ መሆኑን አውቃችሁ ተዘጋጁ፡፡  የመግቢያ ትኬት ከኦንላይን መግዛት ትችላላችሁ፤ቀኑንና ጊዜውን (ጠዋት ወይም ከሰዓት በኋላ) በመወሰን፡፡  
የጉብኝት ጊዜ፡- ኖቬምበር 2019
(ምዙንጉባቤ፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ)

ዕፁብ ድንቅ
ለአንድ ቀንም እንኳ አዲስ አበባ የመሆን ዕድል ከተገኘ፣ አንድነት ፓርክ ሊጎበኝ የሚገባው ሥፍራ ነው፡፡ ቤተ-መንግስቱን ለመጀመሪያ ጊዜ የጐበኘሁት ከጥቂት ዓመታት በፊት ለለቅሶ ገብቼ ነው፡፡ ያን ጊዜ ከነበረው አሁን እስካለው ድረስ ያለው  ለውጥ በስሜት የሚያጥለቀልቅ ነው፡፡
የ8 እና 9 ዓመት ልጆቼን ይዤ ነበር ወደ ፓርኩ የሄድኩት፡፡ እኔን ያስደሰተኝን ያህል እነሱም አስደስቷቸዋል፡፡ የዕጽዋት ሥፍራው፣ የአፄ ምኒልክ የ“ሰም” ምስል፣ እንዲሁም የኃይለሥላሴ፤ አዳራሾቹ ጭምር … ዕጹብ ድንቅ  ናቸው፡፡
የህንፃዎቹ ኪነ- ህንፃ፣ ላይ ሰዓታትን የማሳለፍ ፍላጐት ያሳድርባችኋል፡፡ ህንፃዎቹን የምትጎበኙ ከሆነ፣ በጋይድ እየታገዛችሁ አድርጉት - ክፍያው ወደድ ቢልም፣ በጥቅሉ እያንዳንዷን ሳንቲም የሚመጥን ነው፡፡
እባካችሁን፤ ይህን ዕፁብ ድንቅ ፓርክ መጐብኘት፣ በወደፊት ዕቅዳችሁ ውስጥ ማካተታችሁን አረጋግጡ፡፡
የጉብኝት ጊዜ፡- ዲሴምበር 2019
(ኒና ኤስ፤ አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ)
ሊጐበኝ የሚገባው ምርጥ ሥፍራ
መጐብኘት ያለበት ዕፁብ ድንቅ ሥፍራ ነው! የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎች፤ ሁሉም በአንድ ፓርክ የሚገኙበት፡፡ እያንዳንዱን ሥፍራ ወድጄዋለሁ! አዲስ አበባን ለመጐብኘት በእርግጥም በቂ  ምክንያት ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ ድንቅ ሥራ ነው፤ አበጁ!!
የጉብኝት ጊዜ፡- ዲሴምበር 2019
(ሰላም ወርቁ)

 ለህፃናትና ቤተሰብ ውድ የሆነ ድንቅ ሥፍራ
ይሄ በእጅጉ ልዩ ሥፍራ ነው፤ በአፍሪካ (ከደቡብ አፍሪካ ውጭ) ከሚገኙ ምርጥ ሙዚየሞች አንዱ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ግሩም ሆኖ የተሰራ ነው፤ ቀልብ በሚስቡ አያሌ ገጽታዎች የተሞላ፤ ከኢትዮጵያ አስቸጋሪ ያለፈ ጊዜ አንፃር ጥሩ ማካካሻ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የግድ መታየት የሚገባው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ፣ አንዳንድ ችግሮች ነበሩ፡-
የዋጋ መረጃ አለመኖር፡፡ ድረገፁ የወረደ ሲሆን በመግቢያው በር ላይ ስለ ዋጋ የሚገልጽ ነገር የለም፡፡ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪነቴ፣ “ስታንዳርድ ትኬቶችን” ገዝቼ ነበር፡- ለቪአይፒ 1000 ብር እና ለመደበኛ 200 ብር ከፍዬ፡፡ እዚያ ስንደርስ ግን የነዋሪነት መታወቂያዬ ዋጋ እንደሌለው ተነገረኝ፡፡ እናም በውጭ ዜጐች ተመን፣ 50 ዶላር/1500 ብር ለቪአይፒ እና 20 ዶላር/600 ብር ለመደበኛ ከፈልኩ፡፡  
የህፃናት ተመን የለም፡፡ ለ3 ዓመት ህፃን ልጄ፣ በአዋቂ የዋጋ ተመን እንድከፍል ሲነገረኝ ደንግጫለሁ፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ ለሆነ ሁሉ በአዋቂ ተመን ነው የሚከፈለው (ግን የትም ቦታ አልተፃፈም) በተዘዋወርኩባቸው አገራት፣ ለሁለት ዓመት ህፃን፣ በአዋቂ ተመን የከፈልኩበትን ቦታ አላስታውስም!
 የደህንነት ፍተሻ፡፡ የፍተሻ ሰራተኞች ወዳጃዊ አቀራረብ የላቸውም፡፡ ወደ ውስጥ ተይዞ የማይገባው ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ የልጃችንን የውሃ ጠርሙስ ይዘን እንዳንገባ መከልከላችንን ጨምሮ፣ የኤርፖርት ዓይነት ስታይል ነው፡፡ ውሃ ከውስጥ እንድንገዛ ተመክረናል፡፡ ለብዙ ወጪ የሚዳርግ ሲሆን ቤተሰብ-ተኮር አይደለም (የአንድ ዓመቷ ልጄ ወተቷን ሊወስዱባት ሲሞክሩ አልቅሳለች)፡፡
በአሳዛኝ ሁኔታ፤ ወደ ውስጥ ስንገባ ስለተበሳጨን፣ ጉብኝት ከመጀመራችን በፊት፣ ለመረጋጋት፣ ጥቂት ደቂቃዎች አስፈልጐን ነበር:: ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር ድንቅ ነበር፤ በሳር/ጠጠር ላይ እንዳንራመድ ከተነገረንና ገና ብዙ ሥራ እየተከናወነ ከመሆኑ ውጭ (ይሄም ውዱን ዋጋ ይበልጥ አብሻቂ ያደርገዋል)፡፡
እነዚህ ችግሮች መፍትሔ ይበጅላቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ የዋጋ ተመኑን በመከለስ ነዋሪዎች ደጋግመው እንዲጎበኙት ያደርጋሉ ብዬ እጠብቃለሁ፡፡ የማያደርጉት ከሆነም፣ በድጋሚ መሄዳችን አይቀርም፤ ነገር ግን ህፃናቶቹን በነፍስ ወከፍ 20 ዶላር ከፍሎ ማስገባት ተገቢ  አይደለም፡፡
የጉብኝት ጊዜ፡- ኖቬምበር 2019
(ጃፔ፤ አዲስ አበባ)

