Saturday, 15 February 2020 12:01

‘የሴረኛ ጥላ’ ሲፈተሸ

Written by  በታደለ ገድሌ ጸጋየ
Rate this item
(1 Vote)

የመጽሐፉ ርእስ - የሴረኛ ጥላ ( ልብ ወለድ)
ደራሲ - ገብረ ክርስቶስ ኃይለ ሥላሴ
ዘመነ ኅትመት - 2012 ዓ ም
የገጽ ብዛት - 342
የመጽሐፉ ዋጋ - 200 ብር፤
ኅትመት - ዜድ ኤ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ፤

               በደራሲ ገብረ ክርስቶስ ኃይለ ሥላሴ ተደርሶ በቅርቡ ገበያ ላይ የዋለውን “የሴረኛ ጥላ” መጽሐፍ ያነበብኩት በተለየ  ስሜት ነው፡፡ መጽሐፉ ጽንፈኞች የሆኑት የሀገራችን ፖለቲከኞች በፈጠሩብን ደባ በዘር፤ በጎሳ፤ በክልል፤ በቋንቋ ለያይተው፤ ኤርትራ እንድትገነጠል አመቻችተው፤ ያንድነትን ሳይሆን የመለያየትን ሤራ ጠንስሰው፤   የኢትዮጵያን ሕዝብ አረንቋ ውስጥ ከትተው፤ የጨለማና የመከራ ዘመን እንዲገፋ፤ እንዲፈናቀል፤ እንዲሰደድና፤ እንዲሞት--ያደረጉት መሆኑን በተሳሉት ገጸ ባሕርያት መስታወትነት ያሳየናል፡፡ መድረኩን በውይይት የሚከፍቱት ዶ/ር ፊሊጶስ ፋሲልና ተስፋ በዛብህ ናቸው፡፡
የመጽሐፉ መታሰቢያነት የተሰጠው በአለፉት 27 የግፍና የሥቃይ ዘመናት በሀገራቸው ለመኖር ፈተና ለሆነባቸው፤ እንዳይሠሩ፤ በሤራ ፖለቲካ እንዲሠወሩና በስውርም እንዲገደሉ ለተፈረደባቸው ኢትዮጵያውያን  ነው፡፡ መጽሐፉ መግቢያና ሃያ አንድ ምዕራፎች አሉት፡፡ ምዕራፎቹ የዘመኑን ክፋትና የፖለቲከኞችን ሤራ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ለአብነት: ደንቀራ፤ ልክፍት፤ ጥንስስ፤ ድፍርስ፤ ውጥረት፤ ፍንዳታ፤ ጣፋጭ: መርዝ፤ መሰቀቅ፤ መቀጨት፤ አባዜ፤ ወጥመድ፤ ድንቅፍቅፍ፤ የሕልም፡ ሩጫ፤ የሴረኛ፡ጥላ፡ የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ርእሶች ከሽብር ፈጣሪዎቹ መንፈስ የፈለቁና ሰላማዊውም ነዋሪ ሰላሙን ያጣባቸው እሳቤዎች ናቸው፡፡
መቼቱ አዲስ አበባ ሲሆን በእግረ ኪደት (ረገጣ) ባድሜ ደርሶ መላ ኢትዮጵያን ያዳርሳል፡፡ ኤርትራ እንድትገነጠልና ሌሎች ክልሎችም ለመገንጠል ቢልጉ በሚል በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 39 የመገንጠል መደላድሉን ያመቻቹት  የቀድሞው  ጠቅላይ ሚኒስትር ‘የኢትዮጵያ ግዛት ባድሜ በወራሪው የሻእቢያ መንግሥት ተደፈረች’ ብለው ለካቢኔዎቻቸው ከአሳወቁበት ወቅት ጀምሮ ወሬው የአዲስ አበባ ሕዝብ መነጋገሪያ ሆኖ ይሰነብታል፡፡
