Saturday, 22 February 2020 10:00

ገንዘብ ሆድን ‘ከማባበያ’ ኑሮን ‘ወደ ማባበያ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

“እናላችሁ… እሱ መኪና ሲገዛ “ጎበዝ ነው፣” “ኃይለኛ ነው፣” …ምናምን ይባላል፡፡ እሷ መኪና ስትገዛ “አንዱን ጠብ አድርጋ ነው” ምናምን ይባል፡፡ በእርግጥ ‘ጠብ የማድረግ’ ነገር ከምንጊዜውም በላይ ዙሩ የከረረበት ቢሆንም፣ እንዲሁ ሰው ባልዋለበት ለማዋል መሞከሩ አሪፍ አይደለም፡፡--”
         
             እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እስከመቼ ድረስ በብር አባብዬ፣ በብር አባብዬ
ገንዘቤን ላጣራ ወደሽኛል ብዬ፣ ወደሽኛል ብዬ
--ተብሎ ተዚሞ ነበር፡፡ እንግዲህ እርም ማውጣት ነው፡፡ ልጄ ዘንድሮ…አለ አይደል… እሷዬዋ አይደለም እንደ እንትን ሰፈር ልጅ፣ እንደ ክሊኦፓትራ ምናምን አትታይም፣ “ገንዘቤን ላጣራ” ተብሎ የሚፎከርባት ፈረንካ ኬት ይምጣ! ‘ታች’ ሆነን እያወራን እንደሆነ ልብ ይባልልንማ፡፡ (እንትናዬ ምን ሪል ሰቴት ነው ‘ጂ ፕላስ ዋን ልታገኝ ነው ሲሉሽ የነበረው፣ ተሳካ ወይስ መካከለኛ ገቢ ‘ለምንደርስበት’ ዘመን የተያዘ ቀጠሮ ነው?
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንበልና እሱዬው በሆነ ‘ተአምር’ በሚባል ሁኔታ መኪና ይይዛል፡፡ (“ይገዛል” የሚለው ቃል አንዳንዴ የትርጉም ስህተት ሊያመጣ ይችላል በሚል ነው፡፡ “ገዛ” እና “ገዙለት” የተለያዩ ነገሮች ናቸዋ!) ታዲያላችሁ “ለሚኒባስ አምስትና ሰባት ብር ብር አልከፍልም” ብሎ በጠራራ ጸሀይ በእግሩ ከፒያሳ መካኒሳ ሲያቀጥነው የኖረው ሰው ድንገት  እጁን በመስኮት አውጥቶ “አጅሬው አሁንም በአገርህ ታስነካዋለህ!” ይላችኋል:: (ሞራላችን አይደለም መውደቅ እንኩሮ ቢሆንስ ምን ይገርማል!)
እናላችሁ ‘ዘ ቶክ ኦፍ ዘ ታውን’ የሚሆነው ምን መሰላችሁ… “እንዴት ኃይለኛ የሆነ ሰው መሰላችሁ፡፡ ቢዝነስ እያሯሯጠ ነው እኮ የገዛት” ይባላል፡፡
“የምን ቢዝነስ! የመንግሥት ሠራተኛ አይደለም እንዴ!”
“እሱ የሚያገለግለው ለመታወቂያ ነው:: ቢሮው ቁጭ ብሎ እንኳን የራሱን ቢዝነስ ነው የሚሠራው፡፡  ታዲያ በመንግስት ደሞዝ ኤክስኪዩቲቭ ሊገዛልህ ነው!”
