Saturday, 22 February 2020 10:29

የጠ/ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፎች አሁንም ህዝባዊ ድጋፍ እንዳላቸው አመላካች ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

   በኦሮሚያ የተለያዩ ዞኖች ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይና አመራራቸውን በመደገፍ ሠላማዊ ሠልፎች ሲደረጉ የሰነበቱ ሲሆን ሰልፎቹ ጠ/ሚኒስትሩ አሁንም ከፍተኛ የድጋፍ መሠረት እንዳላቸው አመላካች ነው ሲሉ ይህንን አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ አጋርተዋል፡፡
ቀደም ባለው ሳምንት ጠ/ሚኒስትሩንና አመራራቸውን የሚደግፍ ሠልፍ በትውልድ አካባቢያቸው ጅማ መካሄዱን ተከትሎ ወደሌሎች አካባቢዎችም የተዛመተው የድጋፍ ሠልፉ በጅግጅጋ፣ በባሌ ጐባ፣ ኢሉባቦር፣ ሻሸመኔ፣ አሠላ፣ ለገጣፎ፣ ጋምቤላ፣ ሃዋሳ፣ ቢሾፍቱ፣ ሰንዳፋ፣ ጉጂ፣ ሱሉልታ፣ አፋር፣ ሰሜን ሸዋ ፊቼ እና በሌሎች አካባቢዎች ሲካሄድ ሰንብቷል፡፡
በእነዚህ የድጋፍ ሰልፎች ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ ግራፎች ያሉባቸው ባነሮች በብዛት የትዕይንቱ አካል የነበሩ ሲሆን ‹‹ከዶ/ር ዐቢይ ጋር መጪው ጊዜ ብሩህ ነው፣ ከዶ/ር ዐቢይ ጋር በመሆን ለውጡን ከዳር እናደርሳለን የሚሉት መፈክሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡  
በለገጣፎ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በበኩላቸው ዶ/ር ዐቢይ በዘመናት መካከል የተገኘ ድንቅ መሪ ነው፤ የፈጣሪ ስጦታ ነው ሲሉ ህዝቡ ድጋፍ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
እነዚህ የድጋፍ ሰልፎች ምን አንድምታ አላቸው?ለምን በዚህን ወቅት ተከሰቱ? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ምሁራንና አክቲቪስቶች በበኩላቸው የድጋፍ ሠልፎቹ በባህሪያቸው ቀደም ብሎ በአቶ ጃዋር ፊት አውራሪነት ለተመራውና በርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎችን ላዳረሰው ህዝባዊ የስብሰባ ትዕይንት የመልስ ምት አይነት ናቸው ብለዋል፡፡
“የድጋፍ ሠልፉ ትዕይንት የፖለቲካ ሚዛን መለካኪያ ነው” የሚለው መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ ቀደም ብሎ በአቶ ጃዋርና በኦፌኮ ሲካሄድ ለነበረው እንቅስቃሴም የመልስ ምት ነው” ይላል፡፡
በዚህ እንቅስቃሴም ጠ/ሚኒስትሩ አሁንም በተለይ በኦሮሚያ ሠፊ የድጋፍ መሠረት እንዳላቸው ጠቋሚ ነው” ያለው ስዩም በመጀመሪያ ጨዋታውን ለጀመሩት ለእነ አቶ ጃዋርም መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው ብሏል፡፡ የተለመደውን ስሜት ቀስቃሽ የፖለቲካ አካሄድም ትዕይንቱ የሚያቀዘቅዘው እንደሚሆን መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ አስረድቷል፡፡
“ጉዳዩ የድጋፍ መሠረት ፉክክር አይነት ነው” የሚሉት ፖለቲከኛ እና ጦማሪ አብዱራህማን አህመዲን በበኩላቸው ለዚህ ትዕይንት መነሻውም የእነ አቶ ጃዋርና የኦፌኮ እንቅስቃሴ መሆኑን፣ ጉዳዩም የጉልበት መፈታተሽ አይነት እንደሆነ አቶ አብዱራህማን ያስረዳሉ፡፡
“ጤናማ የጉልበት መፈታተሽ ከሆነና ህዝብን መከታ ወደ ማድረጉ መሄድ ተገቢ ሊሆን ይችላል” ያሉት አቶ አብዱራህማን “ነገር ግን ጉዳዩን ፍልሚያ ካደረጉት ከጥቅሙ አደጋው ያመዝናል” ባይ ናቸው፡፡
በተለይ ሀገሪቱ ካለችበት ያልተረጋጋ የለውጥ ሂደት አንፃር እንዲህ ያሉ መሳሳቦች ከጠቃሚነታቸው ይልቅ ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ያስረዱት አቶ አብዱራህማን የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብር ሳይጀመር እንዲህ አይነት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጐራዎችን የመፍጠር ችግር ያመጣል ባይ ናቸው፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፍ በሚል የሚደረጉት ሰልፎች አሁንም ለጠ/ሚኒስትሩ ያለው ህዝባዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉንና አለመሟጠጡን ያመላክታል ያሉት አቶ አብዱራህማን ይህ የድጋፍ ሠልፍ ግን የምርጫውን ውጤት የሚጠቁም ወይም የሚወስን አይደለም ባይ ናቸው፡፡
በምርጫ ወቅት የህዝቡ መንፈስ የሚለወጥበት ሁኔታ እንደሚኖር ምርጫ 97ን ምሣሌ ጠቅሰው ያስረዱት አቶ አብዱራሂም ለጠ/ሚኒስትሩም ሆነ ለእነ አቶ ጃዋር የሚደረጉት ትዕይንቶች የምርጫን ሁኔታ አያመላክትም ከምርጫው ጋርም መያያዝ የለበትም ባይ ናቸው፡፡
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚደረጉ ሠልፎች ባሻገር ጠ/ሚኒስትሩ ከሰሞኑ በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ከህዝብ ጋር በአደባባይ ስብሰባ የተገናኙ ሲሆን፤ በቀጣይ ምን ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመንቀሳቀስ እቅድ እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 11823 times