የመንግሥት ሠራተኛው፤ ሥራውን ትቶ በየቢሮው፤ በየቡናውና በየቦንቦሊኖው ቤት ስለተደፈረችው ምድርና ስለ ወራሪው እያነሣ ወሬውን ይሰልቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ጀሌዎቻቸው ጫት በድብቅ ስለሚቅሙበትና ስለሚመካከሩበት ቦታም የት እንደሆነ  ከወሬ ሱሰኞች እንረዳለን፡፡ይህ በዚህ እንዳለ ስለ ዐባይ ውኃ አጠቃቀም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰየሙት ባለሙያዎች እነ ዶክተር ፊሊጶስ ፋሲልና እነ ተስፋየ በዛብህ፤ ከሌላ አገር የሥለላ ድርጅት ጋር የሚሠራው ናሁ ሠናይ  የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ ሲወያዩ እናያለን:: በተለይም በምጣኔ ሀብት ከእንግሊዝ  ሦሥተኛ ዲግሪውን ያገኘው ዶክተር ፊሊጶስ ኤርትራ ቀይ ሽንኩርት አምርታ በመሸጥ ከፍኛ ገቢ ለማግኘት  የሚያስችል ጥናት አድርጎ ነበር፡፡ መገንጠሏ ጎዳት እንጂ፡፡
ዶክተር ፊሊጶስ  ለረጅም ዓመታት ትልልቅ ባለ ሥልጣናትን፤ በተለይም ዋናና ምክትል ጠቅላይ  ሚኒስትሮችን በማማከር የሚሠራሰው ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትእዛዝ ከእርሱ ጋር ስለ ዐባይ ውኃ አጠቃቀም በቡድን ተከፋፍለው የሚሠሩት ጓደኞቹ ስለ ዠማና ከሰም ፤ተከዜ፤ስለ ግልገል ጊቤ፤ ስለ ጢስ ዓባይ፤ ስለጣና በለስ፤ስለ ዋቢ ሸበሌና ገናሌ፤ ስለ አኮቦ፤ ስለጊቤ፤ ዴዴሳ፤ ስለ ወንጭትና አንገረብ፤ ባሮ፤ ወንዞች ጥቅም ጭምር ሲወያዩ የኤሌክትሪክና የመስኖ ልማት በሀገራችን የተፋጠነ እስኪመስለን ድረስ ይሰማናል:: የውኃ አጠቃቀሙም እንደተለመደው ለሱዳንና ለግብጽ ያደላ እንዳይሆን ባለሙዎቹ ይመካከራሉ:: ምክንያቱም ለዘመናት ሀብታችንን አሳልፈንና ለባዕዳን ሰጥተን ረሀብተኞችና ተመጽዋቾች ሆነን ስለኖርን ነው፡፡ እናም  ይህ አሳፋሪ ታሪክ በውኃ አጠቃቀማችን ላይ እንዳይደገም ባለሙያዎቹ በብርቱ ሲከራከሩ ይስተዋላሉ:: በመጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው፤ በቀላሉ የሚክዱ፤ የሚያፈቅሩ፤ የሚጠሉ፤የሚታመኑ፤የማይታመኑ ውሽልሽልና ጠንካራ ገጸ ባሕርያት ከቁመናና ከአካባቢ ገለጻ ጋር በየዕለቱ ከእኛ ጋር ያሉና የምናውቃቸው እስኪመስሉን ድረስ ይናፍቁናል፡፡  
ለአብነት ያህል በራሱ ውስልትና ምክንያት በኤች አይ ቪ  ኤድስ ቫይረስ ባለቤቱንና ልጁን ያጣውና ራሱም ከሰውነት ውጭ የሆነው ተበጀ ገመዳ፤እነ ግርማይ አስገዶምና መዓዛ፤ በረከት፤በሥነ ምግባሯና በአኗኗሯ የተመሰገነቺው መልከ መልካሟ  ኤርትራዊቱ ሐኪም ንግሥት፤ ትንቢት ግርማይ፤ተፈሪ ተስፋየ--- የየራሳቸው ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡ግርማይና ተስፋየ ስለ ልጆቻቸው የፈተና ውጤት፤ ስለምደባቸው የሚጨነቁ ወላጆች ናቸው፡፡ ኤርትራዊው  ግርማይ አስገዶም  የኢትዮጵያን ብሔራዊ የሕግ መምሪያ በኃላፊነት ሲመራ ሀገሬ ለሚላት ኤርትራ  ክፍለ ሀገር ከኢትዮጵያ ተገንጥላ  እንደ ሀገር ለመቆጠር በምትፍገመገምበት ጊዜ  በትልቅ ሥልጣን ላይ መቀመጡ አስደስቶታል፡፡ትን
ቢት ግርማይና ተፈሪ ተስፋየ- ዘር ግድግዳ ሆኖ ያልከለላቸው በእጅጉ የሚከባበሩና የሚዋደዱ ወጣት ተማሪዎች ናቸው፡፡
