Print this page
Saturday, 22 February 2020 10:06

“ቁማር”ን ለማቆንጀት መጃጃል በዛ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

      • አዳዲስ የቁማር ድርጅቶች፣ የስራ ፈቃድ እንዳያገኙ ተከልክለዋል - በመንግስት ውሳኔ
            • ነባር የቁማር ድርጅቶች አለፈላቸው፡፡ በብዙ ሙስና የማይገኝ ውሳኔ ሆነላቸው
                     
           “የስፖርት ውርርድ፣ ቁማር ነው ብለን አናምንም” ብለዋል - የብሔራዊ ሎተሪ ባለስልጣን፡፡
የስፖርት ቁማር ለማካሄድ የተቋቋሙትን ድርጅቶች፣ “አቁማሪ” አንላቸውም ሲሉም ተናግረዋል - እኚሁ ኃላፊ፡፡ እህሳ?
“የስፖርት ውርርድ አወራራጅ ድርጅቶች ብለን ነው የምንጠራቸው” ሲሉ የብሔራዊ ሎተሪ ቃል አቀባይ አስረድተዋል፡፡
ወይም ደግሞ “የስፖርት ውርርድ አጫዋቾች” የሚል ስያሜ ሌላ አማራጭ መጠሪያ ነው፡፡
“አጫዋች” ስለሆኑ፤ “ከትርፍ ይልቅ ጨዋታው ላይ” እንዲያተኩሩ አድርገናል በማለት የተናገሩት እኚሁ የብሔራዊ ሎተሪ ባለስልጣን፣ ነገርዬው ቁማር እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡
አንድ የቁማር ድርጅት ኃላፊ በፊናቸው፣ ለቢቢሲ በሰጡት ማብራሪያ፣ የስፖርት ውርርድ፣ የወጣቶችን እውቀት እንደሚያሰፋ ተናግረዋል፡፡ በስፖርት ውርርድ አማካኝነት፣ በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱንም ሲያስረዱም፣ “ከሚታሰበው በላይ የስፖርት እውቀታቸው ጨምሯል” ብለዋል፡፡
እንዴት?
ወጣቶች ገንዘባቸውን ለውርርድ ከመክፈላቸው በፊት፣ ሬዲዮ ያዳምጣሉ፣ ኢንተርኔትን ያያሉ፡፡ እናም፤ “መረጃ ቶሎ ቶሎ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል” በማለት፣ የስፖርት ቁማር ለወጣቶች የሚያስገኘውን ጥቅም ገልፀዋል፡፡ ማን? የቁማር ድርጅት ባለቤት፡፡
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ተወካይም፣ የስፖርት ውርርድ “ማህበራዊ ፋይዳ” ስላለው፣ ቁማር አይደለም ሲሉ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
“ማህበረሰቡ፣ በተለይም ወጣቶች፣ ጊዜያቸውን በሌሎች ነገሮች ከሚያሳልፉ፣ እየተዝናኑ እድላቸውን የሚሞክሩበት ነው” ብለዋል - እኚሁ ባለስልጣን፡፡
ቅሬታዎችና ተቃውሞች ሲቀርቡም፣ “የስፖርት ውርርድ፣” ለኢትዮጵያ ህዝብ ያመጣንለት አዲስ የመዝናኛ ቴክኖሎጂ ነው” በማለት ብሔራዊ ሎተሪ ምላሽ እንደሰጠ ተዘግቧል፡፡
በአጠቃላይ፤ ቁማር፣ ቆንጅዬ ነገር እንደሆነ እየነገሩን ነው፡፡ እንዲያውም፤ ቁማር ብለን እንዳንጠራው ይመክሩናል፡፡ ነገርዬው፣ ውርርድ እና ጨዋታ እንጂ ቁማር አይደለም፡፡
ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ባይ ናቸው:: የወጣቶችን እውቀት ያሰፋል፡፡ በመረጃም ያበለጽጋል ተብሎለታል፡፡
ትርፍ ላይ ሳይሆን ጨዋታ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ምን? የስፖርት ቁማር፡፡
ለብሔራዊ ሎተሪ አኩሪ ስራ ሆኗል፡፡ ለምን?
