Saturday, 22 February 2020 09:59

ዓጼ ምኒልክ - ታላቁ ጥቁር

Written by  በታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(2 votes)

       የመጽሐፉ ርእስ - ታላቁ ጥቁር  ኢትዮ-አሜሪካ  ዘዳግማዊ ምኒልክ
ደራሲ:- ንጉሤ አየለ ተካ
የገጽ ብዛት:- 474
የመጽሐፉ ዋጋ:- 225 ብር-
ኅትመት፡- ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት፤ አዲስ አበባ

ተወዳጁና ዝነኛው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ‘ምኒልክ ጥቁር ሰው’ በሚል የሠራው ድንቅ ሙዚቃ በእውነተኞቹ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሠርፆ ለምንጊዚም ሲታወስ ይኖራል፡፡ ደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ ደግሞ  ‘ታላቁ ጥቁር  ኢትዮ-አሜሪካ  ዘዳግማዊ ምኒልክ’ የሚለውን መጽሐፍ  አዘጋጅቶ እነሆ ብሎናል፡፡ መጽሐፉ እጄ ላይ ገብቶ ያነበብኩት በተለየ ስሜት ነው፡፡ በእኔ አረዳድ፤ ዳግማዊ  ዓፄ ምኒልክ በዘመናቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ያደረጉት ከጀርመን፤ ከኢጣሊያ፤ ከእንግሊዝ፤ ከፈረንሳይና ከመስኮብ ጋር እንጂ ከአሜሪካ ጋር እንደዚህ ስፋት ያለው ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እንደነበራቸው የሚገልጽ መጽሐፍ አንብቤ አላውቅም፡፡ እንደ መጽሐፉ ገለፃ፤ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መኻከል የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተመሠረተው በአሜሪካዊው ፕሬዚደንት ቴዎዶር ሩዝቬልትና በኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ  ዓፄ ምኒልክ ዘመን ነበር፡፡  
ለካስ የምኒልክ ዱካና ሥራቸው  ያልደረሰበት ሀገር የለም፡፡ በዚያ የግንኙነት አውታሮች ውሱን በሆኑበት ዘመን፣ ዝናቸውና ፈለገ መንግሥታቸው፤ በኢጣሊያ ላይ የተቀዳጁት ድልና አስተዋይነታቸው ከአፍሪካ አልፎ አሜሪካ ድረስ ዘልቆ ነበር፡፡ በመሆኑም የምኒልክ ጉዳይ አሜሪካ ውስጥ በነበሩት በእነ ዶክተር መላኩ ባያንና ሌሎች ሰዎች አማካኝነት፣ በዓለም ጋዜጦች ተዘግቦና በስፋት ተዋውቆ  ነበር ይለናል - ደራሲው፡፡  
ደራሲ ንጉሤ አየለ ተካ፤ በድርሰቱ ዓለም ከተሰማራ ብዙ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ ከዚህ ቀደምም “ሐኖስ፤ ጣዝማ” (በደራስያን ሕይወት ላይ ያተኮረ)፤”ፍካት” (ግጥሞችና ወጎች በጋራ የተሠራ)፤ “ዐራተኛው መልስ” (በተለይ ለሕጻናት የተዘጋጀ)፤ ”የገራዶ ዋሽንት” (ሥነ ግጥም) የሚሉ ሥራዎቹን ለንባብ አብቅቷል፡፡ በቅርቡ ደግሞ “ታላቁ ጥቁር  ኢትዮ- አሜሪካ  ዘዳግማዊ ምኒልክ” በሚል ርእስ ያሳተመውን አዲስ መጽሐፍ ለአንባቢያን ማድረሱ ታላቅ ተመራማሪ፤ ሀገሩንና ወገኑን አፍቃሪና አክባሪ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ለምን ቢሉ -- የመጽሐፍ ሥራ የሚያስገኘው፣ የመንፈስ እርካታ እንጂ ትርፍና የገንዘብ ጥቅም የሌለው በመሆኑ ነው፡፡
