Saturday, 22 February 2020 10:51

‹‹ክብረ አድዋ›› የአድዋ ፌስቲቫል ሰኞ ይከፈታል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

     በሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት በየአመቱ የሚሰናዳውና፡፡ ‹‹አድዋ የሰውነት ማህተም›› በሚል መርህ የሚዘጋጀው ‹‹ክብረ አድዋ›› ፌስቲቫል አራተኛው ዙር ሰኞ የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ በብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ አዳራሽ በድምቀት ይከፈታል፡፡
እስከ የካቲት 23 ቀን ለአንድ ሳምንት የሚዘልቀው ፌስቲቫሉ በዋናነት አራት ሁነቶች የሚካሄዱበት ሲሆን ከእነዚህም ሁነቶች መካከል ‹‹አድዋ የፊልምና የቴሌቪዥን ፌስቲቫል፣ ከተለያየ ሙያ የሚመጡና በሙያቸው አንቱ የተባሉ ሊህቃን የሚወያዩበት ‹‹የሊቃውንት ጉባኤ››፣ ክውን ጥበባት (የቴአትርና የባዶ እግር ጉዞ) እና የእንጦጦ ቤተ መንግሥት የግብር ምገባ ዝግጅት ይከናወኑበታል፡፡
በፊልም ፌስቲቫሉ አድዋን የሚዘክሩና አስተሳሰብን የሚቀይሩ ፊልሞች በአዶት ሲኒማ፣ የሊቃውንት ጉባኤው በወመዘክር የዋዜማ የሙሉ ሰዓት ቴአትሩ በብሄራዊ ቴአትር እሁድ የካቲት 22 ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን በቴአትሩ ላይ አንጋፋ ተዋንያን መሳተፋቸውን የሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይመንት ዋና ስራ አስኪያጅ አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን ገልጾ ቴአትሩ በራሱ፣ በመዓዛ ታከለና በምንተስኖት ተፅፎ በሚካኤል ሚሊየን መዘጋጀቱም ታውቋል፡፡
በተለይ በአድዋ ድል በዋናው ቀን ማለትም የካቲት 23ቀን የባዶ እግር ጉዞው በዛ ዘመን አለባበስ እና አጋጌጥ በታጀቡ ሰዎች ከምንሊክ አደባባይ በቴዎድሮስ አደባባይ አድርጎ እስከ አድዋ ድልድይ የሚደረግ የመንገድ ላይ ትርኢት የሚከናወን ሲሆን በዕለቱ ከ7-11 ሰዓት በእንጦጦው የምኒሊክ ቤተ መንግሥት የግብር ማብላት ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡

Read 4014 times