እናላችሁ… “ቢዝነስ እያሯሯጠ ነው” በሚል ይያዝለታል፡፡ “ምን አይነት ቢዝነስ?” ምናምን ብሎ ጭቅጭቅ ነገር የለም፡፡ ዘንድሮ ከሚሠራው መደበኛ ሥራ በተጨማሪ ‘ቢዝነስ የሚያሯሩጥ’ ሰው፣ “ኑሮ በዘዴ አውቆበታል” ይባላል እንጂ “ለምን ደሞዝ የሚበላበትን ሥራ ይበድላል?” አይባልም፡፡ ለነገሩ እንደ ዘንድሮ የኑሮ ክብደት አይደለም ሁለትና ሦስት፣ አስራ ሦስት ቦታ ቢሮጥም አይገርምም፡፡
እሷዬዋ ደግሞ አለችላችሁ፡፡ ጎበዝ ሠራተኛ፡፡ “ይቺ ሴት እንዲህ ደፋ ቀና ስትል ትንሽ እንኳን አይደክማትም!” የሚባልላት፡፡  ጥራ ግራ የሆነች በአራት ጎማ በመሽከርከሯ መኪና የሚባል ስም የተሰጣት ነገር ትገዛለች፡፡ እናላችሁ…‘ቶክ ኦፍ ዘ ታውን’ የሚሆነው ምን መሰላችሁ…
“አጅሪት ሹክክ ብላ አንገቷን ደፍታ አንዱን ነጋዴ ጠብ አድርጋለች ማለት ነው፡፡”
“ኸረ እባካችሁ እሷ እንዲህ አይነት ነገር አታውቅም! ጎበዝ ሠራተኛ ነች፡፡ ደግሞ እኮ እጮኛ አላት፡፡”
“ስማ ሞኞ፣ የዘንድሮ እጮኛ ዘወር፣ ዘወር ብለሽ ገንዘብ ስሪ እንጂ የሚል ነው፡፡”
(የምር ግን እግረ መንገድ የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… የኮሌጅ ተማሪዎች ነገር እንዴት ነው! አሀ… አንድ ሰሞን የሴት ጓደኞቻቸውን “ለበርጫ የሚሆን ሸቃቅለሽ ነይ፣” ምናምን እንደሚሉ በመገናኛ ብዙሀን እንሰማ ነበራ! ነገርዬው አለ አይደል…የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ነው፡፡)
እናላችሁ… እሱ መኪና ሲገዛ “ጎበዝ ነው፣” “ኃይለኛ ነው፣” …ምናምን ይባላል፡፡ እሷ መኪና ስትገዛ “አንዱን ጠብ አድርጋ ነው” ምናምን ይባል፡፡ በእርግጥ ‘ጠብ የማድረግ’ ነገር ከምንጊዜውም በላይ ዙሩ የከረረበት ቢሆንም፣ እንዲሁ ሰው ባልዋለበት ለማዋል መሞከሩ አሪፍ አይደለም፡፡
ወዳኛለች ብሎ ያቺን ልጅ ማመን
በቸርቸል ጎዳና ጥንቸል ማባረር
--አይነት ነገር የሚል የቀድሞ ዜማ አለ:: አሪፈ ፈጠራ አይደል! እስቲ ዝም ብላችሁ በቸርችል ጎዳና ቁልቁለት ጥንቸል ስታባርሩ አስቡት! የዘንድሮ ቁልቁለት... እንኳን ጥንቸል አባረንበት እንዲሁ የሚያንደረድር ቁልቁለት በዝቶብናል፡፡ ታዲያላችሁ፣ በአሁኑ ጊዜ እንዲህ አይነት ግጥም ቢገጠም…. አለ አይደል… ግርጌ ማስታወሻ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ “በዚህ ግጥም ላይ ጥንቸል የሚለው ቃል የሚያመለክተው በምትሮጥበት ጊዜ እጅግ ፈጣን የሆነች…” ምናምን  ተብሎ ማብራሪያ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ‘ጥንቸል’ ምን ማለት እንደሆነ የማያውቅ መአት ሰው ሊኖር ይችላላ!
