Saturday, 22 February 2020 10:41

ኦፌኮ የአቶ ጀዋርን ኢትዮጵያዊነት የሚያረጋግጥ ሠርተፊኬት ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

  ኦፌኮ በ10 ቀናት ውስጥ የአቶ ጀዋር መሐመድን ኢትዮጵያዊነት የሚያረጋግጥ ሠርተፊኬት እንዲያቀርብ ለመጨረሻ ጊዜ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጠየቀ ሲሆን ፓርቲው በበኩሉ፤ ሠርተፊኬት ለማቅረብ በህጉ አልገደድም ብሏል፡፡
ቀደም ብሎ ኦፌኮ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቶ ጀዋር የነበራቸውን የሌላ ሀገር ዜግነት መተዋቸውን፣ ሀገራቸው ተመልሰው እየኖሩ መሆኑን እንዲሁም የዚህ ሀገር ዜግነት እንዲሰጣቸው ማመልከታቸውን በመጥቀስ ምላሽ የሰጠ ሲሆን “በህጉ መሠረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዲሰጣቸው ማመልከት እንጂ ሠርተፊኬት መያዝ አይጠበቅባቸውም” የሚል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
በዚህ የኦፌኮ ምላሽ ላይ ተጨማሪ ህጋዊ ማብራሪያ እንዲሰጠው ወደ ኢምግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ደብዳቤ የፃፈው ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፤ ከመስሪያ ቤቱ ኦፌኮ ያቀረቧቸው መከራከሪያዎች እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያረጋግጥ ሠርተፊኬት መያዝ ይጠበቅባቸዋል ሲል ምላሽ መስጠቱን ቦርዱ አስታውቋል፡፡
በዚህ መሠረት ቦርዱ ለ3ኛ ጊዜ ኦፌኮ የአቶ ጀዋርን ኢትዮጵያዊነት በሰነድ በተደገፈ ማስረጃ በ10 ቀናት ውስጥ እንዲያረጋግጥለት ደብዳቤ ጽፏል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለአሜሪካ ድምጽ ምላሽ የሰጡት የፓርቲው ሊቀመንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ “እኔ በአማርኛም በእንግሊዝኛም ህጉን አንብቤዋለሁ ሠርተፊኬት አቅርብ የሚል የለም” ሲሉ ፓርቲያቸው ሠርተፊኬት ለማቅረብ በህጉ እንደማይገደድ አስታውቀዋል፡፡   

Read 13173 times