Sunday, 16 February 2020 00:00

ከሰሜን ኮርያ ህዝብ ግማሽ ያህሉ አፋጣኝ እርዳታ ይሻል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

      ከሰሜን ኮርያ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ከ45 በመቶ በላይ የሚሆኑት ምግብን ጨምሮ አፋጣኝ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዩፒአይ እንደዘገበው፣ ከ10.4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰሜን ኮርያውያን አፋጣኝ የምግብ እንዲሁም የጤና፣ የንጹህ ውሃና የንጽህና አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ሰብዓዊ እርዳታዎች ድጋፍ ካልተደረገላቸው፣ በአገሪቱ የከፋ ጥፋት ሊከተል እንደሚችልና ይህን ችግር ለማስቀረት 107 ሚሊዮን ዶላር  እንደሚያስፈልግም ተነግሯል፡፡
በአገሪቱ የተፈጥሮ አደጋዎች መስፋፋታቸውና ድሮም የማያወላዳው የግብርና መሰረተ ልማት የባሰ እየተበላሸ መቀጠሉ በፈጠረው የምግብ እጥረት ሳቢያ 10.1 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልጉ የጠቆመው ዘገባው፣ አገሪቱ ከወራት በፊት ባለፈው አስር አመት የከፋውን ድርቅ እንዲሁም አደገኛ ሙቀትና የጎርፍ አደጋዎችን ማስተናገዷንም አስታውሷል፡፡
ከአገሪቱ ህጻናት ከ33 በመቶ በላይ የሚሆኑት ማግኘት የሚገባቸውን አነስተኛ የምግብ መጠን እንደማያገኙና 20 በመቶ ያህሉም በከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚሰቃዩም ተነግሯል፡፡
ከአጠቃላዩ የሰሜን ኮርያ ህዝብ 33 በመቶው ወይም 8.4 ሚሊዮን ያህሉ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንደማያገኝና ከገጠሩ ህዝብ 90 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ለሞት ለሚዳርጉ የጤና ችግሮች ተጋላጭ ሆኖ እንደሚገኝም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንን ጨምሮ አያሌ አለማቀፍ ተቋማት ግን፣ በርካታ ሰሜን ኮርያውያንን ከተፈጥሮ አደጋ በላይ ለከፋ ችግርና ለአስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ የዳረጋቸው ዋነኛ ምክንያት የአምባገነን መንግስቷ የጠበቀ የምግብ ምርትና ስርጭት ቁጥጥር ስርዓትና በጀቱን ለጦር መሳሪያ ፕሮግራሞች ማዋሉ ነው በሚል እንደሚተቹ ዘገባው አመልክቷል፡፡


Read 3168 times