እኔ የምለው…ገንዘብ ‘የማጥራት’ ነገር ካነሳን አይቀር፣ በፊት እኮ የወዳጅ ኪስ በማራቆት፣ ችሎታቸው የክብር ምናምን ነገር ቢሰጣቸው የማይገርሙ ሰዎች ነበሩ:: እንበልና ‘ጉሮሮ ለማራስ’ የሆነ ቦታ አንድ ቢራ ይዛችሁ ተቀምጣችኋል… ቢራ ‘የሰፊው ህዝብ’ መጠጥ በነበረበት ዘመን:: የሆነ የምታውቁት ሰው ይመጣል፡፡ ትውውቃችሁ ይህን ያህል… “ቅዳሜ ለምን ዶሮ ማነቂያ ቁርጥ አንበላም፣” የሚያሰኝ አይነት አይደለም…ቁርጥ ለ‘ፋይፍ ስታር’ ሰዎች ብቻ ባልነበረበት ዘመን ለማለት ያህል ነው፡፡
ሰላምታ ትለዋወጡና አጠገባችሁ ‘ጉብ’ ይላል፡፡  “ብቻህን ነህ?” ወይም “ሰው እየጠበቅህ ነው አንዴ?” ብሎ ነገር የለም:: ወንበሩ የእሱ ስም አብሮ ተጽፎበት ‘ሪዘርቭድ’ የሚል ያስመስለዋል፡፡ እናላችሁ… ያው የተለመደና አሁን፣ አሁን መጋዘን ውስጥ ሊቆለፍበት የሚገባ ‘አራድነት’ አለ አይደል፣ “ጠፋህ፣ አትታይም…” ይላል፡፡ ይቺ “ጠፋህ” የምትል ቃል እኮ የሆነ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ነገር ያላት ናት፡፡
የእናንተ መልስ… “ምን እባክህ፣ ሥራ በዛ፣” ይሆናላ፡፡ “ሥራ በዛ፣” ማለት የሆነ ‘ትከሻ ሰፋ’ ማድረጊያ ነገር ነው፡፡ እናላችሁ… “አንተም ብዙ አትታይም፣” ካላችሁት… “ይበለኝ፣ በገዛ እጄ!” እንድትሉ ነው የሚያደርጋችሁ፡፡
ኑሮ እንዴት ከባድ እንደሆነ፣ ምቀኛ በዝቶበት አላስቆም፣ አላስቀመጥ እንዳሉት፣ የኮንዶሚኒየም እዳ የማያውቀውን በሽታ ሁሉ እንዳመጣበት…ምን አለፋችሁ ‘ቸግርና ሰቆቃ 101’ ኮርስ ይሰጣችኋል፡፡ “የሆነ ነገር ያዝ፣” እስክትሉት አይጠብቅም፡፡ “ማነህ አሳላፊ…” (አሳላፊው አጠገቡ ሆኖም ያጨበጭባል! ”ያላበው ቢራ አምጣልኝ፡፡”)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በሰው ፈራንክ ‘ራሳችንን የምንጋበዝ’ ሰዎች እኮ ትእዛዝ ስንሰጥ ልክ “የቪ.አይ.ፒ. ወንበር አምጡልኛ፣” ለማለት ምንም አይቀረን! አንድ ጊዜ “ያላበው ቢራ” ካልን በኋላ “ስማ በደንብ የቀዘቀዘ፣ ከዲፕ ፍሪዝ አውጥታችሁ…” ምናምን አይነት ድርደራ ምን የሚሉት ‘አሜንድመንት’ ነው! የምር ግን… በሆቴሎችና በመሳሰሉ መገልገያዎች ብዙዎቻችን ለየት ብለን ለመታየት ትአዛዝ ስንሰጥ “አንድ በየአይነቱ…” ለማለት ሁለት ገጽ ተኩል ይጨመርባትና ነገሩን የሆነ ‘ትረካ’ ነገር እናስመስለዋለን፡፡
እናላችሁ፣ ዓለም ሁሉ እሱ ላይ አንደተነሳበት እየነገራችሁ ያለው፣ ራሱን በእናንተ ኪስ የሚጋብዘው ሰው እኩል ሰዓት ሳይሞላ ሦስተኛው ቢራ ላይ ደርሷል:: እዚህ ላይ አሪፉ ነገር ምን መሰላችሁ… “ማነህ አሳላፊ ሂሳብ” ማለት፡፡ አለበለዛ ዝም ካላችሁት በኋላ ዋናው ‘ሂሳብ’ የመድሀኒት ይሆናል፡፡
እስከመቼ ድረስ በብር አባብዬ
ገንዘቤን ላጣራ ወደሽኛል ብዬ፣
ተብሎ ተዚሞ ነበር፡፡ ያን ጊዜ በሰላሳ ሳንቲም አሪፍ ኬክ ስለነበር፣ ብር ማባበያ ይሆን ነበር፡፡ አሁን ብር ‘ማባበያ’ ነው (ቂ…ቂ…ቂ…)፡፡ የምር እኮ፣ እኛ ዘንድ አይደለም ኪሳችን ሊገባ፣ በአጠገባችን አላልፍ ያለው ብር፣ ሌላው ዘንድ ሞልቶ ሲፈስ፣ ሆዳችን የማይባባሳ! በዛ ሰሞን ባንኮች የሚሰጡት ብር አጠራቸው ነው ምናምን የተባለ ጊዜ… “የት ሄዶ ነው፣ እኛ ዘንድ እንደሁ ጠብ ያለ ሳንቲም የለም፡፡” የገንዘቡ ጡንቻው ፈርጥሞ ‘የምንባባበት’ ሳይሆን፣ ኑሮን ‘እያባበልን’ የምናሸንፍበት ይሁንልናማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1757 times