መጽሐፉ፤ ከሚታወቀው ወደ ማይታወቀው  የሀገር ታሪክ የሚያሸጋግርና በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የኢትዮ-አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበር የሚተርክ ነው፡፡ የመጽሐፉ ዝግጅት ከ12 ዓመታት በላይ እንደፈጀና የጥናትና ምርምር ሥራ እንደሆነ ደራሲው ያስረዳል፡፡ ጥሩ አንባቢ ያልሆነ ሰው ከመጽሐፉ ባሕር ውስጥ ገብቶና ዋኝቶ በቀላሉ  ለመውጣት አይችልም፡፡ ለ“ፌስ ቡክ አርበኞችም” አይመችም፡፡ ሥራው በሁለቱ አገሮች ረገድ ከተጻፉት መጻሕፍት የመጀመሪያው እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ መጽሐፉ 474 ገጽ ያለው ሲሆን መጠኑም ከፍተኛ ነው፡፡ ከመጽሐፉ የኅትመት ጥራትና የገጽ ብዛት፤ ከያዘው መሠረታዊ ቁም ነገር አንጻር ሲታይ፣ ዋጋው አነስተኛ ነው፡፡ ዛሬ 100 ገጽ የማትሞላና  የውሻ ምላስ የምታህል መጽሐፍ ከ100 - 150 ብር ስታወጣ፣ የዚህ ትልቅ የምርምር መጽሐፍ ዋጋ 225 ብር ብቻ መሆኑ የደራሲውን ሚዛናዊነት ያመለክታል::
የመጽሐፉ ደራሲ ኢትዮጵያ ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምራ ከአሜሪካ ጋር የነበራት የወዳጅነትና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ምን እንደሚመስል የጻፈልን በአሜሪካ ልዩ ልዩ መዚየሞችና አብያተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙና ስለ ኢትዮጵያ የሚያስረዱ መጻሕፍትን፤ ጋዜጦችን፤ ልዩ ልዩ የፕሮቶኮልና የታሪክ ሰነዶችን፤ ፎቶግራፎችን በማሰስና ያለ መታከትም በየቦታው ተዘዋውሮ፣ ሰፊ ጥናትና ምርምር  በማካሄድ ነው፡፡ ደራሲ ንጉሤ አየለ፤ እስከ ዛሬ ድረስ አብዛኛው ሕዝብ የማያውቃቸውን አዳዲስ መረጃዎችንና ታሪካዊ  ክንውኖችን ተንትኖ እነሆ ብሎናል፡፡ የአሜሪካ ጋዜጦችና የዲፕሎማሲ ባለሙያዎች፤ ዳግማዊ ምኒልክን ብልህና ገናና የአፍሪካ ንጉሥ ናቸው ሲሉ  ከማድነቅም አልፈው፣ «የዓለም ታላቁ ጥቁር ሰው ምኒልክ፤ የፓን አፍሪካን የክብር ፕሬዚደንት መሆን አለባቸው» ማለታቸውን ደራሲ ንጉሤ ያስነብበናል፡፡
ደራሲው ለብዙ ዓመታት የደከመበትንና የለፋበትን የታሪክ ትሩፋቱን ያቀረበልን  መንግሥት ወይም የግል ድርጅት ባጀት መድቦለት ሳይሆን በራሱ ገንዘብ በአሜሪካ ልዩ ልዩ ግዛቶች መረጃ ለማግኘት በመዘዋወር ነው፡፡ በዚህ ዓይነት እስከ ዛሬ የተሰወሩትን ጥልቅ መረጃዎች፣ ከመላ አሜሪካና ከአንዳንድ የአሜሪካ  ደሴቶች  ውስጥ ከሚገኙ የታወቁ አብያተ መጻሕፍት፤ ታላላቅ ሙዚየሞች፤ በየቤተ መጻሕፍቱ በጥንቃቄ ከተቀመጡ ሰነዶች፤ ጋዜጦችና መጻሕፍት ጭምር በመሰብሰብና የተሰወረውን ጉዳይ በመግለጥ ነው:: በዚያን ዘመን በሁለቱ አገሮች መካከል የተጀመረው ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነትም ኋላ ላይ ለተከናወኑት በርካታ ቁም ነገሮች ዋነኛ መሠረት እንደሆነ ከመጽሐፉ መረዳት ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀው፤ ገናናው ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ በዘመናቸው፣ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር የዲፕሎማሲና የወዳጅነት ግንኙነት ያደርጉ የነበረው አንድም በደብዳቤ ወይም እንደ ራስ መኮንን የመሰሉ ታማኞቻቸውንና ባለሟሎቻቸውን ወክለውና ሌሎች መልእክተኞቻቸውን አስከትለው በመላክ ነበር፡፡