የስፖርት ቁማር፣
ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ውለታ ነው - በአዲስ የመዝናኛ ቴክኖሎጂ ጋር የመተዋወቅ እድል ሰጠነው…
ለወጣቶችም ትልቅ እፎይታ ነው፤ የሌሎች ነገሮችን ትተው የሚዝናኑበትና ሽልማት የመብላት እድል ፈጥረንላቸዋል…
ቁማርን ለማቆንጀት የሚቀርበው ሰበብ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ብሔራዊ ሎተሪ እንደገለፀው፤ በስፖርት ቁማር በኩል፤ ብዙ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ ይሆናል:: መንግስት፣ “ኮሚሽን ይቀበላል፡፡ ቫት ያስከፍላል፡፡ የትርፍ ግብር ይቆርጣል፡፡ “የቁማር ድርጅቶች” “ይቅርታ፤ “የውርርድ አጫዋቾች” ለበጐ አድራጐት እርዳታ ይሰጣሉ በማለትም ብሔራዊ ሎተሪ ገልጿል፡፡
መንግስት፣ በቁማር ድርጅቶች በኩል በዓመት፣ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አግኝቷል፡፡ ከኮሚሽን ብቻ 20 ሚሊዮን ብር ተቀብሏል፡፡
ጥያቄው ምንድነው? ይሄ ሁሉ ብር ከየት የመጣ ገንዘብ ነው? ከዜጐች፣ በተለይም ከወጣቶች ኪስ የወጣ ብር ነው፡፡
ለስፖርት ቁማር በዓመት 140 ሚሊዮን ብር ገደማ ከዜጐች ኪስ ወጥቷል፡፡ ግማሹ ወደ መንግስት ይገባል፡፡ 10% ያህል ለውክልና (ወይም፣ ለቦታ ኪራይና፣ ለስራ ማስኬጃዎች)፣ ለማስታወቂያ፣ ለቁሳቁስና ለሌሎች የሚውል ገንዘብም አለ፡፡
በተለመደው አሰራር ከሆነ፣ እስከ 10% የሚደርስ ገቢ፣ የቁማር ድርጅቶች ትርፍ ይሆናል፡፡ 10% ያህል ደግሞ ለቁማር ተጫዋቾች የሚደርስ ሽልማት፡፡
በአጭሩ፣ ቁማር ተጫዋቾች፣ 140 ሚሊዮን ብር ይከፍላሉ፡፡ “አሸናፊዎች” ወይም “እድለኞች” 15 ሚሊዮን ብር “ይሸለማሉ”፡፡ “እድለ ቢሶቹ” 125 ሚሊዮን ብር ይከስራሉ - በዓመት፡፡
ከዚህ የደንበኞች ኪሳራ ውስጥ የሚገኝ ነው የቁማር ድርጅቶች ገቢ፡፡ ደንበኞች እንጂ የቁማር ድርጅቶች መቼም ቢሆን አይሸነፉም፡፡ ይሄ የቁማር ቤት ባሕርይ ነው:: “The house always wins” ከሚለው ቁጥር አንድ የቁማር አባባል ጋር፣ በእውን የምንተዋወቅበት አጋጣሚ ተሰጠን ማለት ይቻላል፡፡
የቁማር ቤቶች ዋና ባህርይ ምን እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ በአንድ በኩል፣ የቁማር ክፍል፣ ወንበርና ጠረጴዛ፣ የቁማር ካርድና ዘበኛ በማቅረብ፣ የቁማር ደንበኞችን የሚያስተናግዱ ቤቶች ይኖራሉ፡፡ ደንበኞች እርስበርስ ይወራረዳሉ፡፡ ቁማር ቤቶች ደግሞ፣ የደንበኝነት ክፍያ፣ አልያም ከቁማር አሸናፊ ኮሚሽን ይቀበላሉ፡፡
