Print this page
Saturday, 22 February 2020 10:02

የካቲት 12፤ ከብርሃን በፊት የነበረ ጨለማ

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

       “--የካቲት 12 እልቂቱ ከመጀመሩ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ አርባ ሺህ ጥቁር ለባሽ ፋሽስትና ሰላሳ አምስት ሺህ ሜትሮ ፖሊታንት (የከተማ ፖሊስ) የጣሊያን ሠራዊት ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሶስት ሺህ ሊቢያዊያንና አምስት ሺ ኤርትራዊያን፣ በድምሩ ሰማኒያ ሶስት ሺህ ጦር በከተማዋ ነበር፡፡- “
       
           ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የከፈቱት በሁለት ዋና ዋና ግንባሮች ነው:: አንደኛው ከአሥመራ፤ ሁለተኛው ከኢጣሊያ ሶማሌ ላንድ፡፡ ከፍተኛውን የጦር ኃይላቸውን ያሰለፉት ከኤርትራ ወደ መሐል አገር በሚያጠቃው የጦር ክፍላቸው ሲሆን፣ ይህን ያደረጉት ደግሞ በእነሱ የቅኝ ግዛት ሥር ይገኝ የነበረው የሐማሴን፣ የአካለ ጉዛይና ሌላውም ሕዝብ ለኢትዮጵያዊነቱ አድልቶ ከጠላት ጋር ይተባበርብናል፤ ድንገትም መንገድ ከፍቶ ከኋላ ሊያስወጋን ይችላል ብለው ስለሰጉ ነው፡፡ ከአሥመራ ሆነ ከሞቃድሾ የተነሳው የጣሊያን ጦር ፊት ለፊት በገጠመው የኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ያለ ኃይሉን አሟጦ መጠቀሙ የታወቀ ነው::
ከመሬት በታንክ፣ በመድፍና በመትረየስ፣ ከአየር መትረየስ በሚተኩሱና ቦምብ በሚጥሉ የመርዝ ጋዝ በሚያዘንቡ አይሮፕላኖች፣ አይናቸው እስከገባ እጃቸው እስከደረሰ ድረስ፣ ጣሊያኖች የኢትዮጵያን ጦር ጨፍጭፈዋል፤ እንደ ቅጠል አርግፈውታል፡፡
በቂ ስንቅና መሣሪያ ብቻ ሳይሆን ምንም ዓይነት ዘመናዊ ሥልጠና ያልነበረው የኢትዮጵያ ጦር፣ ከሞቱ በፊት የሀገሩን መደፈር ላለማየት በመወሰን፣ ጓደኛው ተመቶ ሲወድቅ የወንድሙን ሬሳ ተራምዶ ጠላት መሐል እየገባ በሰይፍና በጐራዴ ሳይቀር መራራ ፍልሚያ ተፋልሟል:: የነፃነት ፍቅሩና እራሱን ለመስዋዕትነት ማዘጋጀቱ፣ የጣሊያንን የመሣሪያ የበላይነት መክቶ፣ ሀገሩን በጠላት ከመደፈር ሊያድናት ግን አልቻለም፡፡
አዲስ አበባ መጋቢት 28/1928 ዓ.ም በኢጣልያ ጦር ተያዘች፡፡ አሥራ ሶስት ሺህ ጦር ይዞ አዲስ አበባ የገባው ጄነራል ቦዶሊዮ፤ በእዚያው እለት አንድ ሺህ አምስት መቶ ኢትዮጵያውያንን ገድሏል፡፡ ‹‹የተነሳነው ኢትዮጵያን ለማሰልጠን ነው›› እያሉ አስቀድመው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያካሂዱ የቆዩት ጣሊያኖች፤ በእርግጥ የመጡት አገር ለማሰልጠን ሳይሆን አገርን ቅኝ ግዛት ለማድረግ፣ ሕዝቡን ለማጥፋት መሆኑን በተግባር አሳዩ፡፡
በምሥራቅ፣ በደቡብና በሰሜን ግንባር ተሰልፎ የመከላከል ጦርነት ሲያደርግ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር አባላት ወደ ቀበሌያቸው ከተመለሱ በኋላ ብዙዎች በየአካባቢያቸው የራሳቸውን ቡድን እየፈጠሩ ወደ ነፃነት ትግሉ ተመለሱ:: ጣሊያኖችን የተቀመጡበት ወንበር ምቾት የማይሰጥ እንዲያውም የሚለበልብ አደረጉባቸው፡፡