መጎብኘት  የሚገባው!
ውብ ሥፍራ፡፡ ትኬት መግቢያው ላይ ለእያንዳንዳችን በ600 ብር ገዛን (አስጐብኚ አልቀጠርንም፤ በዚህ የተነሳ ወሳኝ ጉዳይ እንዳመለጠንም አልተሰማንም)፡፡ እቦታው የደረሰውን ጠዋት ከ4 ሰዓት በኋላ ሲሆን ምንም ወረፋ አልነበረም (በኋላ ላይ ሰው በዝቶ ነበር):: የታሸገ ውሃና በርቀት የሚያሳይ መነጽር ፍተሻ ላይ ተወስዶብን ነበር (ጨርሳችሁ ስትወጡ መቀበል ትችላላችሁ፤ግን ካስታወሳችሁ ነው… እኔ ትዝ አላለኝም)፡፡ ወደ 3 ሰዓት ገደማ በስፍራው አሳልፈናል፤ጉብኝቱን በሁለት ሰዓት ውስጥም ማጠናቀቅ ይቻላል፤ ከወደዳችሁት ግን አራት ወይም ከዚያ በላይ ሰዓታትን በቀላሉ ልታሳልፉ ትችላላችሁ፡፡
አብዛኛው የፓርኩ ክፍል አሁንም በግንባታ ላይ ነው (ለምሳሌ፡- ዋናው የእንስሳት ፓርክ)፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አያሌ የሚታዩ ነገሮች ነበሩ፤ የደርግ የቀድሞ እስር ቤትን የተመለከተ በቅጡ የተደራጀ ማስረጃ፣ እንዲሁም የሃይማኖትና ፖለቲካ ታሪክ … ማስረጃዎች፣ እንዲሁም የንግስት ሳባን ታሪክ የሚያሳይ  መግለጫን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ የተለያዩ ባህላዊ ክልሎችን ለማሳየት የተዘጋጀው ውጭያዊ ኤግዚቢት፣ የጥንቱ ዓለም ከአዲሱ ሲገናኝ የሚታይ ድንቅ ጥምረት ነበር::
የመታጠቢያ ክፍሎቹ ንጹህ ናቸው፤ በቅጡ የተሰናዳ የምግብ/ካፌና የመገበያያ ሥፍራ አለ (ለምሳና ሳንድዊቾች፣ ለባህላዊ ምግብ፣ ፒዛና ኬኮች፣ ግሩም ነው - ፒዛና ሁለት ቡና በ200 ብር ይገኛል)፡፡ ለሕጻናት በጣም አዝናኝ የመጫወቻ ሥፍራም ተዘጋጅቷል፡፡ ይሄን ሥፍራ እንድትጐበኙት አበክሬ እየጠቆምኩ፣ በቅርቡ ለሌላ ጉብኝት ተመልሼ እመጣለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡   
የጉብኝት ጊዜ፡- ፌቡራሪ 2020
(ጄኒፈር ቢ፤ ሴንት ጆንስ፤ ካናዳ)

Read 2335 times
Administrator

Latest from Administrator