Saturday, 22 February 2020 10:45

‹ሐይለ ጊዜ›› አዲስ የሙዚቃ አልበም ለአድማጭ ሊቀርብ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   በወጣቶቹ የሙዚቃ ባለሙያዎች የተመሰረተውና ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን በጠበቀ መልኩ በባህላዊ ሙዚቃ ታጅቦ ሥራዎቹን ሲሰራ የቆየው መሶብ ባህላዊ ባንድ የሰራው ‹‹ሀይለ ጊዜ›› የተሰኘና በባህላዊ ሙዚቃ የተቀነባበረ የሙዚቃ አልበም ለአድማጭ ሊቀርብ ነው፡፡ አልበሙ 10 ዘፈኖችን የያዘ ሲሆን አብዛኛው ‹‹አንዲር›› ለተሰኘው የሙዚቃ ኮንሰርት ለሚቀርበው መሰናዶ የተሰሩና ‹‹ኧረ አምሳለ›› ለተሰኘው ለገጣሚ ምልዕቲ ኪሮስ የግጥም ሲዲ ከተሰራው ሶስት ሙዚቃ የተውጣጣ መሆኑን የሞሶብ ባህላዊ ባንድ ዋና መስራችና የዋሽንት ተጫዋች ጣሰው ወንድም ገልጿል፡፡
አልበሙ ሰሞኑን ለአድማጭ እንደሚቀርብም ሀሙስ ረፋድ ላይ በሀገር ፍቅር ቴአትር ትንሹ አዳራሽ የባህል ቡድኑ በጋራ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቋል፡፡
ባህላዊ ባንዱ በአገር ውስጥ በተለያዩ ትልልቅ ፕሮግራሞች፣ በኤምባሲዎች፣ በኪነ ጥበብ ምሽቶች በሆቴልና በተለያዩ ተቋማት ምረቃቶች እየተጋበዘ ጣዕም ያላቸው ሙዚቃዎችን በማቅረብ ዝግጅቶችን የሚያደምቅና እውቅናን ያተረፈ ሲሆን በተለያዩ የዓለም አገራት እየተዘዋወረ ስራዎቹን ከማቅረብም በተጨማሪ ‹‹አንዲር›› በተሰኘውና በየወሩ በሚያዘጋጀው የዋሽንትና ኮንሰርትና ‹‹ጥሞና›› በተሰኘው የመጀመሪያ አልበሙ ይበልጥ የሚታወቀ ሲሆን ሰሞኑን ለአድማጭ የሚቀርበው ‹‹ሀይለ ጊዜ›› ሁለተኛ የአልበም ስራቸው ነው፡፡

Read 892 times