Print this page
Saturday, 15 February 2020 11:59

ቫለንታይን ወዴት እያመራ ነው?

Written by 
Rate this item
(4 votes)

   ከቅርብ ዐመታት በኋላ ፈረንጅ ፈረንጅ የሚሸቱ ነገሮች በእንግድነት ወደ ሃገራችን ገብተው ተመልሰው ከመውጣት ይልቅ ተንሰራፍተውና ተመቻችተው እየኖሩ ይመስላል፤ ምናልባትም መኖራቸው ሳያንስ የራሳችንን አሻራ ሳያጠፉም የቀረ አይመስልም፡፡ነገሩ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ነውና ልንወያይባቸውና በጊዜ መስመር ልናበጅላቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ወደቤታችን መጥቶ የተራገፈው ሸቀጥ፣ ነገ ቤታችንን ሊያፈርሰው ይችላል፡፡
 በየዐመቱ እንደዋዛ ብቅ ብለው ይጠፋሉ ስንላቸው፣ ስር ሰድደው፣ለገበያ ፍጆታ መዋልና የማስታወቂያ የአየር ሰዐት ማጣበብ ከጀመሩት ነገሮች ውስጥ አንዱ ‹‹የፍቅረኞች ቀን›› እየተባለ የሚጠራው ቫለንታይን ነው፡፡
የፍቅረኞች ቀን ሲባል ስሙ ደስ ይላል፤ፍቅርን የሚጠላም የለም፡፡ችግሩ ውስጡ ሲፈተሸ፣ጓዳው ሲበረበር ነው፡፡ፈረንጆች እንደኛ ያለወግ ይጫወቱበት፣ ወይም በስርዐት ያክብሩት ባላውቅም እኛ ሃገር ግን መስመር እየለቀቀ ወደ ወሲብ ገበያነት እያደገ መጥቷል፡፡
ፍቅር ትዳርን ለማክበር፣ ለወግ ለማዕረግ ካበቃ መልካም ነው፡፡ ፍቅር ለመተሳሰብ፣ ለመከባበር መንግድ ከሆነ ደስ ይላል:: ዘማዊነት ግን የፍቅር መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡
አሁን በኛ ሃገር እየታየ ያለው መልካም አይደለም፡፡ ጉዳዩ የፍቅረኞች ቀን ሳይሆን የዘማውያን ቀን እየሆነ ነው፡፡ ፍቅር ያለ አካል አንድነት አይሆንም›› ብንልም ያ ቀን በትዳር ለተሳሰሩ፣ በእጮኝነት ላሉ ቃል ኪዳን የማደሻ ቀን እንጂ ገና ሕይወታቸውን በቅጡ መምራት የማይችሉ ጨቅላዎችን ሕይወት መቅጠፊያና መንገዳቸውን ማሳሳቻ መሆን የለበትም፡፡
ሬድዮውና ቴሌቪዥኑ የማስታወቂያ ድቤውን በደበደበ ቁጥር የወጣቶችን ልብ በመስረቅ፣ ለተሳሳተ የሕይወት አቅጣጫ እያመቻቸ እንደሆነ ልብ ያልነው አልመሰለኝም፡፡ ትምህርታቸውን ማጥናት ትተው ወደ አደባባዮች መጥተው እንዲቀላቀሉን የዝሙት ነጋሪት መጎሰማችን የጠፋንም ይመስላል፡፡
ፍቅረኞች ቀን ስጦታ መሠጣጫ፣ መገባበዣ፣ መወያያና የቀጣይ ሕይወት ውይይት አጋጣሚ እንጂ ባህልን ባልጠበቀና ጨዋነት በጎደለው ሁኔታ ሰክሮና ተንዘላዝሎ መገኘት አይደለም፡፡
‹‹ፍቅር›› ስንል በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠቀለሉ በርካታ መገለጫዎች እንዳሉት የስነጋብቻ ምሁራን ይናገራሉ:: ለቤተሰብ፣ ለጓደኛ፣ ለስጋ ዘመድ፣ ለተቃራኒ ጾታ ወዘተ በማለት ይከፋፍሏቸዋል፡፡