በአዲስ አበባ ዙሪያ ከጣሊያን ጋር እየተዋጉ የነበሩ አርበኞች፣ ሐምሌ 28/1928 በሁሉም አቅጣጫ አጥቅተው አዲስ አበባን ለመያዝ እቅድ አወጡ፡፡ እቅዱ እንደታሰበው ባይሳካም ተሞከረ፡፡ ደጃዝማች ፍቅረ ማርያም አበበ የካ ሚካኤል ድረስ፣ ደጃዝማች ባልቻ እስከ አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ዘልቀው አጠቁ፡፡ ከጦሩ ጋር አብረው አዲስ አበባ የገቡት አቡነ ጴጥሮስ ተይዘው ተገደሉ፡፡
አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም፣ ከእነሱ ጋር የተባበሩት በርካታ ሰዎችመ የካቲት 12/1929 የጣሊያን ከፍተኛ መኮንኖችና መሪዎች ለማወስገድ ያደረጉት ሙከራ፣ ጨለማውን የመስበር - ለብርሃን መስመር የመክፈት ሙከራ በማለት መግለጥ ይችላል::
እነ አብርሃም ደቦጭ ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው፣ ግፈኛና ፋሽስት የጣሊያንን አመራሮች ገድለው ለመገላገል ሲነሱ፣ ሙከራቸው ባይሳካ ምን ሊያስከትል እንደሚችል፣ ሙከራቸው ቢሰምር ምን ውጤት እንደሚያመጣ ሳይገምቱ አይቀሩም:: ሙከራው ቢሳካ ኖሮ ጀኔራል ግራዚያኒና ሌሎችም የጦር መኮንኖች ቢሞቱ አዲስ አበባ ላይ ሥልጣን መያዝ የሚችል ኃይል ከጐናቸው እንዳልነበርም ይረዳሉ:: እነሱ ያንን በማድረግ ግን በዓለም ፊት ኢጣሊያ ተደላድላ አገር እየገዛች አለመሆኗን ከማስመስከራቸው በላይ በዱር በገደሉ ለተሰማራው አርበኛ የነፃነትና የተስፋ ብርሃን እንደፈነጠቀላት ያደርጋሉ፡፡ ይህን ከልብ ያሰበበት ይመስለኛል፡፡
ቢከሸፍ እነሱም ሆኑ ሌሎች የእለቱ እለት ወይም በሌላ ጊዜ ታድነው መያዛቸው፤ መገደላቸው እንደማይቀር እርግጠኞች ናቸው፡፡ ቀደመ ብሎም ጣሊያኖች የተማሩ ኢትዮጵያዊያን እያሰሱ እየገደሉ መሆናቸውን ደጋግመው ስላዩት፣ እነሱ አንድ ቀን ተረኛ መሆናቸው ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ስለዚህም ሞት ወይም አስራት የሚያስፈራቸውና የሚያስጨንቃቸው አልነበረም፡፡ እናም ወዲያ እና ወዲህ የማይል የማያወላውል ውሳኔ ላይ ደረሱ፤ ግራዝያኒንና ግብረ አበሮቹን ገድሎ የመጣውን መቀበል፡፡
ሁለቱም፤አብርሃም ደቦጭና ሞገስ አስገዶም በነፍሳቸው ቆርጠው በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ተከታታይ ጣሉ፡፡ ጀኔራል ግራዚያኒን ጨምሮ 30 የሚሆኑ ጣሊያኖች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አንድ ሰው ሞቷል:: ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከተረፉት ውስጥ የአዲስ አበባ ጳጳስ የነበሩት ካቶሊኩ አቡነ ኮርሊኒ ይገኙበታል፡፡ በሶስት ቀን ውስጥ አዲስ አበባ ላይ 30ሺህ ሰው፣ ደብረሊባኖስ ላይ 2500 መነኮሳት ሲጨፈጨፉ፣ ጳጳሱ አንድም ቃል ትንፍሽ አላሉም፡፡ “ኧረ በቃችሁ” ብለው ለመናገር እንኳ ያልተነሱ ሰው ናቸው፡፡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከጣሊያን ፋሺዝም ጐን ለመቆሟ ማሳያ ሆኖ ከሚጠቀሰው ተግባሯ አንዱ ይህ ነው፡፡