በዘመኑ ከነበረው የግንኙነት ቴክኖሎጂ ውሱንነት የተነሣ በመርከብ የሚደረገው የባሕር ላይ ጉዞ አሰልቺና ጊዜም ወሳጅ በመሆኑ ምክንያት ለአንድም ጊዜ ቢሆን ወደ ውጭ አገር ሄደው የማያውቁት ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ፤ በመልእክተኛ ደረጃ በ1884 ዓ.ም የውጭ አገር ግንኙነቱን የጀመሩት በራስ መኮንን ተጠሪነት፣ በእንግሊዝዋ ንግሥት ቪክቶርያ ልጅ፣. በኤድዋርድ 7ኛ የዘውድ በዓል ላይ እንዲገኙ፣ እነ መምህር ገብረ እግዚአብሔርን፤ ፊታውራሪ አባ ታቦርን፤ ትርጁማን ሚካኤል ብሩን፤ ፊታውራሪ ኃይለ ሥላሴ ዓባይነህን (የራስ እምሩ አባት) ከንቲባ ገብሩን ወደ እንግሊዝ በመላክ ነበር፡፡ (መርስኤ ኀዘን 1999፡84) ከእነዚህ መልእክተኞች ውጭ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ፣ ከሀገሩ ርቀት የተነሣም ሊሆን ይችላል፤ ሌሎች ሰዎችን ወደ አሜሪካ አልላኩም፡፡
ይሁን እንጂ ዳግማዊ ምኒልክ አሜሪካ እንደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ወደ አፍሪካ መጥታ የሰው አገር የማትወርርና ድንበርም የማታፈርስ መሆኗን በሚገባ በመረዳታቸው፣ ወዳጅነቷን አጥብቀው ይፈልጉት ነበር፡፡ በፕሬዚደንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ዘመን ለአሜሪካና ለኢትዮጵያ  የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሠረት የጣለውም ቆንሲል ጄ. ሮበርት ስኪነር ነው፡፡ ዓፄ ምኒልክ በወቅቱ ስለ አሜሪካ ሲገልጹ፤ “ሌሎች አገሮች ወደ አፍሪካ የሚመጡት ልክ ልጆች ወደ አባታቸው መጥተው ‘አባዬ፤ ኑዛዜ ፈጽመህ ’አንዳች ነገር ትተውልናለህ’ እንደሚሉ ዓይነት ነው፡፡ አሜሪካ ብቻ ናት በአፍሪካ መሬት የሌላትና ምንጊዜም የማትፈልግ፡፡ የአሜሪካ ፍላጎቷ የመነገድ ፈቃድ ብቻ ነው» ብለዋል፡፡ ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ይህንን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ቴዎዶር ሩዝቬልት ደስ የሚያሰኘውን የወዳጅነት ደብዳቤ ከጻፉላቸው በኋላ ነበር:: ደብዳቤውም እንዲህ ይላል፡-
“ለትንሹም ሆነ ለትልቁ  አገር ያለን አመለካከት እኩል አክብሮት የተሞላውና በእውነተኛ ወዳጅነት ላይ የተመሠረተ  ሊሆን ይገባል፡፡ የሌሎችን መብትና ፍላጎት አክብረን፣ ሐቀኛ ወዳጅነት መመሥረት ተገቢና ፍትሐዊ ነው፡፡ ይህንንም በቃላት ብቻ ሳይሆን በተግባር የምንገልጸው መሆን አለበት::”
ንግሥት ሳባ፤ በጠቢቡ ሰሎሞን ጥበብ ተደንቃና ተመስጣ ጥብብና ዕውቀትን ለመቅሰም ወደ ኢየሩሳሌም እንደተጓዘች ሁሉ፣ ዓፄ ምኒልክም  እውቀትና ጥበብ ቀስመው እንዲመለሱ በመላው አውሮፓ በእግረ ልቡናና በመንፈስ ተጉዘውና መልእክተኞቻቸውንም ወደ ፈረንሳይ፤ ኢጣሊያና እንግሊዝ ልከው፣ ሀገራቸው የሥልጣኔ ባለቤት እንድትሆን ብዙ ጥረት አድርገዋል፤ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለሀገራችን ያስገኙትም በዚሁ የጥበብና የሥልጣኔ አፍቃሪነታቸውና አሳሽነታቸው  ነው፡፡