አብዛኛው የቁማር ስራ ግን ከዚህ ይለያል:: የቁማር ደንበኞች፣ ከቁማር ድርጅቶች ጋር ነው የሚወራረዱት፡፡ ከቁማር ቤቶች ጋር ነው የሚቋመሩት፡፡ የስፖርት ቁማር እንደዚህ ነው፡፡ የቁማር ደንበኞች እርስ በርስ አይወራረዱም፡፡ ከቁማር ድርጅት ጋር ነው - ውርርዱ፡፡
የቁማር ድርጅቶች፤ አቋማሪ፣ አወራራጅ፣ አጫዋች የሚል ስያሜ ከተሰጣቸውም፣ ‹‹አዋዳጅ››፣ ወይም ‹‹አናካሽ›› በሚል አይነት ትርጉም ሊሆን አይችልም፡፡ ከዳር ሆኖ፣ ደንበኞችን የሚያዋድድ ወይም የሚያናክስ አይደለም - የቁማር ድርጅት፡፡
በደንበኞች ሂሳብ አብሮ እንደ የሚጠጣ የመጠጥ ቤት ባለቤት ናቸው - ቁማር ቤቶች፡። የደንበኞች ‹‹አጣጭ›› እንደማለት፡፡ ‹‹አጫራሽ›› የሚሉም ይኖራሉ፡። ግን ሁሌም፣ በደንበኞች ኪሳራ ነው አጣጪነቱ፡፡ የቁማር ቤቶች አቋማሪነት፣ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሁሌም በቁማር ደንበኞች ኪሳራ፣ ትርፍ ያገኛል፡፡ ‹‹ለመብላት›› ከሚመጡ ደንበኞች ላይ ትርፍ መብላት የሚችል ነው - የቁማር ቤት፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የቁማር ቤት ሁሌም አሸናፊ ነው፡፡
በዓመት ከደንበኞቹ 140 ሚሊዮን ብር ይቀበላል፡፡  ለጥቂት ዕድለኞች 15 ሚሊዮን ብር ይሸልማል፡፡ የብዙዎቹ ደንበኞች ገንዘብ ቀልጦ ይቀራል፡፡ ይሄ ቁማር ካልሆነ፣ ቁማር ምንድነው?
በአሜሪካም ሆነ በእንግሊዝ፣ የስፖርት ውርርድ ከቁማር አይነቶች አንዱ ነው ተብሎ እንደሚዘረዘር ይታወቃል፡፡ ከበርካታ የ‹‹gambling›› አይነቶች አንዱ ነው፡፡ ታዲያ፣ “ቁማር ሳይሆን የመዝናኛ ውርርድ ነው” ምና ምን እያሉ በከንቱ ለማቆንጀት መጃጃል ምንድነው? ለቁማር ድርጅቶች ጥብቅና የመቆም ትክክለኛው መንገድ፣ የመጃጃልና የሽንገላ መንገድ አይደለም፡፡ ቁማር፣ በመሰረቱ መጥፎ መሆኑን ለመካድና ለማስካድ መሞከር፣ ከቁማር የባሰ ጥፋት ነው፡፡
ይልቅስ፣ የቁማር ንግድ መካሄድ ካለበት፣ ህፃናትን ለማታለል እስካልሞከረ ድረስ፣ ሰዎችን ከመንገድ ጎትቶ ‹‹ቁማር ተጫወቱ›› ብሎ እስካላስገደደ ድረስ፣ ቁማር ቤት መክፈት… መብት ነው… የሚል ሀሳብ ማቅረብ ይቻላል፡፡
አሁን እያየን ያለነው ግን፣ ቁማርን የማቆንጀት ሙከራ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ቅሬታና ተቃውሞ የቀረበባቸው የቁማር ድርጅቶች፣ ያለ ተወዳዳሪ በብቸኝነት የመስራት ልዩ የከለላ እድል እየተሰጣቸው ነው፡፡
ለአዳዲስ ድርጅቶች ፈቃድ እንዳይሰጥ ታግዷል፡፡ ቅሬታ የቀረበባቸው ነባር የቁማር ድርጅቶች አለፈላቸው፡፡ እንዲህ አይነት ውሳኔ፣ በብዙ ጉቦ የማይገኝ አስደሳች ውሳኔ ይሆንላቸዋል፡፡  

Read 2660 times