Saturday, 22 February 2020 09:58

‹‹ሁሜዲካ›› 10ኛ ዓመት አከበረ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

ከ40 ዓመታት በፊት በባለ ራዕዩ ሚስተር ዎልፍጋንግ ግሮስ ባካውፍበረን (ባቫሪያ) ጀርመን የተቋቋመውና በበጎ ስራና ሰብዓዊ ድጋፍ ስራ ላይ የተሰማራው ‹‹ሁሜዲካ ኤቪ›› ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ ድጋፍ ሥራ የጀመረበትን 10ኛ ዓመት ባለፈው ማክሰኞ መስራቹ ሚስተር ዎልፍ ጋንግ ግሮስ በተገኙበት አከበረ፡፡ በዓለም ላይ በ90 አገራት በሕክምና፣ በመሰረታዊ የጤና ክብካቤና በዘላቂ ልማት ዘርፎች፣ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ድንገተኛ አደጋዎች ለተጎዱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ስደተኞችና ተፈናቃዮች፣ በድህነት ላይ ለሚገኙና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑ ሕጻናትና ቤተሰቦቻቸው ዘር፣ ቀለም ሀይማኖትና ፆታ ሳይለይ ሰብአዊ ድጋፍ የሚሰጠው ሁሜዲካ ኤቪ፤ በኢትዮጵያም በ2010 ዓ.ም ተመዝግቦ ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፤ ባለፈው ዓመት ደግሞ የእንደገና ምዝገባ የምስክር ወረቀት አግኝቶ እየሰራ እንደሚገኝ፣ የድርጅቱ የአገር ውስጥ ተጠሪዎች በክብረ በዓሉ ላይ ተናግረዋል፡፡ የእርዳታ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ጽ/ቤቱ አማካኝነት በመሰረታዊ የጤና አገልግሎትና የጤና ማዕከል ግንባታ፣ በድህነት ውስጥ ለሚገኙ በተለይም ለሴት ቤተሰብ አስተዳዳሪዎች፣ የኑሮ ማሻሻያ ገቢ ማስገኛ መነሻ ካፒታልና የስልጠና ድጋፍ በመስጠት፣ በወርሃዊ የምግብ አቅርቦት፣ እንዲሁም በመዋዕለ ሕጻናት ግንባታዎች ላይ ሲንቀሳቀስ የቆየ የበጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑ ተገልጿል፡፡   
በ10ኛ ዓመቱ ክብረ በዓል ላይ የድርጅቱ ዋና መስራች የኢትዮጵያዋ ተጠሪ ሚስ ሱዛን ሜርኬል፣ አቶ ሞትባይኖር አበራና የድርጅቱ ሰራተኞች እውቅናና ምስጋና አግኝተዋል። በቀጣይ ከመሰረተ ልማት ርቀው የሚገኙ የህብረተሰቡ ክፍሎች የድርጅቱን አገልግሎት የሚያገኙበት አዲስ ፕሮጀክትና የቃል ኪዳን ማደስ ስራም ተከናውኗል፡፡

Read 2697 times