ከየካቲት 12/1929 በፊት የነበረችውን አዲስ አበባና የእለቱ እለት ጀምሮ በተከታታይ ለሶስት ቀን የሆነውን መለስ ብለን እንመልከት፡፡ ሐምሌ 28/1928 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዙሪያ የነበሩ አርበኞች ያደረጉት ሙከራ፣ ጣሊያኖችን የአዲስ አበባን ጥበቃ እንዲያጠናክሩ አድርጓቸዋል፡፡
የካቲት 12 እልቂቱ ከመጀመሩ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ አርባ ሺህ ጥቁር ለባሽ ፋሽስትና ሰላሳ አምስት ሺህ ሜትሮ ፖሊታንት  (የከተማ ፖሊስ) የጣሊያን ሠራዊት ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሶስት ሺህ ሊቢያዊያንና አምስት ሺ ኤርትራዊያን፣ በድምሩ ሰማኒያ ሶስት ሺህ ጦር በከተማዋ ነበር፡፡
“ያለ ርህራሄ ያገኛችሁትን ሁሉ ግደሉ” የሚል ትዕዛዝ የተላለፈው ለዚህ ሁሉ ሠራዊት ነው፡፡ ግድያ ላይ ያልተሠማራው ካምፕና ቢሮ የሚጠብቀው ብቻ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡
አንዱ “ምላጭ የሳብኩበት እጄ ዛለ”፤ ሌላው “ሁለት ብቻ ነው የገደልኩት” ብሎ ሲቆጨው እናገኛለን፡፡ ደግሞ ሌላው “በአንድ ትንሽዬ ጣሳ ቤንዚን፣ እስር ቤት አቃጠልኩ” እያለ ይፎከራል፡፡ መንገዱ በሙሉ በሬሳ ተሸፍኖ ታይቷል፡፡ በዚህ ሁኔታ አዲስ አበባ በሶስት ቀን ውስጥ የተጨፈጨፈው ሰው ሰላሳ ሺህ ነው ብሎ ማለት የምር ቀልድ አይሆንም?
የካቲት 12/1954 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ይህን ቁጥር ወደ ሰማንያ ሺህ አሳድጐ መግለጡን አስታውሳለሁ፡፡ እኔም የምስማማው በዚህ ነው፡፡
ጣሊያኖች የካቲት 12 ለተከታታይ ሶስት ቀን ያካሄዱት ግድያ መደፈር፣ የቀሰቀሰው የግንፍልነት በቀል አይደለም:: አጋጣሚውን በመጠቀም የተካሄደ የዘር ማጥፋት እርምጃ ለመሆኑ ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ቦንቡን የወረወረው አንድ እንግሊዛዊ ወይም ስዊድናዊ ወዘተ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ይሠራ ነበር? ብዬ እራሴን ስጠይቅ የማገኘው መልስ፣ ዘር ለማጥፋት መነሳታቸውን የሚያጠናክር ነው የሚሆንብኝ፡፡
ከእነ ቤታቸው የነደዱት፣ በአካፋና በዶማ ሳይቀር የተገደሉት ኢትዮጵያዊያን ሞት፣ ተራ ሞት አልነበረም፡፡ የአርበኞችን ትግል ለማጠናከር ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሯል፡፡ ሁኔታውን ከብርሃን በፊት የነበረ ጨለማ ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡
ክብር ለሰማዕታት!

Read 1916 times