ታዲያ ለፍቅረኛም ቢሆን ነፍስና ስጋን የሚያጣምረው ፍቅርና በወሲብ ስሜት የተግለበለበው ስሜት በአንድ ጎራ አይመደቡም፡፡ ኢሮስ የተባለው የተቃራኒ ፍቅር እንኳ በአንድ ከረጢት የሚያዝ አይደለም፡፡
አንድ በፍቅርና በጋብቻ ጉዳይ የጻፉ ተመራማሪ እንደሚሉት፤ ብዙ ሰዎች ፍቅርን በሁለት ተቃራኒ ጾታ መካከል የሚፈጠር መስተጋብር ብቻ አድርገው ያዩታል፡፡ ለብዙ ዘመናት ፍቅርን ከአንሶላ መጋፈፍ ጋር ተያይዞ ሲታሰብና ሲተረክ ኖሯል፤ ብለው ይናገራሉ፡፡ ያም ብቻ አይደለም፤ከተገለጠው የፍቅር ግንኙነት ይልቅ በስርቆትና በድብቅ የሚደረገው ወሲብ ይጥማል እስከ ማለት ይስታሉ›› ብለዋል፡፡
ኤድ ዌት የተባሉት  ጻሐፊ ፍቅርን‹‹ መንፈሳዊ፣ስሜታዊና አካላዊ መሳሳብና መተሳሰር ነው ››ይሉታል፡፡ ይሁንና ፍቅር አንዴ ተመስርቶ ሳይፈተን ጣሪያ ላይ ተሰቅሎ የሚቆይ አይደለም፤ የሚያድግና የሚታደስ ነው፡፡ አንዳንዶች ሲገናኙ በአፍላ ፍቅር የነበራቸው ስሜት ይጠፋባቸዋል፡፡ ያ ደግሞ እንደገና ሊታደስ የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ እኒሁ የጋብቻ አማካሪጋ ከሙ ሰዎች የተጠየቁትን ነገሮች እንይ፡
 “We have lost the love that we once felt for each other.”
አንዴ አንዳቸው ለአንዳቸው የነበራቸውን የጦፈ ፍቅር ተነጥቀው፣ ሰማይ ሰማይ የሚያዩ ሞልተዋል፡፡ ደግሞ ለጊዜው ትዳራቸው በፍቅር እንዝርት የምትሾር፣ነገር ግን ያንኑ እያሳደጉ መሄድ የሚፈልጉ እንዳሉ ከጸሐፊው ድርሳን እንረዳለን፡፡
“We have good marriage now,but we want to continue to grow in love for each other”.
ፍቅር ስለሚታመምም መታከም አለበት:: የሚታከመውም አንዳንዴ ነገሮች ፈር ሳይለቁ በሚደረግ ግምገማና ፍተሻ ነው፡፡ የፍቅረኞች ቀን ለዚህ አይነቱ ሕክምና ቢውል ደግ በነበረ፡፡ አሁን እንደምንሰማው፤ በዕለቱ የሆቴሎች መኝታ መጣበብና ዘማዊነትን ነው፡፡ ዘማዊነት ደግሞ ትዳር ከማፍረስና ባህል ከማቆሸሽ ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ሲብስም ለሌላ በሽታ ይዳርጋል፡፡ እኛ ሃገር ጥምቀት በዐል ላይ ሎሚ መወራወርም በጨዋ ደንብ ትዳር ለመመስረት እንጂ ያለዕድሜና ያለ ዕቅድ ቀብጦ ሕይወትን ለማበላሸት አይደለም፡፡
<<the one who commit adultery with a woman is lacking sense;he who would destroy himself does it.>>
ከሴት ጋር የሚያመነዝር ግን አእምሮ የጎደለው ነው፤ እንዲሁም የሚያደርግ ነፍሱን ያጠፋል፡፡›› ይህ የጠቢቡ ሰለሞን አባባል ብዙ ሰዎች ላይ ሆኖ አይተናል፡፡ የሕይወት ጣዕም ሲያጠፋ፣ለፍቺ ሲዳርግ ተመልክተናል፡፡ ስለዚህ በየሰበቡ ባገኙበት መጋደም አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን ትውልድ ገዳይ ነው፡፡