በድንገት በአንድ ቄስ  አቧሬና ቀበና  ወንዝ አካባቢ የተጣለ ደንቀራ የብዙ ቤተሰብ ሕይወት ሲያተራምስ ይታያል፡፡ ልብ ብሎ ድርጊቱን ለተከታተለው ደንቀራና ዐባይ ጠንቋይ ሕዝቡን በዘር ከፋፍሎ የሚያምሰው ፖለቲከኛው ነው፡፡ በዚህ ትርምስ መኻል ተስፋየ የሦስተኛ  ዲግሪ መመረቂያ ጥናቱን ጨርሶ ከተመረቀ በኋላ ለጥናቱ ተግባር በተመደበቺው ኤሊኮፕተር ወደ ባሕር ዳር፤ ከዚያም ወደ መተከል ጉባ ሸለቆ ሲጓዝና በአካባቢው ቅኝት ሲያደርግ፤ አድልዎና መድልዎ ያለበትንና ለአንድ ክልል ብቻ ትኩረት የሚደረግበትን  አሠራር ሲያወግዝ  እናስተውላለን፡፡ተስፋየ ሐቅን ተከትሎ ለመሥራት ሲፈልግ ልክ እንደራሱ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ አማካሪ የሆነው ደ/ር ፊሊጶስ ግን እንዲሰክን፤ እንዲረጋጋ ይመክረዋል፡፡  የሀሪቱን ሀብት በማግበስበስ ከርሳቸው የማይጠረቃ ለከት በሌላቸው ቢስቶች፣ ተምቾች ሀገሪቱ እንደተከበበች በጉባ የኤሌትሪክ ግድብ በማሰራት ሰበብ ወርቁን እያፈሱ በለመዱት መንገድ ሲከቸልቡት የሴረኛ ጥላ ያሳየናል፡፡
የኢትዮጵያ ፓርላማ ተቻኩሎ የባድሜ  ጦርነት እንዲደረግ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ ሁለቱን ሀገሮች ማሸማገል ተገቢ እንደነበር በረከት ግርማይ  ጦርነቱን ኮንኖ ይናገራል፡፡የሤረኛ ጥላ እስከወዲያኛው ድረስ  የሰውን ልጅ ይከተላልና  ጦርነቱ ባስከተለው ጦስ ታጣቂዎች ወደ ቀበና የሚወስደውን መንገድ ግራና ቀኝ ከበው አውቶቢሶች ተራ በተራ ሲንቀሳቀሱ ተጔዞች እጆቻቸውን ሲያውለበልቡ፣ ትዕንቢት አንገትዋን በመስኮት አውጥታ “እኔ ሀገሬ እዚህ ነው፣ ዕትብቴ የተቀበረውም ኢትዮጵያ ምድር ነው፣ ከወገኔ አትለዪኝ” እያለች ስታነባ ህዝቡም ጊዜ ሆይ ፍረድ እያለ ተቀባብሎ ጮኸ፡፡ አውቶቢሶች ጡሩንባቸውን እያስጮሁ ወሰ ሰሜን ነጎዱ  አዲስ አበባና በሌሎች ክልሎች  ውስጥ ተወልደውና ከነዋሪውም ጋር ተዛምደው የሚኖሩ የኤርትራ ሰዎች ሀብትና ንብረታቸውን ሳይዙ ሲፈናቀሉ፤ ሲሰደዱና ሲያለቅሱ፤ ተንኮል፤ ክፋትና ዘረኝነት የሌለው  ደጉ የአዲስ አበባና ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያስቀራቸው ቢፈልግም፤ እንደ እናት እያለቀሰና ዕንባዕ  እያፈሰሰ በደግነት፤ በቸርነት ሲለያያቸው፤ሲሸኛቸው የሴረኛ ጥላ እንደመስታወት ያሳየናል ፡፡ ቤተ ሰብ፤ ወዳጅ ዘመድ ይበታተናል፤
ትንቢት ግርማይ  በአጋጣሚ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ፡ትጓዛለች፡እዚያም
‘የኢትዮ ኤርትራ ዳግም ጥምረት’ የሚል ዓለም አቀፍ  ድርጅትመሥርታ፤ ስትመራ፤ ስታስ ተባብር፤ ወንድሟን በረከትን፤ አፍቃሪዋን ተረፈን ስትፈልግ እናያታለን፡፡ጊዜ ደግሞ አል ፋና ኦሜጋ ነውና እነዚህ በግፍና በተንኮል  እንዲለያዩ የተደረጉ ሕዝቦች ውሎ አድሮ ሊገናኙና አንድ ሊሆኑ እንደሚችሉ ደራሲው ያለውን እምነት ገልጧል፡፡እናም  ይህንን ለታሪክ ማጣቀሻነት ጭምር የሚያገለግለውን  ውብ መጽሐፍ ማንበብና ትምህርተ ኅቡአቱን መመርመር  ስለሚጠቅም ቀሪውን ለአንባቢዎች ትቸዋለሁ፡፡

Read 1464 times