Saturday, 22 February 2020 10:27

ኦነግ በምርጫ ዋዜማ እስራትና ወከባ እየተፈፀመብኝ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

      ኦነግ በሰባት የኦሮሚያ ዞኖችና በ26 ወረዳዎች ውስጥ 350 ያህል አባላቶችና ደጋፊዎቹ እንደታሰሩበት ያስታወቀ ሲሆን በምርጫ ዋዜማ የጅምላ እስራትና ወከባ እየተፈፀመ መሆኑ ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ሽግግር መልካም አይሆንም ብሏል፡፡
የ ጅምላ እስራት፣ የሲቪል ሰዎች ግድያ፣ ሕዝብን ለይቶ የብዙሃን መገኛና አገልግሎትን ማቋረጥ፣ ተማሪዎችን ለይቶ ከዩኒቨርሲቲ ማባረር፣ ወታደራዊ አስተዳደር (ኮማንድ ፖስት)… በኦሮሚያ ክልል እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ናቸው ያለው ኦነግ፤ ድርጊቶቹ በምርጫ ዋዜማ እየተፈፀሙ ያሉ የአፈና ተግባር ናቸው ብሏል፡፡
ኦነግ በኮማንድ ፖስት ስር ናቸው ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምስራቅ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና፣ ቡኖ በደሌና ኢሉ አባቦራ ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀም አመት አልፎታል ብሏል - የኦነግ መግለጫ፡፡
የጅምላ እስራት ተፈፅሞባቸዋል ተብለው በመግለጫው ከተጠቀሱት መካከልም የፊኒፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ተጠቃሽ ሲሆን በዚህ ዞን ስር በሚገኙት ሰበታና ቡራዩ ብቻ ከ200 በላይ ሰዎች ታስረዋል ሲል ስም ዝርዝራቸውንም በመግለጫው አካትቷል፡፡
የጅምላ እስራት ተፈፅሞባቸዋል የተባሉ ሌሎች ዞኖች ማለትም ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ኢሉ አባቦራ፣ መቱ፣ ሮቤ፣ ዶሎ መኖ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ ኦዳ ቡልቱም፣ ኤጄሬ፣ ጀልጁ፣ አደአ በርጋ፣ ጊንጪ፣ አምቦ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ጽ/ቤቶቹ እየተዘጉበትና በአባላትና ደጋፊዎቹ ላይ በተለያየ መንገድ ወከባ እየደረሰ መሆኑን ኦነግ ጠቁሟል፡፡
ቀደም ባለው ሳምንት የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባወጣው መግለጫ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ የሕግ ጥሰት ሲፈጽሙ የቆዩ ግለሰቦችን ከያሉበት እየያዘ እያቀረበ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡  

Read 11664 times