ደራሲው ንጉሤ አየለ፤ ስለ አሜሪካና ኢትዮጵያ ወዳጅነት ለብዙ ዓመታት ያልተቋረጠ ጥናትና ምርምር በማድረግ፣ ከዚህ በፊት በአንባብያን ዘንድ የማይታወቁ አዳዲስ  መረጃዎችን ይዞልን በመምጣቱ፣  መጽሐፉን የላቀ ሥፍራ ያሰጠዋል፡፡ ደራሲው ኢትዮጵያዊነት በአሜሪካ ምን እንደሚመስል፤ በጉብኝት፤ በንባብና በፍለጋ አማካይነት፣ የሁለቱን አገራት ወዳጅነት በተመለከተ ምን ዓይነት ውጤት እንዳገኘ፤ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በሁለቱ አገሮች መካከል ስለነበረው ንግድና ወዳጅነት፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ በኋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት አጀንዳ እንደነበረ፣ አሜሪካዊው ቆንሲል ሮበርት ፒን ስኪነር የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት ለማጠናከር ስላደረገው ጥረት፤ ስለ መጀመሪያው የሩዝቬልት ካምፕ በድሬዳዋ፤ ዊልያም ኤሊስ በኢትዮጵያ ፍቅር እንዴት እንደተነደፈ -- ወዘተ ያነግረናል፡፡
በተጨማሪ፤ በምኒልክ አደባባይ፣ የሩዝቬልትን መልእክተኛ ለመቀበል ስለተደረገው ሰልፍና ሕዝባዊ ሥነሥርዓት፣ ስለ ታላቁ ጥቁር ሰው፤ ስለ ዓፄ ምኒልክ ባሕርያትና በአሜሪካውያን ዘንድ ስለነበራቸው ተወዳጅነት፤ በስጦታ  መልክ በመርከብ ወደ አሜሪካ የተጓዘው የምኒልክ አንበሳ፣ በመርከበኞች አጠራር “ቴዲ” በዋሺንግተን ዲሲ እንዴት እንዳገሳ---ከቦረና ተነሥተው አሜሪካ ስለገቡት የጥንት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤ በአሜሪካ ኢትዮጵያውያውያን ስለሠሩት ጥንታዊ ቤተ ክርስቲያን --- በፎቶግራፎች ጭምር አስደግፎ አዳዲስ ታሪኮችንና መረጃዎችን ያስተዋውቀናል፡፡ በዚህ ረገድ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ‘ዳግማዊ ምኒልክ በዓለም ላይ ምን እየተከናወነ እንደሆነ የሚያውቁ፤ መልካም ሆኖ ላገኙት ነገር ግርማ ሞገስ ያለውን አድናቆታቸውን የሚሰጡ ታላቅና ጠቢብ ንጉሥ፣ በዚህ ዘመን በአቢሲኒያ ነግሠው እንደነበር ይመሰክር ዘንድ (ይህ የምኒልክ ደብዳቤ) ለመጭው ትውልድ ይቀመጣል’ ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡
ዓፄ ምኒልክ የኢትዮጵያ ወጣቶች ዘመናዊ ትምህርት የሚማሩበት ዘመን መምጣቱንም ለአሜሪካው ቆንሲል ለሮበርት ስኪነር መናገራቸው፣ ዘመናዊ ሥልጣኔ ወደ ሀገራችን እንዲገባ የጸና እምነት እንደነበራቸው ያሳያል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ስለ ሁለቱ አገራት ብዙ ሰው ገና ያልተረዳውንና ያላወቀውን ታሪክ አስፍቶ የጻፈውና የጎደለውን ነገር የሞላው  ደራሲ ንጉሤ  አየለ፤ ታላላቅ የታሪክ ሥራዎችን እንዳበረከቱልን የጥንት ደራሲዎቻችን ሊመሰገንና ሊታወስ የሚገባው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡


Read 1943 times