ፍቅርም ቢሆን ልንቆጣጠረውና ልንገዛው፣ በወጉ ልንጠቀምበት እንጂ ባሪያው ሊያደርገን አይገባም የሚሉ አሉ፡፡ እኔ ግን ለንጹህና በታማኝነት ለተመላ ፍቅር ባሪያ መሆንም ክፋት ያለው አይመስለኝም::
ይሁንና አንዱ የስነጋብቻ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡፡ love is an active power that I control by my own will.I am not the helpless slave of love. >>
ኢሮስ የተሰኘውን የፍቅር ዘውግ እንደ ወሲብ ቁና አድርገው ቢተረጉሙትም፣ የዘርፉ ምሁራን ግን ጉዳዩ ያ ብቻ አይደለም፤ ብዙ ጊዜ ወደ ትዳር የምንሻገርበት ድልድይ ነው›› ብለው ያደናንቁታል፡፡ እንዲያውም ያ ፍቅር በር ሲያንኳኳ ሁሉም ሰው ግጥም መጻፍና በዜማ ማንጎራጎር ይጀምራል፡፡ እኔ ስጨምርበት ደግሞ የፍቅር ልቦለዶችን ማሳደድ ይጀምራል፡፡ እዚያም ውስጥ ራሱንና ፍቅረኛውን ይፈልጋል፡፡ ሌሊቱ ይረዝምበታል፡፡ ፍቅር ግን ከወሲባዊ ስሜት የዘለለ ዘላለማዊ የመንፈስና የነፍስ ቁርኝት መሆኑ የተጨበጨበለት እውነት ነው፡፡
በግሪክ ቋንቋ ኢፒቱሚያ የተባለው የፍቅር አይነት መጽሐፍ ቅዱሱ እንደ ስጋዊ ምኞት ቢተረጉመውም በባልና ሚስት ጥምረት ግን የራሱ በጎ ድርሻ አለው፡፡ ከወሲብ ያለፈ ጉድኝትና ትስስር ይፈጥራልና!!
ይህ ማለት ደግሞ ለባልና ሚስቱ በባህልም ሆነ በመለኮት የተፈቀደ መንገድ የሚያምር ጎዳና ነው፡፡ የመዘክር ግርማ ቀጣይ ግጥም ውሃ ልኩን ሳትገጥም አትቀርም፡፡
‹‹ከመቼ ወዲህ ነው፣ወፍ ልብስ የምታወልቀው?
ይልቅ እሷን ምሰል፣ ልብስህን አውልቀው!››
   ብላኝ ልብሷን ጥላ
ትታኝ ገሰገሰች፣ወፏን ተከትላ፡፡
‹‹እሺ ስንቅ እንያዝ?››ልላት አሰብኩና
 ተውኩት ሳልጀምረው
የትኛዋ ወፍ ነች፣ ስንቅ ይዛ ምትዞረው?!
በቃ ተከተልኳት፤
ጥብቅ አረገችኝ፣ጥብቅ አደረኳት፡፡
አንደበቴ ሰላ፣ዝማሬ ጀመረው
ልቤ ክንፍ አወጣ፤መንሳፈፍ አማረው
ከመቼ ወዲህ ነው ወፍ የማትበረው?!
ይህ ሁሉ ፍቅር ግን የመንዘላዘል ሕመም ካልተጠናወተው የከበረና የሰው ልጆች የሚቆረፍደውን የሕይወት መንገድ እያደሱና አቅም እየጨመሩ እንዲቀጥሉ ከአምላካቸው የተሰጠ ሥጦታ ነው፡፡ ካከበርነው የከበረ ነው፤ ካረከስነው የረከሰ ይሆናል፡፡ ሕይወታችን በነውጥ እንዳይዋከብ ያለቦታው ከመቅበጥ መጠንቀቁ ይበጃል:: በተለይ ሣይገረዝና ሣይፈተሽ ቀጥታ ድንበር ጥሶ የገባው የፍቅረኞች ቀን በሃገራችን መልክና ሓይማኖታዊ ዳራ ተለውጦ በከበረው መንገድ እንድንጠቀምበት ማሳሰብ የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
ወይ የፍቅረኞች ቀን!!

Read 1820 times
Administrator

Latest from Administrator