Saturday, 22 February 2020 09:58

ለማናቸውም ድርጊትህ ጊዜ ምረጥ፤ ጊዜ መስጠት ለማይገባው ነገር ጊዜ አትስጥ

Written by 
Rate this item
(15 votes)

      ከዕለታት አንድ ቀን የዱር አራዊቶች ተሰባስበው አያ አንበሶ ስለታመመ “እንዴትና መቼ እንደምንጠይቀው እንወያይ” እየተባባሉ ሃሳብ እንዲሰጥበት አንድ በአንድ ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡
ዝሆን - “እንደሚታወቀወ አያ አንበሶ ለብዙ ዓመታት ጌታችንና ንጉሣችን ሆኖ የቆየ ባለ ግርማ ሞገስ መሪያችን ነው፡፡ ስለዚህ አሁኑኑ ሄደን እንጠይቀውና ልንረዳው የምንችለው ነገር ካለ በዐይናችን በብረቱ ዐይተን፣ ከራሱ ልሣን የምንሰማውን ችግሩን አድምጠን፤ የምናደርገውን እናድርግ” አለ፡፡
ቀጥሎ የአቶ ነብሮ ተራ ሆነ፤
“እኔም ጌታ ዝሆን ያለውን ነው የምደግፈው፡፡ ስንት ዘመን በሥነስርዓት ሲገዛንና ሲያስተዳድረን የኖረውን የዱር አራዊት ንጉሥ ቢታመም ማሳከም፣ ራበኝ ጠማኝ ቢል ማብላት ማጠጣት ይጠበቅብናል፡፡ ስለዚህ ወደዚያው እንሂድ ነው የምለው፡፡”
ቀጥሎ ዝንጀሮ ተነሳና፤
“ግዴላችሁም የአያ አንበሶን ነገር ከጥንት ከጠዋት ጀምራ መላውን የምታውቀው ጦጢት ስለሆነች እሷ የምትለውን ብንሰማ ደስ ይለኛል፡፡”
ተኩላ ቀጠለ፡-
“እኔም የአያ ዝንጀሮን ሃሳብ ነው የምደግፈው፡፡ ጦጢት የምትለውን እናዳምጥ፡፡”
ድኩላ በበኩሉ፤
“ግዴላችሁም ወዲህ ወዲያ ማለታችንን ትተን ቀጥታ አያ አንበሶ ቤት ሄደን ጡረታም መውጣት ይፈልግ እንደሆን፣ ድኖ ዳግመኛ መምራት ይሻም እንደሆነ… ከራሱ አንደበት እንስማ:: ስለዚህ ሳንውል ሳናድር ወደዚያው ሄደን እናረጋግጥ፡፡”
በማህል ጦጢት እየሮጠች መጣች፡፡
“ጦጢት ምን ትያለሽ?” ተባለች፡፡
“አንድ መልዕክተኛ እንላክና ሁኔታውን አጣርቶ ይንገረን” አለ አዞ፤ ከጦጣ በፊት፡፡
አዞን ተከትሎ ዘንዶ ተናገረ፤ “ከጦጣ በፊት መናገር መርጫለሁ፡፡ እዚህ ተቀምጠን ይሄ ይሁን ያ ይሁን ከምንል ቀጥ ብለን ሄደን በዐይናችን በብረቱ አይተን እንፍረድ” አለ፡፡
በመጨረሻ፤
“ጦጢት ምን ይሁን ትያለሽ ታዲያ?” ተባለች፡፡
ጦጢትም፤
“ግዴላችሁም ጊዜ ሰጥተን እንይ፡፡ ወይ አያ አንበሶ ይድናል፡፡ አሊያም እግዜር ካለልን ይሞታል፡፡ ብቻ አደራ አያ አንበሶ ያልኩትን እንዳይሰማ፡፡ ፀጥ እርጭ በሉ - አደራ፤ እኔ ግን ዕውነት ተናገሪ ካላችሁኝ… አያ አንበሶ ሲሞትም ይምረናል ብዬ አላምንም?”
አለችና እቅጩን ተናገረች፡፡
***
ክፋትና ጉልበት አለው ብለን የምናምነውን ሁሉ መፍራትና ባልሰማብኝ ብሎ መስጋት ያለ ነው፡፡ በተለይ የህገርና የህዝብ ጉዳይ ነው የምንለው ነገር ላይ ከሆነ ስጋታችን በጣም ይጨምራል፡፡ አንዳንዱ ጉዳዩን ከፖለቲካ ጋር ያዛምደውና ላብ ላብ ይለዋል፡፡ አንዳንዱ ምንም ይሁን ምን ስሜት አይሰጠኝም የሚል ይሆናል፡፡ ኑረዲን ኢሣ ያለውን ማስታወስ ይበጃል እዚህ ጋ፡-
“እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሀረግ
እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደበግ
ብዬ ግጥም ልፅፍ ተነሳሁኝና
…ምን አገባኝ ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና!”
ምን አገባኝ የማለት አባዜ አይጣል ነው!
ይሄ የእኔ ጉዳይ አይደለም እያልን የምንተወው ብዙ ነው፡፡ ይሄን ዓይነቱ አመለካከት ውሉ አድሮ ክፉውንም ደጉንም ደርቦ የመጨፍለቅ ችግር ላይ ይጥላል፡፡ እስከ ዛሬ በዲሞክራሲ፣ በእኩልነት፣ በወንድማማችነት፣ በፍትሐዊነት፣ በመተዛዘንና በመደጋገፍ ዙሪያ ያሳየነው ቸልተኝነት ዘለዓለማዊ እስኪመስል ድረስ ሲደጋገምብን የሚኖር ሆኗል፡፡ የፖለቲካ ህይወት “ይደገም አይደገም” የሚባል የፊልም ትርዒት አይደለም፡፡ ከማህበራዊ ሂደት ጋር ተስናስሎ ድርና ማጉን ለይቶ ማየት እስከማንችል ድረስ ሊወሳሰብ የሚችል ነው፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችን አያሌ ናቸው፡፡ ጊዜ እየረዘመ ሲሄድ የሚረሱም፤ የሚድበሰበሱም፣ ከናካቴው ደብዛቸው የሚጠፋም አያሌ ናቸው፡፡
በተለይ የኢኮኖሚ ጥያቄዎቻችንን በቅጡ አለማጤን ጣጣው የትየለሌ ነው፡፡ እንዳዲስ ደግመው ወደ ጠረጴዛው ብቅ የሚሉበት ሰዓት ግን ሊመጣ እንደሚችል አለመዘንጋትም፣ አለመዘናጋትም ደግ ነው፡፡ ሀገራችን ብዙ ታይቶ ጠፊ (Volatile) ክስተቶች ማስተናገዷ ከቶም አዲስ አይደለም፡፡ ጊዜና ቦታ እየመረጡ የሚመጡ ሂደቶችን በቅጡ አጥርቶ ማየት ይገባል፡-
እንደ ሼክስፒር፤
“ዛሬ ለወግ ያደረግሺው
ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው
ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞም የሠለጠነ እንደሁ
ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል
…ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ዘበት በልማድ የጀመርናቸው ነገሮች ማቆሚያ እንዳያጡ ለከት ማበጀት ያሻል፡፡ ድክመቶቻችንን በወቅቱ እናሸንፍ፡፡ ስለ ትምህርት እንጨነቅ፡፡ ስለ ጤና እንጨነቅ፡፡ አስቦ ሂያጅ እንጂ የድንገቴ መንገደኞች አንሁን፡፡ ለዚህም በተቻለ፤ ጥብቅ ጥናት ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
እንደ እስካሁኑ ያለ አንዳች እርምጃ ቸል የተባሉትን ብዙ ጉዳዮች ወቅታዊ መፍትሔ ከመስጠት ከመቆጠባችን የተነሳ እያደር ለሚገዝፉ ችግሮች እንደምንጋለጥ ልብ አንበል፡፡
“ለማናቸውም ድርጊትህ ጊዜ ምረጥ ጊዜ መስጠት ለማይገባው ነገር ጊዜ አትስጥ” እላለሁ፡፡”


Read 13783 times